1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ዓመትና የባንዲራ ዉዝግብ በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ መስከረም 4 2011

የአዲስ ዓመት ዋዜማና መባቻ ስሜትእንዲሁም የባንዲራና የአርማ ዉዝግብ በአዲስ አበባ የዛሬዉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት የዳሰሳቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/34tQZ
Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien
ምስል Yohannes Geberegziabeher

Social Media Review 14-9-2018 MMt - MP3-Stereo

አሮጌዉ 2010 አ/ም ተሸኝቶ ያለፈዉ ማክሰኞ መስከረም አንድ ቀን አዲሱን አመት 2011 ተተክቷል።የዘንድሮዉ አዲስ አመት ከሌሎቹ በተለዬ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አዲስ የለዉጥ ተስፋና ስጋት በአንድ ላይ የተቀላቀለበት ነዉ።በዋዜማዉ በአዲስ አበባ የሚሊኔም አዳራሽ ጠቅላይ ሚንስትሩ በተገኙበት የተለያዬ የፖለቲካ አጀንዳና የሀሳብ ልዩነት ያላቸዉ ሰዎች ከአራት ወራት በፊት ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ በፍቅር ሲጨባበጡና ሲተቃቀፉ  ማየት አብዛኛዉ ህዝብ አዲሱን አመት በተስፋ እንዲመለከት አድርጓል።በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ብዙዎችን አነጋግሯል። ያፌት ጉዴታ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ «ይህንን ሳያዩ የሞቱ ሰዎች ገነት እንኳ ቢገቡ ይቆጫቸዋል።እኔ ግን እድለኛ ነኝ  ይህን ለማየት ታደያለሁና »በማለት በደስታ ማንባታቸዉን ከሚያሳይ ምልክት ጋር ሀሳባቸዉን አጋርተዋል።አረቢ አረጆ የተባሉ  የፈስቡክ ተከታታይ ደግሞ  ደግሞ «እንኳን ከዘመነ እስር ወደ ዘመነ መፈታት፣ከዘመነ ጥላቻ ወደ ዘመነ ፍቅር  አደረሰን» ሲሉ ፅፈዋል። «ብዙዎች ወደናፈቋት ሀገራቸው ተመልሰዋል፣ በርካቶች ከግፍ እስር ቤት ተፈተዋል። በዚህ ደስ እንሰኛለን። መልካም አዲስ ዓመት ለሁላችሁም!»ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በቲዉተር ገፁ ያሰፈረዉ ነበር። 
የአዲሱ አመት መባቻ ደግሞ ሌላ ትዕይን ይዞ ነበር የመጣዉ።በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰሜን ምስራቃዊ ድንበር ፤ዛላአንበሳ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ከኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና በድንበር ከሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች ጋር አዲሱን አመት ሲያከብሩ መታየቱ ሌላዉ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ።«በአዲሱ አመት ከተኩስ ድምፅ ወደ ከበሮ ድምፅ ተሸጋግረናል» በማለት ነበር አሰገዶም የተባሉ ሰዉ በፌስቡክ ገፃቸዉ ስሜታቸዉን የገለፁት። እዉነተኛ እዉነት የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ «ከእንግዲህ የሁለቱ ሀገራት የጦር መሳሪዎች መድፍና ክላሽ ወደ ማጭድና ማረሻ ይቀየራሉ።»ሲሉ ፅፈዋል።
አባይነህ አንያ ኢትዮጵያ የተባሉ ሌላዉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ካሰፈሩት ምኞት በጥቂቱ ደግሞ «እንኳን ለ2011 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት።ሁሉም ወደ ፈቀደው ሄዶ በነፃነት ይኑር! የሰው ልጅ ከብሔሩ ይበልጣል! ሰው ነኝና ሰውነቴን አትቀሙኝ 
የኢትዮጲያዊነት ውበት አንድነት የሚደምቅበት ይሁን አሜን!!»ሲሉ ምኞታቸዉን አስፍረዋል።
ሳቢሳዉ በሚል ስም በፌስ ቡክ ገፃቸዉ የፃፉት ደግሞ እንዲህ ይላል።«የሚመች መንግስት አግኝተናል ።ፈጣሪ የተመቸ ህዝብ እንዲሰጠን የአዲስ አመት ምኞቴ ነዉ »
በዚሁ የአዲስ አመት ዝግጅት ላይ ሁለት እትማማች ወጣት የሴት ወታደሮች ተቃቅፈዉ የተነሱት ፎቶ  ሰሞነኛ መነጋገሪያ ነበር። በጉዳዩ ዳዊት ከበደ የተባሉ ሰዉ በፌስ ቡክ ገፃቸዉ እንዲህ አስፍረዋል። «እነዚህ ሁለት ወጣት የሰራዊት አባላት እህትማማቾች ናቸው፤ አዎ እህትማማቾች። አንዷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ስትሆን ሌላኛዋ ደግሞ የኤርትራ ሰራዊት አባል ናት። በዛሬው እለት የዛላምበሳ ድንበር ተከፍቶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በይፋ ሲጀመር እነኚህ እህትማማቾችም ከ20 አመት በኋላ በአካል ይገናኙ ዘንድ ፈጣሪ ፈቅዶ፣ በአይነ ስጋ ተገናኝተው እንባ ተራጩ።በአጭሩ ድንበሩ ተከፍቶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጀመር አበክረን የወተወትነው ለዚህ ነው።»  
«በ2011ዓ.ም ኢትዮጵያ ለሁላችንም የተሻለች እንድትሆን እንዲህ ብናደርግስ» በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ ዮናስ ወልደየስ በፌስ ቡክ ገፁ ካሰፈረዉ የአዲስ አመት ምኞት የተወሰነዉ እንዲህ ይላል።
«አዲሱ አመት የሌሎችን ቁስል የሌሎችን በደል ለመረዳት የምንሞክርበት ዘመን ቢሆን፤አዲሱ አመት ማሀበራዊ ገፆችን በሃላፊነተ የምንጠቀምበት ዘመን ቢሆን፤ዛሬ የምንፅፋቸው የምናካፍላቸው ሃሳቦች የነገ ታሪካችን አካል እንደሆኑ መርሳት የለብንም፡፡ለመልካም አበርክቶአችን ምስጋና፣ለጥፋታችን ተጠያቂነት አይቀርልንም፡፡በተለይ አንድን የተወሰነ ህዝብን፣ቡድን፣ ብሄረሰብ፣ ሃይማኖት የጥቃትና የበደል ኢላማ አድርገው የሚፃፉ መልእክቶች በዓለምአቀፍ ህግ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይቀር ተጠያቂ እንደሚያደርጉ መዘንጋት የለብንም፡፡ዛሬ የምንከትባት እያንዳንዷ ሃሳብ ነገ ምን መልካም ነገር ይዛ እነደምትመጣልን ወይም ምን መዘዝ ይዛ እንደምትመጣብን አስቀድመን መተንበይ ያሻናል፡፡እነሆ በኛ ላይ የሚመዘዘውን የገዛ ማስረጃችንን እያደራጀን እንደሆነ እንወቅ፡፡DELETE በማድረግ የምናስቀረው እውነት የለም፡፡በተለይ ሁሌም ልዩነትን፣ጥላቻን፣በደልን፣በቀልን የምናስፋፋ ሰዎች እስቲ በአዲስ አመት አዲስ የእርቅ መንገድ እንጀምር፡፡»በማለት አስፍሯል።
ያለፈዉ ቅዳሜ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮችና አባላትን በመቀበል ደምቃ የሰነበተችዉ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ለመቀበል የፊታችን ቅዳሜ ቀጠሮ ተቆርጦ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።ይሁን እንጅ የኦነግ አርማና ባንዲራ ለመስቀል፤ ለአርበኞች ግንቦት 7 መቀበያ የተተከሉ ባንዲራዎችና አርማዎችን አንሱ አታንሱ በሚልና የከተማዋን ጎዳናዎች ቀለም በመቀባት ዙሪያ በጥቂት ወጣቶች የተጀመረዉ አለመግባባት መላዉ አዲስ አበባን በመናጥ ላይ ይገኛል። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ጉዳዩ እጅግ አነጋጋሪ ሆኗል።
አበበ ቶላ «አብረን ከምንወድቅ አብረን ብንቆም የተሻለ ነው! በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገፁ እንዲህ ፅፏል።
«ወዳጄ… ይወክለኛል የምትለውን ሰንደቅ አላማ ባሻህ ግዜ ብታውለበልብ ችግር የለውም። አንዳችን የአንዳችንን አርማ እና ባንዲራ መቀበል የውዴታ ግዴታችን ነው! ነገር ግን የአንዱን ለመስቀል የሌላውን ማውረድ የአንዱን ለመቀባት የሌላውን ማጥፋት ኢ ዴሞክራሲያዊ ነው። በዴሞክራሲ ውስጥ ትልቁ ቁምነገር መቻቻል ነው። ባይመችህም ባይጥምህም በአንድ አገር ላይ እስካለህ ድረስ ተከባብሮ እና ተቻችሎ መኖር ምርጫ የለውም።አብሮ ከመውደቅ ይልቅ አብሮ መቆም የተሻለ ነው። ሃገሪቷ ለሁሉም በቂ ናት… የኔ ብቻ ከፍ ይበል ካልን ግን መጨረሻችን አያምርም!»
ዮኒ ገረመዉ ደግሞ«ክቡር የሆነውን የሰው ልጅን አጣጥለን ስናበቃ ለአርማና ለባንድራ ክብር በመስጠት ነብስ ሲጠፋ ማየት ነውረኝነት ነው።
በራሳችን ትንሽ አርቀን ማሰብ የማንችል ከሆነ ከኛ በእውቀትና በኑሮ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ምክር እንስማ።»ሲሉ ፅፈዋል።
«ሁሉም ፅንፍ ይዘዋልና በድጋሚ መሀሉን ስለመጠቆም በሚል» ቴዲ ጌታቸዉ በፌስ ቡክ ያሰፈሩት ጽሁፍ ደግሞ፤ከረጅሙ ባጭሩ እንድሂ ይላል።
 
በመሰረቱ አዲስ አበባ የማንም ብቸኛ ይዞታ አይደለችም:: ከሁሉ በቅድሚያ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት አልፎም የመላው ኢትዮጵያውያን ናት አልፎም የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ናት::ለእንግዳ አቀባበል ሲባል አይደለም ታላቁን የኦሮሞ ህዝብን "እወክላለሁ የሚለው ኦነግ ቀርቶ የማንም ባንዲራ ሊውለበልባት ሊሰቀልባት ይችላል:: አይደለም የኢትዮጵያው ኦነግ ቀርቶ የኡዝቤኪስታንና የጉዋቲማላ ሁሉ ሲውለበለብባት አይደለም የምትውለው?! ስለዚህ የኦነግ ደጋፊ የኢትዮጽያ ልጆች የሌላውን መብት ሳትጋፉ እንደፈለጋችሁ አሸብርቁ; በደመቀ ሁኔታ ዝግጅታችሁን አስኪዱ:: በፍቅር ሲሆን ሁሉም ያደምቅላችኃል!
ከቬሮኒካ መላኩ ረዥም ፅሁፍ የተቀነጨበዉ የፌስ ቡክ መልክት ደግሞ የአዲስ አባባን እንግዳ ተቀባይነት ያወሳል።«የአዲስ አበባ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ ለተወለዱት ዶ/ር አቢይ አህመድ እና ለማ መገርሳ ድጋፍ በመስጠት የቀደመው ማንም ህዝብ የለም ። የአዲስ አበባ ህዝብ ለእነዚህ ከኦሮሞ ህዝብ ለወጡ መሪዎች ብሄርና ዘር ሳይመርጥ ሰኔ 16 ቀን መስቀል አደባባይ ደሙን አፍሶላቸዋል። 
ጃዋር መሀመድም ሲመጣና ያ ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ አዲስአበባ ገብቶ አቀባበል ሲደረግለት ኮሽ ያለ ነገር አልነበረም።ይሄ የሚያመለክተን የአዲስአበባ ህዝብን ፍቅር እና አስተዋይነትን ነው »ብለዋል።
የሰሞኑ የባንዲራ ንትርክ  ከአዲስ አበባ ወጣቶች አልፎ መንግስትን በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቧል። ከዶክተር አብይ መግለጫ በተጨማሪ፤የኦሮሚያ ክልል ፤የአዲስ አበባ አስተዳደር ፤የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ አስፈፃሚ ኢብሳ ነገዎ ጋር በመሆን መግለጫ የተሰጠበት ጉዳይ ነዉ። የመንግስት አካላት ስጋታቸዉን በግል የፌስ ቡክ ገፃቸዉ እያስቀመጡ ነዉ። የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚንኬሽ ሀላፊ አቶ ታዬ ደንደአ በግል የፌስ ቡክ ገፃቸዉ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል።
«አሁንም ጥንቃቄ »በሚል ርዕስ አቶ ታዬ ደንድአ በግል የፌስ ቡክ ገፃቸዉ የጉዳዩን አሳሳቢነት አስፍረዋል።
«ከዝህ በፊት ብያለሁ። አሁንም ደግሜ እላለሁ! ከትናንሽ አጀንዳዎች እንዉጣ። ስለ ምልክት ሳይሆን ስለሀገር ከልብ እናስብ! ሀገር ካለች ባንዲራ መስቀል እና ሀዉልት መገንባት አይከብድም! ሀገር ከሌለ ግን ባንዲራ ብቻዉን ትርጉም የለዉም! አሁን ሊቢያ ወይም የመን ላይ ባንዲራ መያዝ ወይም ሀዉልት መትከል ምን ያደርጋል? ችግራችን በባንዲራ ወይም በሀዉልት አይፈታም።የግጭት ነጋዴዎችን ሴራ እናክሽፍ።ጆሮ ያለዉ ይስማ»ብለዋል።
 

Äthiopien Addis Abeba, Unruhen
ምስል DW/B. ze Hailu
Logo Patriot Ginbot 7
Äthiopien Addis Ababa - Isaias Afwerki und Abiy Ahmed
ምስል Reuter/T. Negeri
Äthiopien Addias Ababa - Meron Alemayehu - ex-rebellenmitglied Patriotic Ginbot 7 erreicht den Addias Ababa
ምስል F. Asimamaw

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ