1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ሐምሌ 2 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የሁለት ቀናት የኤርትራ ጉብኝታቸዉን  አጠናቀው ዛሬ ወደ አገራቸዉ ተመልሰዋል። የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ዛሬ አስመራ ውስጥ የተለያዩ ስምምነቶችን ፈርመዋል።

https://p.dw.com/p/316G3
Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

አዲሱ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በኤርትራ ቆይታቸዉ ከኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ እሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለቱ አገራት ፖለትካዊ፤ እኮኖሚያዊና የሰለም ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኋላ ፤ ስምምነት ተፈራርመዋል። ለሁለት አስርተ-አመታት ቋርጦ የነበረ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዓለም አቀፍ የስልክ መስመር በትላንትናዉ ዕለት ስራ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸዉ ላይ አስፍረዉ ነበር። ለዓመታት ተቋርጦ የነበረዉ የአየር በረራ እንደሚጀምር ፤ ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደብ መጠቀም እንደምትጀምርና ሁለቱም ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደሚያድሱ አቶ ፍፁም ጠቅሰዋል። የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝና የፖለትካ ተንታኝ አቶ ገረሱ ቱፋ በቅርቡ ወደ ኤርትራ በመጓዝ የታዘቡትን እንዲህ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዛሬዉ እለት በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ለማስፈንና ግንኙነቶችን ለማደስ በአምስት ጉዳዮች ላይ ስምምነቶችን መፈራረማቸዉንም የሁለቱም አገራት ባለስልጣናት ያዋጡት መረጃ ያስረዳል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን የጦርነት ስጋት ለማቆም፤ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና የደህንነት ትብብር ለማጠናከር፤ ንግድ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል፤ የድንበር ጉዳይ ውሳኔን ለመትግበርና በአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸዉን አቶ ፊፁም አረጋ እንዲሁም የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገፃቸዉ ላይ ይፋ አድርገዋል።

Äthiopien Präsident  Isaias Afwerki und Premierminister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information

የድንበር ማካከል  ዉሳኔ መተግበር የሚለዉ በመሪዎቹና በሕዝቡ መካከል በሚካሄድ ዉይይት መፈታት እንዳለበት በመቀሌ ዩኒቬርስት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መምህር  አቶ መሃሪ ዮሐንስ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። መሪዎቹም ሆኑ ሕዝቡ ማድረግ አለበቸው ያሉትንም አቶ መሃሪ ተናግረዋል።

በቅርቡ ኤርትራ የነበሩት አቶ ገረሱ ፣የኤርትራ ባለሥልጣናትም ሆነ ህዝቡ የዶክተር ዐብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራም ተስፋ ሰጭ ነው የሚሉ  አስተያየቶችን ይሰሙ እንደነበር ገልጸዋል።

አቶ መሀሪ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት የአገር ወይም የሕዝብ ግጭት ሳይሆን ይልቁንም በህወሓትና በኤርትራ ህዝብ ነፃ አዉጭ ግንባር መካከል የተፈጠረ ግጭት መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ1990 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ባካሄዱት ጦርነት 100 ሺህ የሚገመት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ጦርነቱን ያበቃዉ የሰላም ስምምነት ለ18 ዓመት ሳይፈፀም ቆይተዋል።

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ