1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍልሰት ጉዳይ ረቂቅ ህግ 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 15 2010

በአዲሱ ህግ  ጀርመን ውስጥ በሙያቸው ተፈላጊ የሆኑ የውጭ ዜጎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መሥራት የሚያስችሏቸው መስፈርቶች ተቀምጠዋል። የትምህርት ደረጃ፣ እድሜ፣ የቋንቋ ችሎታ፣ የተጨበጠ የሥራ እድል እና ኑሮን በራስ የመምራት አቅም ጀርመን ለሥራ የሚመጡ የውጭ ዜጎች የሚመረጡባቸው መስፈርቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/33WSq
Ausländische Fachkräfte in Saudi-Arabien
ምስል Getty Images/AFP/F. Nureldine

አዲሱ የጀርመን የፍልሰት ጉዳይ ረቂቅ ህግ

የሰለጠነ የሰው ኃይል ከውጭ ወደ ጀርመን በቀላሉ እንዲገባ ያስችላል የተባለው አዲሱ የጀርመን የፈላስያን ጉዳይ ህግ ዕውን ሊሆን የተቃረበ ይመስላል። ጀርመን ውስጥ በአንዳንድ የሞያ መስኮች በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለ። በተለይ የመሀንዲሶች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሙያተኞች እና የጤና ባለሞያዎች እጥረት ከፍተኛ ነው።  የኤኮኖሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት  እንዳስቀመጠው 1.6 ሚሊዮን ክፍት የስራ ቦታዎች አሉ። በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚታየውን ጉድለት ለመሙላት በመፍትሄነት ከሚቀርቡት ውስጥ ከውጭ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማስገባት አንዱ ነው። ይህም ከ20 ዓመታት በላይ ሲያነጋግር ሲያከራክር እና ሲያወዛግብ የቆየ ጉዳይ ነው። ከአከራካሪዎቹ ጉዳዮች ውስጥ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ከውጭ ይግባ ፣የለም ጀርመን ያሉ ስራ አጦችን ችግሩ ባየለባቸው ዘርፎች በማሰልጠን ለመተካት ጥረት ይደረግ የሚሉ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ከዚሁ ጋርም የሀገሪቱ የፍልሰት ጉዳይ ህግ የውጭ ዜጎችን በተለይም በልዩ ክህሎታቸው የሚፈለጉትን ባለሞያዎች የሚማርክ አለመሆኑ ችግሩ እንዳይፈታ እንቅፋት ሆኖ መዝለቁ ነው የሚነገረው። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሙያቸው የሚፈለጉ የውጭ ዜጎች በቀላሉ ጀርመን ገብተው እንዲሰሩ ያስችላል የተባለ  አዲስ ህግ በቅርቡ አርቅቋል። የጀርመን ሥራ ሚኒስቴር እና የኤኮኖሚ ሚኒስቴር የተስማሙበት ይህ ረቂቅ ከአንድ ሳምንት በኋላ ለጀርመን ካቢኔ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ ህግ እንደሚጠቁመው የችግሩ መንስኤ በሀገሪቱ ሥራ አጥነት መቀነሱ እና ከወጣቱ ይልቅ በእድሜ የገፋው ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ነው። በዚህ የተነሳም የጀርመን ኩባንያዎች የሰው ኃይል እጥረት ባለባቸው የስራ መስኮች ሙያተኞችን ለማግኘት ለሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች የበለጠውን እድል ሲሰጡ ቢቆዩም የሚፈልጉትን ሙያተኛ ማግኘት አለመቻላቸው በረቂቁ ተገልጿል። እናም ጀርመን ከአውሮጳ ህብረት ውጭ ከሦስተኛው ዓለም ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ሙያተኞችን ማስገባት የግድ ይላታል በረቂቁ እንደሰፈረው። ሀገሪቱ የዛሬ 3 ዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን  ስትቀበል  የሞያተኞች እጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይቀንሳል የሚል ግምት ነበር። ሆኖም በጀርመኑ የኤኮኖሚ ትብብር እና የልማት ድርጅት የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪ ቶማስ ሊቢሽ እንደሚሉት ይህ ተስፋ እንደተደረገው መፍትሄ ሊሆን አልቻለም። ሊቢሽ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ስደተኞች በብዛት መግባታቸው ጥቅም ነበረው። ግን ያኔ ወደ ጀርመን የገባው ስደተኛ ግን እዚህ ያለውን የሥራ ገበያ የሚመጥን አልነበረም። 
« ስደተኞች መግባታቸው በተወሰነ ደረጃ ረድቷል። ሆኖም አብዛኛዎቹ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ በኢንዱስትሪው እና በጤና ዘርፍ ሙያተኞች የሆኑ ሰዎች ይመጣሉ። ሆኖም ለሥራው የሚፈልገው አቅም የሌላቸው  ወይም የሥራ ገበያው የማይፈልጋቸው ናቸው። ከ2 ከ3 ዓመት በፉት የገቡት ስደተኞች ተስፋ እእንዳደረግነው ሆነው አላገኘናቸውም።» 
በአዲሱ ህግ  ጀርመን ውስጥ በሙያቸው ተፈላጊ የሆኑ የውጭ ዜጎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መሥራት የሚያስችሏቸው መስፈርቶች ተቀምጠዋል። የትምህርት ደረጃ፣ እድሜ፣ የቋንቋ ችሎታ፣ የተጨበጠ የሥራ እድል እና ኑሮን በራስ የመምራት አቅም ጀርመን ለሥራ የሚመጡ የውጭ ዜጎች የሚመረጡባቸው መስፈርቶች ናቸው። የውጭ ዜጎች ለነዚህ መስፈርቶች የተቀመጠውን ነጥብ ካሟሉ ጀርመን መግባት ይፈቀድላቸዋል። የፖለቲካ ሳይንስ እና የህግ ምሁሩ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ  ከከዚህ ቀደሞቹ መመዘኛዎች ተፈላጊ ሙያተኞችን የሚስቡ አልነበሩም ይላሉ። በዚህ የተነሳም ችግሩን መፍታት አለመቻሉን ያስረዳሉ። ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር እያነጻጸሩ ስለ አዲሱ ረቂቅ ህግ በሰጡት አስተያየት  በውስጡ የተቀመጡት መስፈርቶች የውጭ ዜጎችን መማረክ መቻላቸው ያጠራጥራል ይላሉ ዶክተር ለማ ።
ጀርመን የውጭ ዜጎችን ለሥራ እየመለመለች ወደ ሀገርዋ ማስገባት የጀመረችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። ያኔ የሀገሪቱ ኩባንያዎች ሠራተኞች በእጅጉ ያስፈልጓቸው ነበር። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1950 ዎቹ እና 60ዎቹ በጦርነቱ የወደመውን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልግ የሰው ኃይል በርካሽ ጉልበት ጀርመን ገባ።  በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች ከኢጣልያ፣ ከግሪክ እና ከቱርክ  «እንግዳ ሠራተኞች» እየተባሉ መጥተው በሀገሪቱ የኤኮኖሚ ተዐምር ማምጣት ተቻለ። ከዚያን ወዲህ የውጭ ዜጎችን የሚመለከተው የጀርመን ህግ እንዳወዛገበ ነው። ለሥራ የመጡ የውጭ ዜጎች ሥራቸው ሲያበቃ ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ጀርመን መቅረታቸው ከሚያወዛግቡት ጉዳዮች  አንዱ ሆኖ ዘልቋል። በነዚህ ውዝግቦች መንስኤ የፌደራል መንግሥቱ በጎርጎሮሳዊው 1973 የውጭ ዜጎችን ለሥራ መመልመልን አስቁሞ ነበር። በ2000 ዓም መንግሥትን ይመራ የነበረው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ይህን እገዳ አንስቶ በተለይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በምህጻሩ የአይ.ቲ ባለሞያዎች በአሜሪካኑ ግሪን ካርድ አምሳያ ጀርመን እንዲገቡ ተደረጓል። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የፖለቲካው ትኩረት በሥራ ወደ ጀርመን የሚገቡ ስደተኞች እና አጠቃላዪ የፍልሰት ጉዳይ ሆነ። ጀርመንን አሁን የሚመራው የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲዎች እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ተጣማሪ መንግሥት በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ሲመሰረት አንድ የፍልሰት ጉዳይ  ህግ ለማውጣት ተስማምቶ ነበር ። በዚሁ መሠረት የተዘጋጀው አዲሱ ሰነድ በጀርመን ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር በአግባቡ እና በግልጽ አሰራር መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ ተጠቅሷል። ከዚህ ቀደም የተቀመጡ አንዳንድ ገደቦችን ማንሳት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። ለዓመታት ለዘለቀው ችግር መፍትሄ ያስገኛሉ የተባሉ ሌሎች ህጎችም ወጥተው ነበር። አሁን ሌላ አዲስ ህግ ያስፈለገው የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪው ሊቢሽ እንደሚያስረዱት የቀደሙት መሻሻል ስላለባቸው ነው። 
«ከህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘ ምክንያት ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል። በሚቀጥለው ዓመት ብዙ ሰዎች በጡረታ ይሰናበታሉ። እነርሱን የሚተካ በቂ ወጣት የለም። ስለዚህ ከቀድሞው የበለጠ የሠራተኛ ኃይል ያስፈልገናል። እነዚህ ማሻሻያዎች ስለሚያስፈልጉን ጥሩ እና የፍልሰተኞች ጉዳይ ህግ ያስፈልገናል።»
በእስከዛሬው ህግ በማንኛውም ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሀገር ውስጥ አመላካቾች ነበር። ሠራተኞችም ከውጭ የሚገባ የሰው ኃይል ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በሆነባቸው ሥራዎች ብቻ ነበር የሚፈለጉት ። የሚገቡትም ሥራ ካገኙ በኋላ ነበር ይሁን እና  የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD አሁን ይህን የሚቀይር ሃሳብ ይዞ ነው የቀረበው። ወደፊት የውጭ ዜጎች ሥራ ሳያገኙም ለሥራ ፍለጋ ጀርመን መምጣት ይችላሉ። ሥራ መፈለጊያ የ6 ወራት ጊዜ ይሰጣቸዋል ተብሏል። በዶክተር ለማ እምነት ይህም የውጭ ዜጋ ሞያተኞች ጀርመን ለሥራ ፍለጋ እንዲመጡ የሚያበረታታ አይመስላቸውም። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሞያዎች እጥረት ብቻ አይደለም ያለባት። መካከለኛ በሚባል ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግርም ሰንጎ ይዟታል። የነርሶች፣ የበሽተኛ ተንከባካቢዎች፣ የመዋዕለ ህጻናት ረዳቶች ከእጅ ሞያ ዘርፍ ደግሞ ፣የኤሌክትሪክ ባለሞያዎች እና የአናጢዎች አጥረት አለ ። በእነዚህና በመሳሰሉት ዘርፎች ሙያተኞችን ከሦስተኛው ዓለምም ጭምር ለማስገባት የሚደረገው ሙከራ የሁሉንም ፖለቲከኞች ይሁንታ አላገኘም። ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ  ረቂቁ  ለፍልሰት የተከፈተ የጓሮ በር ነው ሲል ይቃወማል። ከሁሉ በተለየ የግራዎቹ ፓርቲ ይህን መሰሉ አሠራር በሌሎች ሀገራት የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ይፈጥራል ሲል ስጋቱን ይገልጻል። አሠሪዎች ግን የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት እንዳይደናቀፍ ችግሩን መፍታት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ። 

Symbolbild Industriearbeiter
ምስል picture-alliance/PhotoAlto
Symbolbild Flüchtlinge als Fachkräfte
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe
Deutschland ausländische Experten
ምስል picture-alliance/dpa
Deutschland ausländische Experten
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ 

ነጋሽ መሐመድ