1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 26 2016

በመግባቢያ ሰነዱ መፈረም ላይ የሶማሊያና አሜሪካንን ጨምሮ የሌሎች አገራት መንግሥታት እንዲሁም የአካባቢውና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሰጡት አስተያየት ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ልዩ ልዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል። ዜጎች ፣ሶማሊያን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታት ፣አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶች ሰጥተዋል፤

https://p.dw.com/p/4as9X
የሶማሌላንዱ የበርበራ ወደብ
የሶማሌላንዱ የበርበራ ወደብ ምስል Jonas Gerding/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ታኅሳስ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

 

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የሚገኘውን የበርበራ ወደብ በሊዝ መጠቀም የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላገኘችው ከራስ ገዝዋ ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሙ በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች የተሰጡበት አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር።   ሁለቱ መንግሥታት በአዲስ አበባ  የተፈራረሙት የስምምነት ሰነድ “ለኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር ኃይል ጦር ሰፈርና የኮሜርሽያል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ » መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምኒኬሽን አገልግሎት የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመ በሦስተኛው ቀን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት እንደሚያስችልም መግለጫው ጠቁሟል። በሂደትም ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበት አግባብ እንደሚያካትትም » መግለጫው አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ ላይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ ላይ ምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

በሰነዱ መፈረም ላይ ዜጎች ፣ሶማሊያን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታት ፣አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶች ሰጥተዋል፤ እየሰጡም ነው። አስተያየቶቹ  ድጋፍ ተቃውሞ ጥርጣሬ  ቅሬታ ማሳሳቢያ ጥያቄዎች እና ሌሎች ሀሳቦችን ያካተቱ ናቸው። ከመካከላቸው አንዱ የንጉሴ መሸሻ አስተያየት ነው። እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ያስቀደሙት ንጉሴ ስምምነቱ የታላቅ ስልጣኔ ባለቤት ለሆነችውና ከ3 ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ላላት ሆኖም ተገዳ ለሦስት አሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ወደብ አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያ ላሳለፈችው መራር ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ታላቅ ታሪካዊ ክስተትም ነው ይላል።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት-የወደብ ጥያቄ፣ የአዉሮፕላን ግዢና ድርድር «ይመስገን ጌታ አምላክ ሲሉ» አስተያየታቸውን የጀመሩት ታደለ ባል ቻጉቶ «በእውነትም ዛሬ ለኢትዮጵያ የሁለት ታላላቅ ክስተት ቀን! አንዱ የባህር በር በሊዝ ለመጠቀም የመግባቢያ ስምምነትን ፊርማ ከሱማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ጋር የተፈፀመበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆናችን በይፋ የታወጀበት! ፈጣሪ ሆይ ሰላምና አንድነትን ጨምርልን! የሚሰሩ እጆችን ባረክ፣ የሚያሰላስል አእምሮ አብዛልን !» በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል።


ዮሴፍ ስዩም ሙሉጌታ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበው አስተያየት ደግሞ ጥያቄ ያስቀድማል «ኢትዮጵያ በግዢም ይሆን በኪራይ አስተማማኝ የባሀር በር ኢንዲኖራት የማይፈልግ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላምንም። ነገር ግን በመግባቢያ ሰነድ ላይ ብቻ ተመስርተን ገና አሳሪ ውል ሳንፈራረም ይሄን ያለቀለት ጉዳይ አድርጎ መቁጠር ተገቢ ነው? የቸኮልን አይመስልም? ሲል አበክሮም ይጠይቃል ። አቡ ፈውዛን ሂክ ደግሞ «ወደቡን በሚመለከት ከነ ችግሩም ቢሆን እንዲህ በፍጥነት ለመፈራረም የቻለው መንግስታችን የሀገሬቷን ሰላም ለማስተካከል ለምን ይሆን ግዜው የረዘመበት? የሚልጥያቄ አቅርበዋል። ሬቢ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየትም ከአቡ ፈውዛና ሃሳብ ጋር የሚቀራረብ ነው «የሚያስፈልገን የባህር በር ሳይሆን መጀመሪያ ሀገር ሰላም ይሁን» ሲል  ያሳስባል ። ኤርሚያስ ወልዴም በፌስቡክ ባሰፈሩት መልዕክት «ወደቡም እኮ የዜጎች ደህንነት ሲጠበቅ ነው ያለዚያ ፋይዳ የለውም ለዜጎች እንቁምላቸው ከሸኔ እናስጥላቸው ሸኔ ማነው እንወያይበት ተጨንቀናል ዜጎች ታግተው ከሚሊየን ብር በላይ እየተጠየቁ ነው ።» ሲሉ ተማጽነዋል።

የበርበራ ወደብ
የበርበራ ወደብ ምስል Jonas Gerding/DW


የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል አቋም በተንታኞች ዕይታኢትዮጵያና ሶማሌላንድ፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ በሊዝ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ሶማሌላንድ የግዛት አካሌ ናት የምትለው ሶማሊያ በጥብቅ ተቃውማለች ።የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱን ባዶ  ዋጋ ቢስና ሕጋዊ ኃይል የሌለው በማለት አጣጥሎ ለአካባቢው መረጋጋትም አስጊ ሲል ውድቅ አድርጎታል። የአውሮጳ ኅብረት ጉዳዩን አስመልክቶ  ባወጣው መግለጫ የሚደረጉ ስምምነቶች የሶማሊያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት፣የአፍሪቃ ኅብረትን መተዳደሪያ ደንብና የመንግስታቱ ድርጅት መርሆች ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን አለባቸው ሲል አሳስቧል። የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን ኢጋድ የሰነዱ መፈረም በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት ላይ ያጠላው ጥላ እንዳሳሰበው አስታውቋል። ሁለቱ እህትማማች ሃገራትም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድና  በመግባባት ለመፍታት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል። የአፍሪቃ ኅብረት ሁለቱ ሀገራት እንዲረጋጉና በመካከላቸው የሰፈነውን ውጥረትም በመከባበር እንዲያረግቡ ጠይቋል።ልዩነቶቻቸውንም በድርድር እንዲፈቱ መክሯል። ከፊርማው በኋላ በቀጣናው የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰባት የተናገረችው ዩናይትድ ስቴትስ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እውቅና እንድምትሰጥ አስታውቃለች። የእስላማዊ ትብብር ድርጅት  “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ማንኛውንም እርምጃ” እንደማይቀበል ገልጿል። 


በመግባቢያ ሰነዱ መፈረም ላይ የሶማሊያና አሜሪካንን ጨምሮ የሌሎች አገራት መንግሥታት እንዲሁም የአካባቢውና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሰጡት አስተያየት ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ልዩ ልዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል። «ምነዉ ተንገበገባችሁ» በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት ደረጀ ታምራት በፌስቡክ «አሜሪካ አዉሮጳ እስያ መካከለኛዉ ምስራቅ መተዉ የጦር ሰፈር መስርተዉ የለ፤ የኢትዮጵያ ሲሆን ደሃ ስለሆንን ያዙኝ ልቀቁኝ ይላሉ እኛኮ በሰቶ መቀበል በጋራ እንደግ ነዉ ያልነዉ ብለዋል። ስለ ስምምነቱ  የቀድሞው ዲፕሎማት አምባሳደር ዴቪድ ሺን ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት «በአእምሮዬ የሚመላለሰው ትልቁ ጥያቄ፣ኢትዮጵያ ለምን ይህን ለማድረግ ፈለገች የሚለው ነው።የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትና የወደብ ጥያቄ የመግባቢያ ስምምነቱ፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ በኩል ምርቶቿን ከማስገባት እና ከማስወጣት ይልቅ፣በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የኢትዮጵያን የጦር ሰፈር መመስረት ላይ ያተኮረ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው እንዲሁም በተለይ በኤርትራ ዘንድ  ፣ኢትዮጽያ በበርበራ በኩል የባህር ኀይል ጦር ሠፈር ለምን ለማቋቋም ፈለገች?  ዓላማውስ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል» ብለው ነበር።

ጭነቶች የሚራገፉበት የበበራ ወደብ
ጭነቶች የሚራገፉበት የበበራ ወደብ ምስል Brian Inganga/AP/picture alliance


አምባሳደር ሺን በሰጡት አስተያየት የተገረሙ የሚመስሉት ተፈራ አዲሱ ጥያቄ አቅርበዋል።«ኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እኮ ነበራት። ለምን ባሕር ኃይል መገንባት ፈለገች ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ቤዝ እና የማሪታይም ንግዷን ለማሳለጥ ተቋሟዊ እና አስተዳደሪያዊ አቅም የሚሰጣትን ወደብ ለመገንባት ስምምነት ማድረጓን ገልፃለች ። የሶማሌ ፌዴራል መንግሥትም ሆነ ምዕራባውያን ሃገራት እየወሰዱት ያለው አቋም ተጠባቂ ነው።  ለምን ባሕር ኃይል መገንባት ፈለገች የሚለው ግን አስቂኝ ጥያቄ ነው። በአሰብ በኩል ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የምትርቀው 57 ኪሎሜትር ብቻ ነው። የኤርትራ መንግሥትስ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለመገንባት የምታደርገው ጥረትስ ለምን ያሰጋዋል በማለት በጥያቄ የጀመሩትን አስተያየት በጥያቄ ጨርሰዋል።  አብራር ነስረዲን ኤ ኤን ደግሞ «ሐገሪቱ የባሕር በር ቢኖራት የሚጠላ ዜጋ አይኖርም። የሚገኘበት መንገድ እንጂ ሲሉ ኽሳድ ግመል ደግሞ «የወደብ ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም አካሄዱ ችግር ያለበት መስሎ ይታየኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱማሊያ ወደቦች ይልቅ የኤርትራ ወደቦች ላይ ትኩረት ቢያደርጉ የተሻለ አለምአቀፋዊ ድጋፍ ያገኙ ነበር።ምክንያቱም የኤርትራ ወደብ በአንድም በሌላ የኢትዮጵያ ወደቦች ነበሩና ብለዋል።

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር