1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ጥንታዊ ግኝት በያልዳ ሸለቆ - ኮንሶ

ዓርብ፣ ጥር 6 2014

በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ የሲምሶንያን ኢንስቲትውት የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ዘለቀም በጥናቱ ተሳትተፈዋል። በዚህ በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ ወር ቡድኑ ባካሄደው ጥናት ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ቅሪተ አካል እና የጥንት ሰዎች የተገለገሉባቸው የድንጋይ መሣሪያ ክምችቶች አግኝተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/45V6C
Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University

“ኢትዮጵያ የምድረ-ቀደምት መገኛ” የሚለውን የቱሪዝም መሪ ቃል የሚያጠናክር ነዉ


ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ«ቴማቲክ ፈንድ» በተገኘ የምርምር ገንዘብ በሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ቅሪት በአርኪኦሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዓለምሰገድ በልዳዶስ መሪነት ከተለያዩ ኮሌጆች እና የትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች  በደቡብ ኢትዮጵያ በኮንሶ ዞን በያልዳ ሸለቆ ከ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአርኪኦሎጂ እና የከባቢ አየር ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ የሲምሶንያን ኢንስቲትውት የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ዘለቀም በጥናቱ ተሳትተፈዋል። በዚህ በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ ወር ቡድኑ ባካሄደው ጥናት ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ቅሪተ አካል እና የጥንት ሰዎች የተገለገሉባቸው የድንጋይ መሣሪያ ክምችቶች አግኝተዋል፡፡ እነዚህ የእንስሳት ቅሪተ አካላት እና የድንጋይ መሣሪያዎች ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ሊኖራቸው እንደሚችል ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ የሲምሶንያን ኢንስቲትውት የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ዘለቀ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል የተጋበዙት፤ ለዶክትሬት ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎችን በፊልድ ሥራ እገዛ ለመስጠት ነዉ። 
በበያልዳ ሸለቆ - ኮንሶ በተካሄደዉ ጥናት እና ምርምር የጥንት የዝሆን ዝርያ፣ የጋማ ከብት ዝርያዎች፣ የአሳማ ዝርያ፣ የጉማሬ ቅሪተ-አካል፣ የከብት ቅሪተ-አካሎች፣ የየብስ እና የባህር እንስሳት ቅሪተ-አካሎች እንዲሁም ሌሎች የዱር እንስሳት ቅሪተ-አካሎች መገኘታቸዉን ዶክተር ዮሐንስ ዘለቀ ተናግረዋል። በግኝቱ የሰው ልጅ የባህል ጅማሮ አመልካች የሆኑ ጥንታዊ የድንጋይ መሳሪያዎች መገኘታቸዉን የምርምሩ መሪ በአርኪኦሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዓለምሰገድ በልዳዶስ ገልፀዋል። ጥንታዊ ግኝቱ ከቅሪተ-አካል እና የድንጋይ መሳሪያ ክምችቱ እና ክምችቱ ከተገኘበት ውስን መልክአ ምድር አንጻር ሲተመን እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ከተገኙት የቅድመ-ታሪክ ስፍራዎች ከግንባር ቀደሞቹ ጋር ሊያስመድበው የሚያስችለው ነው፡፡ ጥናቱ ምንም እንኳን በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም፣ የያልዳ ሸለቆ ያለፈ ዘመን የከባቢ አየር ለውጥን ለማጥናት፣ የባህል እና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች የተክለ-ሰውነት ዘገምተኛ ለውጥን ለማጥናት፣ የከርሰ ምድር እና የመልክአ ምድር ለውጥ ሂደትን ለማጥናት፣ የጥንት የእጽዋት ዝርያዎችን ለማጥናት አመቺ ስፍራ እንደሆነ ምሁራኑ ተናግረዋል። 
“ኢትዮጵያ የምድረ-ቀደምት መገኛ” የሚለውን የቱሪዝም መሪ ቃል የሚያጠናክር ግኝት ነው ያሉት በአርኪኦሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዓለምሰገድ በልዳዶስ ፤ የሳይንስ ጥናቶች እና ግኝቶች ለሃገር እና ለህብረተሰብ ቀጥተኛ የሆነ አስተዋጾ ሊኖራቸው ይገባልም ነዉ ያሉት። እንደነዚህ ያሉ የባህል እና የተፈጥሮ አመልካች የሆኑ ስፍራዎች ለምተው አስፈላጊው መሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ሊያሳድግ እንደሚገባም አፅኖት ሰጥተዋል። የአካባቢው ማህበረሰብም ከሚካሄዱ ጥናቶች እና ግኝቶች ተጠቃሚ መሆን አለበት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም እንደነዚህ አይነት ልማቶች እውን እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት (ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከቱሪዝም ሚኒስትር) ጋር ተባብሮ በትጋት እንደሚሰራ ገልፀዋል። 
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች እና ምሁራን የምርምራቸዉን ሂደት በየጊዜዉ የሚያሳዉቁን መሆኑን ቃል ገብተዉልናል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዓለምሰገድ በልዳዶስ እና ዶክተር ዮሐንስ ዘለቀ ለሰጡን ቃለ ምልልስ እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።    

Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University
Äthiopien neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University
Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University

 
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ