1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ተሿሚዎቹ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንትና ም/ፕሬዝዳንት

ማክሰኞ፣ ጥር 9 2015

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸው ተነገረ። በፈቃዳቸው ሥራ በለቀቁት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ምትክ አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ወይዘሮ አበባ እምቢአለ የተባሉ ሰዎች ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሾመዋል።

https://p.dw.com/p/4MKL5
Äthiopien Der neu ernannte Präsident Tewdros Mihret und der Vizepräsident des Obersten Gerichtshofs Abeba Embiale
ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸው በይፋ የታወቀዉ አዲስ ሹመት ሊሰጥ ሲል ነዉ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸው ተነገረ። በፈቃዳቸው ሥራ በለቀቁት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ምትክ አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ወይዘሮ አበባ እምቢአለ የተባሉ ሰዎች ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሾመዋል ። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእጩነት ያቀረቧቸው አዲሶቹ ተሿሚዎች ላለፉት አራት ዓመታ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩትንና በፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸው የተገለፀውን ወይዘሮ መአዛ አሸናፊንና አቶ ሰለሞን አረዳን የሚተኩ ናቸው።  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኝ ያሉትን የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት አዲሶቹ ተሿሚዎች ነፃ ፣ ገለልተኛ እና ከብልሹ አሰራር የፀዳ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን ጠንካራ አመራር እንደሚሰጡ በማመን ሹመቱን ተቀብለው በአብላጫ ድምፅ አጽድቀውታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚያገለግሉ የተነገረላቸው አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሾሙ ወይዘሮ አበባ እምቢአለ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ዛሬ ጥር 9 ቀን 2015 ዓ. ም ተሾመዋል።
አዲሱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በቀድሞው ኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ እና በአቢሲኒያ ባንክ በከፍተኛ ነገረ ፈጅነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ አገልግሎት በኃላፊነት እንዲሁም በብርሃን ኢንሹራንስ በቦርድ ሰብሳቢነት ማገልገላቸው ተገልጿል።
ግለሰቡ የዳኝነት ልምድ የሌላቸው መሆኑ ተጠቅሶ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበበት ይህ ሹመት በሦስት ድምጽ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ አዲሱ ሹመት ከከፍተኛ ኃላፊነት ጋር የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል። ኢዲስ ተሿሚዎች "የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን የማጠናከር፣ ጠንካራ ተቋም የመገንባት ፣ ከሕዝብ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እና እምነት ተጥሎባቸዋል" የምክር ቤት አባላት ይህ ሹመት ቀድሞ እንዳልቀረበላቸው በመግለፅ ይህ አሰራር መስተካከል የለበትም ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህንን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ዐፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበላይ ኃላፊዎችን አሰያየም ሂደት በመጥቀስ አሰራሩ ሕግን የተከተለ መሆኑን በምሳሌ አስረድተዋል። አያይዘውም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እና ምክትል እንባ ጠባቂዎችን "የአመራር ሥርዓቱን ለማስተካከል ሥራ መጀመሩን" ጥቆማ በመስጠት ጭምር የጠቅላይ ፍርድ ባት መሪዎች በጡረታ ፣ በሕመም ወይም በሌላ ምክንያት ከሥራ ሊለቁ እንደሚችሉ እና ይሄኛው ሹመት ያስከተለው መልቀቂያ ግለሰቦቹ ባቀረበት ጥያቄ መሰረት የተሰጠ አዲስ ሹመት መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የቀድሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀቁ የተባለው ምን ያህል ተጨባጭ እና እውነት ነው?  የሚል ጥያቄም ከምክር ቤት አባላት ቀርቦ ነበር። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ "በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል ፣ ይህም ሕጋዊም ተገቢም አሠራር ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የፍትሕ ሥርዓቱ ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ ያልተለየው ፣ ፍትሕ በገንዘብ የሚገዛና የሚሸጥበት ፣ በዘመድ አዝማድ አላግባብ ተጠቃሚነትና በአንፃሩ እንግልት የሚታይበት፣ የፍርድ ቤት ትእዛዞች በአግባቡ የማይፈፀምበትና በውስብስብ ችግር ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል።

Äthiopien Der neu ernannte Präsident Tewdros Mihret und der Vizepräsident des Obersten Gerichtshofs Abeba Embiale
ወይዘሮ አበባ እምቢአ: የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ምክትል ፕሬዝዳንትምስል Ethiopian Broadcasting Corporation
Äthiopien Der neu ernannte Präsident Tewdros Mihret und der Vizepräsident des Obersten Gerichtshofs Abeba Embiale
አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation


ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ