1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ ኦሚክሮን

ማክሰኞ፣ ኅዳር 21 2014

ኮሮና ተሐዋሲ በወረርሽኝነት ዓለምን ካዳረሰ ሁለት ዓመት ሊሞላ ጥቂት ወራት ቀርተዋል። ተሐዋሲው በየጊዜው ራሱን እየለወጠ የመሰራጨት አቅሙንም እያጠናከረ መምጣቱ እየታየ ነው። ካለፈው ሐሙስ አንስቶ ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው የኮሮና ተሐዋሲ አዲስ ስጋት ሆኗል።

https://p.dw.com/p/43fkm
Symbolbild Corona Covid Variante Omicron B.1.1.529
ምስል Pavlo Gonchar/Zumapress/picture alliance

ኦሚክሮን ልውጡ ኮሮና ተሐዋሲ

ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ የመዛመት ፍጥነቱ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው። ሆኖም ስለልውጡ ተሐዋሲ በአሁኑ ደረጃ ብዙም እንደማይታወቅ የዓለም የጤና ድርጅት ትናንት ይፋ አድርጓል። ኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ሆኖ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቢቀርም አሁንም አስፈሪነቱ፤ አሁንም የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መሆኑን አላቆመም። እንደውም ራሱን መለዋወጡን ቀጥሏል። ክትባቱስ ምን ለውጥ አስገኝቷል?

ኮሮና ተሐዋሲ ከቻይናዋ ውኃን ግዛት ተነስቶ መላውን ዓለም ካዳረሰበት ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 መጨረሻ ወራት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት መለዋወጡ ታይቷል። ተሐዋሲው በመጀመሪያ ተለውጦ በተገኘባቸው ሃገራት ስም ብሪታኒያ የተገኘው፤ የብራዚሉ፣ የደቡብ አፍሪቃው የሚል ቅጽል ሲሰጠው ቆይቶ ባለሙያዎቹ የግሪክ ፊደላትን በመጠቀም አልፋ እና ዴልታ እያሉ መጥራት ጀመሩ። ባለፈው ሳምንት  የተገኘው ደግሞ B1.1.529 የሚል ኮድ የተሰጠው ልውጥ ተሐዋሲ ኦሚክሮን ተብሏል። ተሐዋሲውን በመጀመሪያ የለዩት የደቡብ አፍሪቃ ተመራማሪዎች ናቸው። ይፋ መሆኑን ተከትሎም ደቡብ አፍሪቃ እና የአካባቢው ሃገራት ላይ የበረራ እገዳ እስከማስጣል ዓለምን አደናግጧል። የመዛመት ፍጥነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው የተባለው ኦሚክሮን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ እሁድ ዕለት ብቻ 2,800 ሰዎች ላይ መገኘቱ ስጋቱን አባብሶታል። በዩናይትድ ስቴትሷ ቨርጂኒያ ግዛት የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን ስለኦሚክሮን ብዙም ባይታወቅም መላውን ዓለም ማደናገጡን ይናገራሉ።  ስለተሐዋስያን ጸባይ እና ምንነት የሚመራመሩ ባለሙያዎች ማንኛውም ተሐዋሲ ወደሰዎች አካል ሲገባ በተለያዩ ምክንያቶች እራሱን እንደሚለውጥ ያመለክታሉ። ፕሮፌሰር ያሬድም የኮሮና ተሐዋሲ በየጊዜው የመለዋወጡ ነገር የብዙ ተሐዋስያን ጸባይ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ።   

Symbolbild I Großbritannien zeigt sich besorgt über die neue COVID-Variante
ምስል Jeff J Mitchell/AFP

የኮሮና ተሐዋሲን ስርጭት ለመግታት ከዚህ ቀደም ባልታየ ፍጥነት ክትባት ተዘጋጅቶ በርካታ ሃገራት ኗሪዎቻቸውን በብዛት መከተብ ችለዋል። በቀዳሚነት እስራኤል እና ብሪታንያን መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም ዛሬም በእነዚሁ ሃገራትም ሆነ አብዛኛው ነዋሪያቸው ክትባት እንዳገኘ በሚነገርላቸው ሃገራት  በተሐዋሲው የሚያዝ ሰው መበራከቱን በየዕለቱ ይፋ ይደረጋል። ይኽም በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ሆኗል። እንዲህ ያለው የተወሰደ ክትባት በጊዜ ሂደት የመከላከል አቅም መቀነስ በሌሎች ክትባቶች ላይም ያጋጥማል ባይ ናቸው ባለሙያው። 

ሰዎች በኮሮና ክትባት ላይ የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥርጣሬዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ፕሮፌሰር ያሬድ እንዲህ ያለው ክትባትን የመጠራጠር አካሄድ እንግዳ እንዳልሆነም ነው የገለጹት። ብዙ ጥናት ተደርጎበት የኮሮና ተሐዋሲ ክትባት መዘጋጀቱን ፣ እስካሁንም ብዙ ሚሊየን ሰዎች የወሰዱት መሆኑን በማመልከትም ከሌሎች ክትባቶች የተለየ ምንም የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለም አጽንኦት ሰጥተዋል። የኮሮና ክትባት ሌሎች ክትባቶች በሚዘጋጁበት በድሮው ስልት ሳይሆን ዘመናዊ ቴክኒዎሎጂን ተጠቅሞ የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።  ይኽ ክትባት የሚዘጋጅበት ቴክኒዎሎጂ አዲስ እና በተለይም የኢቦላ ተሀዋሲን ለመከላከል ከተደረጉ ጥናቶች ጋር የተደረሰበት ስልት መሆኑንም አመልክተዋል። 

አሁን በቅርቡ የተገኘው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ አፍሪቃ ላይ ምንነቱ ስለተደረሰበት ከአፍሪቃ የተገኘ ነው በሚል አፍሪቃ ሃገራት ላይ እየተደረገ ያለው የበረራ እገዳም ሆነ ከዚያ የሚመጡት ላይ የሚደረገው የተጠናከረ ምርመራ ተገቢ ነው ብለው እንደማይቀበሉትም ነው ፕሮፌሰር ያሬድ የገለጹልን። በትንሽ ቀናት ብዙዎች ላይ መገኘቱ ስጋቱ እውነት ነው ቢያሰኝም በጥናቶች በኩል ብዙ ይቀረዋልም ባይ ናቸው። ለሰጡን ማብራሪያ ፕሮፌሰር ያሬድን እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ