1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ የሚዋቀረው ‹‹ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል ››

ቅዳሜ፣ ኅዳር 24 2015

በደቡብ ክልል ሲነሳ የቆየውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለመመለስ የፌዴሬሽን ም/ቤት በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ አሁን ያለው ክልል በሁለት እንዲከፈል የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/4KR5l
Äthiopien Büro der südlichen Nationen und Nationalitäten (SNNPR)
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምስረታ እና አንድምታው

‹‹ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል ››                                                 

በደቡብ ክልል ሲነሳ የቆየውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለመመለስ የፌዴሬሽን ም/ቤት በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ አሁን ያለው ክልል በሁለት እንዲከፈል የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ የጉራጌ ፣ የሃድያ ፣ የስልጤ ፣ የሀላባ ፣ የከንባታ ጠምባሮ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ በአንድ የጋራ ክልል ሥር እንዲቀጥሉ የቀረበውን አጀንዳ ከጉራጌ በስተቀር ሁሉም የዞንና የልዩ ወረዳ ም/ቤቶች ውሳኔውን በይሁንታ መቀበላቸው የሚታወቅ ነው ፡፡ የጉራጌ ዞን ም/ቤት ግን ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው አስቀድሞ ነሀሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነበር፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የዞኑ ቁልፍ አመራሮች ከሀላፊነት ተነስተዋል፡፡ የጋራ አደረጃጀቱን የሚቃወም በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በተለይ በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ በተደጋጋሚ ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ እስከአሁንም አድማውን አስተባብረዋል በሚል የተጠረጠሩ 70 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የክልሉ መንግሥት ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡ አሁን ላይ ዞኑ በፀጥታ ዕዝ / command post / ሥር እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡ 

የቡታጅራው ምክክር  

የደቡብ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላለፉት ሁለት ቀናት በቡታጅራ ከተማ በመሰባሰብ በአደረጃጀት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ም/ቤት ጉራጌ ራሱን በቻለ ክልል እንዲደራጅ በመጠየቅ የጋራ አደረጃጀቱን ውድቅ ካደረገ ካለፈው የነሀሴ ወር 2014 ዓ.ም. ወዲህ በክልል ደረጃ ይህን መሰሉ ምክክር ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ በውይይቱ ላይ መንግሥት የሚያስተዳድራቸውም ሆኑ ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች አልተጋበዙም፡፡ ያም ሆኖ የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በውይይቱ ላይ የደቡብ  ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ  ርስቱ ይርዳዉን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች መሳታፋቸውን በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ መሠረት ያለህዝበ ዉሳኔ በቀጥታ በአዲስ መልክ  ለሚዋቀረውና ‹‹ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል ›› የሚል ሥያሜ ያለውን ክልል  ለማደራጀት አሥፈላጊ  የሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ አንደሚገኙ ተገልጿል። በአሁኑወቅትም ክልሉን ለማደራጀት ሥራውን ያስተባብራል የተባለ  የኘሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው መግለጻቸውን ነው ቢሮው የጠቀሰው ፡፡ 

አደረጃጀቱ ከህገ መንግሥታዊ ቅርቃር እንዴት ይውጣ ? 

‹‹ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል ›› በተባለውን አዲስ ክልል ዙሪያ የጉራጌ ዞን ም/ቤት አስቀድሞ ያሳለፈው ውሳኔ የአደረጃጀት ሂደቱ አልጋ በአልጋ እንዳይሆን ያደረገው ይመስላል፡፡ በተለይም በአንድ በኩል የጉራጌ ዞን ም/ቤት በጋራ አደረጃጀቱን ይሁንታ በነፈገበትና በሌላ በኩል ደግሞ አደረጃጀቱን ገቢራዊ የማድረግ ሂደት መጀመሩ ብዙዎች ጉዳዩን ከሕግ አንጻር አከራካሪ አድርጎታል እያሉ ይገኛሉ፡፡  ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ኘሮፌሰር ሺመልስ አሻግሬ በጋራ መደራጀቱና መቀጠሉ በራሱ ችግር የለውም ነገር ግን አፈጻጸሙ ህገ መንግሥቱን የሚሸራርፍ ነው ይላሉ ፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ህግ መንግሥት አንቀጽ 47 ሥር የተዘረዘሩት እራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች በቀጥታ ለብሄር ብሄረሰቦች የተሰጡ ናቸው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሺመልስ  ‹‹  ጉራጌም የራሴን ክልል መመሥረት ነው የምፈለግው የሚለው ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግሥታዊ መብት የሚመነጭ ነው  ፡፡  ይህንን ደግሞ የህዝብ ውክልና ባለው የዞን ምከር ቤት አረጋግጧል ፡፡ የዞን ምክር ቤቱን ውሳኔ ወደ ጎን ትቶ አደረጃጀቱን ተፈጻሚ ማድረግ በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው  ›› ብለዋል  ፡፡  

በዞኑ ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ እና በአንድ የጋራ ክልል የመደራጀት አማራጭ በህገ መንግሥታዊ ተቃርኖ ውስጥ ሳይገባ እንዴት ሊፈጸም ይችላል በሚል በዶቼ ቬለ DW  የተጠየቁት ረዳት ፕሮፌሰር ሺመልስ አሁን የተጀመረውን የጋራ አደረጃጀት በአተገባበር ሂደት ሊያስከትል የሚችለውን ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ለመታደግ የጉራጌ ዞን ም/ቤት ዳግም ጉባዔውን በመጥራት የቀደመ ውሳኔውን መቀልበስ ይኖርበታል ፡፡ አሊያም የዞኑ ምክር ቤቱን ወሳኔ ዳግም እንዲታይ ለማድረግ ከአጠቃላይ የዞኑ ህዝብ የአምስት በመቶ ያህል ፊርማ ማሰባሰብ ይገባል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በፖለቲካ ውሳኔ ለማስፈጸም የሚደረግ አካሄድ ያልተገባ የህግ ሂደት / proccegeral irragularity / ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ የህግ ክርክር የሚያስነሳ ሊሆን ይቻላል  ›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ፎቶ ፡ ከዶቼ ቬለ ፋይል የተወሰደ  

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ