1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢ ሕጎችን የማሻሻል ሂደት በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 24 2010

የኢትዮጵያ  ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር፤ የበጎ አድራጎት እና የማህበራት አዋጆችን ለማሻሻል ውይይት እንደሚያካሂድ አስታወቀ :: የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ ውይይቱ  የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በተባለው ተቋም በተዘጋጁ የማሻሻያ ጥናቶችን ላይ ይደረጋል።

https://p.dw.com/p/3441n
Justitia mit  Waage und Schwert in Görlitz
ምስል picture alliance/dpa/W. Rothermel

አወዛጋቢ ሕጎችን የማሻሻል ሂደት በኢትዮጵያ 

አሸባሪ እና ሽብርተኝነትን በተመለከተ ሃገራት ብቻ ሳይሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገራት ጭምር እስከዛሬ አንድ ወጥ የሆነ ትርጓሜ እና መግባባት ላይ አለመድረሳቸውን በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመደራጀት መብቶችን በሕገ መንግሥቶቻቸው በግልጽ ያሰፈሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራትም ጨቋኝ መንግሥታትን የሚታገሉ የተለየ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና አስተሳሰብ የሚያራምዱ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን በአሸባሪነት ፈርጀው ለእስር  እና ሰቆቃ አጋልጠዋል የሚለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት ክስ እና ወቀሳም ለዚህ ምስክር ነው :: የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ዓመታት አወዛጋቢ ሆነው የቆዩትን እና በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ክስ ዋና ምክንያት የነበሩትን እነዚህን አወዛጋቢ የፀረ ሽብር የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጆችን ለማሻሻል ከውሳኔ ላይ መድረሱን በቅርቡ አስታውቋል:: በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ እንደሚሉት በህጎቹ አተገባበር እና አፈጻጸም ዙሪያ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት ሰፊ ጥናት እና ውይይት በባለሙያዎች ሲካሄድ ቆይቷል ::በተቃውሞ ጎራ የተለየ አመለካከት የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከህጎቹ በተለይ መንግሥት ተቃዋሚውን ኃይል ለማዳከም ሲከተለው የቆየው የህጎቹ ስልታዊ አተገባበር ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል :: ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራትም ለነጻነት እና ለሕዝቦች መብት መከበር በሚታገሉ ተቃዋሚዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ እየመሰረቱ ሰላማዊ የነጻነት ትግሎችን በሕግ ሽፋን ሊያዳፍኑ ሞክረዋል እየተባሉ ሲወቀሱ ቆይተዋል :: በተለይም የጸረ ሽብር ሕጉን አስመልክቶ  በራሱ በመንግሥት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ጀምሮ እስከ ቅርብ ወራት በኃላፊነት ሲያገለግሉ በሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ምክንያት ከ 12 ጊዜያት በላይ በሽብር ወንጀል እየተከሰሱ ለእንግልት መዳረጋቸውን እና በሕጉ እና በአፈጻጸሙ መካከል ያለውን ተቃርኖ  የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በመንግሥት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀው ተግባራዊ በሆኑት የፀረ ሽብር የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ህጎችን እና በአተገባበራቸው ላይ የፌደራል አቃቤ ሕግ የሕግ እና የፍትህ አስተዳደር ጉባኤ የስራ ቡድን በሟቋቋም ላለፉት ወራት  ሰፊ ጥናት አካሂዷል። አቶ ታዬ ጥናቱ የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን እና ድንጋጌዎችን እንዲሁም የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ጭምር ያካተተ ነበር ይላሉ:: በኢትዮጵያ የፀረ ሽብር የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ህጎችን እና አተገባበራቸውን ለማሻሻል እንቅስቃሴ የተጀመረው አገሪቱ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 በተደነገገው መሰረት የዜጎችን በነጻነት የመደራጀት መብት በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ ነው። ህጎቹን ለማሻሻል የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በበጎ አድራጎት እና ማህበራት ህግ ላይ ከነሃሴ 25 እስከ መስከረም 10, 2011 ዓ.ም በፀረ ሽብር ህጉ ዙሪያ ደግሞ ከመስከረም 7-14, 2011 ዓ.ም በመላው አገሪቱ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱንም የፌደራል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ ገልጸዋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ 

አርያም ተክሌ