1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2011

ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አግኝታለች። ሲልቬስተር ኢሉንጋ ኢሉካምባ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ እና በአሁኑ ፕሬዝደንት ፌሊክ ሼኬሴዲ መካከል በተደረገ ፖለቲካዊ ስምምነት መሠረት መሆኑን የመንግሥት ቃል አቀባዩ ይፋ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3IxTw
Sylvestre Ilunga Ilunkamba des. Premierminister DR Kongo
ምስል Presidence RDC

ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቬስተር ኢሉንጋ ኢሉካምባ

አዲሱ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቬስተር ኢሉንጋ ኢሉካምባ ቀደም ሲል የሀገሪቱ የምድር ባቡር ኩባንያ ኃላፊ ነበሩ። ከዚያ በፊት በፕሬዝደንት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ዘመንም በገንዘብ ሚኒስትርነት ሠርተዋል። ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከአወዛጋቢ የምርጫ ሂደት በኋላ አዲስ ፕሬዝደንት ባገኘች በአምስት ወር ገደማ መሆኑ ነው። 
በዚያ ምርጫ የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ በአባልነት የሚገኙበት የተባበሩት የኮንጎ ግንባር የተሰኘው ፓርቲ የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 485 መቀመጫዎች 342ቱን ይዟል። የአዲሱ ፕሬዝደንት የፌሊክ ሼኬሴዲ "የለውጥ ሂደት" ፓርቲ ደግሞ 50 አባላቱ ብቻ ከምክር ቤት ገብተዋል። የኮንጎን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች ካቢላ ሥልጣናቸውን በብዙ ውዝግብ ቢለቁም ካቢኔውን በረጅም ገመድ እንደሚቆጣጠሩት ይገምታሉ። ምንም እንኳን ሼኬሴዲ በካቢላ የቀረቡላቸውን የተለያዩ እጩዎች ውድቅ ቢያደርጉም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኢሉንጋ አሰያየምም የዚህ ውጤት መሆኑን ዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚገኘው የኮንራድ አደናወር ተቋም ኃላፊ ቤኖ ሙሽለር ያመለክታሉ።


«ይህን ምርጫ የተመለከተ በስተመጨረሻ ማንም ያላሸነፈበት የጦርነት አውድ እንደነበር በግልፅ ይረዳዋል። እናም ውጤቱን ምናልባት በስተመጨረሻ ለተመለከተው ወደ ሁለቱም አቅጣጫ ያመለክታል። በዚህም ቢሆን ከሁለቱ ኃያላን በትክክል ልጓሙን በእጁ ያስገባው ማን እንደሆነ መጨረሻው ግልፅ አይደለም።»

DR Kongo scheidender Präsident Joseph Kabila neben Nachfolger Felix Tshisekedi während einer Einweihungsfeier in Kinshasa
ምስል Reuters/O. Acland


በኮንጎ የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የኃይል ሚዛኑን ለማመጣጠን ካቢላ እና ሼስኬዲ በጥምረት ሀገር ለመምራት ባለፈው መጋቢት ወር ተስማምተዋል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ አሁንም ካቢላ ከበስተጀርባ በረጅም እጃቸው ሥልጣኑን እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል የሚለውን ስጋት አስከትሏል። ቤኖ ሙሽለር ግን ምንም እንኳን ካቢላ በፓርላማ አብላጫ ድምፅ ቢኖራቸውም በመጨረሻ ውሳኔዎች በፕሬዝደንቱ የውሳኔ አፈጻጸም ስር ናቸው ነው የሚሉት። ያንን ለማረጋገጥ ግን በቀጣዩ ወራት የሚከናወኑትን ተግባራት መመልከት እንደሚያሻም ያሳስባሉ።


«በመጪዎቹን ጥቂት ወራት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳትፎ ታክሎበት አዲሱን መንግሥት በዚህ ሂደት ውስጥ ሼስኬዲ እንዴት መምራት እንደሚችሉ ገና ማሳየት ይኖርባቸዋል።»
በሌላ በኩል ግን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኢሉንጋ ኢሉካምፓ ሲሆን በካቢላ ፓርቲ የተባበሩት የኮንጎ ግንባር የተሰኘው እና በሼኬሴዲ የለውጥ ሂደት ፓርቲ መካከል ሚዛን መጠበቁ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ተገምቷል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተሾሙ ዕለት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር የተሰጣቸውን ስልጣን «በሀገሪቱ ታሪክ በወሳኝ ወቅት የተቀበሉት ኃላፊነት» መሆኑን ገልጸዋል።

Flagge der DR Kongo
ምስል Colourbox

ዕድሜያቸው በ70ዎቹ ውስጥ መሆኑ የተገለጸው ኢሉንጋ ከ40 ዓመታት በላይ በመንግሥት የተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የቆዩ በመሆናቸው የካቢላ ፓርቲ «የተፈተኑ ባለሙያ» እያለ ቢያሰማምራቸውም እርሳቸው በኃላፊነት የመሩት የኮንጎ ብሔራዊ የምድር ባቡር ኩባንያ የገንዘብ አያያዝ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ይነገራል። ኢሉንጋ አሁን አዲስ በተቀበሉት የመንግሥት ሥልጣን በሁለት ፓርቲዎች መካከል ከሚገጥማቸው ውጥረት በተጨማሪ የኮንጎ ሕዝብ ለ18 ዓመታት በሥልጣን የቆዩት ካቢላ የልቡን ላላደረሱለት መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ ማቅረብም ሌላው የሚጠብቃቸው ትልቅ ተግዳት ነው።  ከእርሳቸው አስቀድሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቡርኖ ሺባላ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝደንት ፌሊክ ሼስኬዲ ሰኞ ዕለት አቅርበዋል። 

ሸዋዬ ለገሠ/ ካላሪሳ ሄርማን  

ተስፋለም ወልደየስ