1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጤና አጠባበቅ በዘመነ ኮሮና 

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2012

በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀ ያለዉን የኮሮና ተዋህሲ ስርጭትን ለመግታት ሀገሮች የተለያዩ ገደቦችን ጥለዋል።ከነዚህም መካከል አካላዊና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ይገኙበታል።እነዚህ ገደቦች አብሮነትን የሚያሳጡ በመሆናቸው፤ የማህበራዊ ኑሮ ትስስር ከፍተኛ ለሆነባት እንደ ኢትዮጵያ ሁኔታዉ ከባድ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3bCoh
Deutschland Dortmung | Coronakrise [ Symbolbild Breitensport & Fitness
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ጤና እና አካባቢ፦ አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጤና አጠባበቅ በዘመነ ኮሮና 

የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭትን ለመግታት ሀገሮች ከጣሏቸው ገደቦች መካከል አካላዊና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ዋነኞቹ ናቸው። በዚህ የተነሳ ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶች ፣የአምልኮ ቦታዎችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘግተዋል። ማህበራዊ ግንኑነቶችም ተቋርጠዋል።እነዚህ ገደቦች የጓደንነት፣ የጉርብትናና የቤተሰባዊ ትስስሮችን የሚያሳጡ በመሆናቸው፤ የማህበራዊ ኑሮ ትስስራቸው ጥብቅ ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ቀርቶ ግላዊነትን ልማድ ላደረጉ ሀገሮችም ሁኔታዉ ከባድ መሆኑ እየታየ ነዉ።ቢሆንም ግን በሽታውን ለመከላከል ብቸኛው መፍትሄ በመሆኑ ሳያቅማሙ ይተገብሩታል። 
 ኢትዮያም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር አካላዊና ማህበራዊ ርቀትን ከመጠበቅ በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ደርሳለች።ያም ሆኖ ክልከላው ህብረተሰቡ የቆየንበትን አብሮነትን የሚጠይቁና ከዕለት ተዕለት ህይወቱ ጋር የተጋመዱ እንደ እድር፣ማህበር፣ሰርግ፣ጉርብትና፣አብሮ መብላትና መጠጣት፣መጠያየቅ እንዲሁም የበዓላት አከባበርን የመሳሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚያሳጣ በመሆኑ ለመተግበር ሲቸገር ይታያል።ነገር ግን በሽታው ህይወትን እስከማጣት የሚያደርስ በመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን ከማህበራዊ ህይወት መቆጠብ የግድ መሆኑን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ፣ የሳንባና የፅኑ ህሙማን ባለሙያ ዶክተር አስቻለው ወርቁ ገልጸዋል። 
 ምንም እንኳ ባህልንና የቆዩ ልማዶችን ቶሎ መተው ቢያስቸግርም ፤በመንግስት በኩልም በሽታውን ለመከላከል የወጡ ህጎችን ማስተግበር፣ አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ፣አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የምርመራ ስራን ማጠናከርና በተዋሲው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች መከታተል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ያካልሆነ ግን ወረርሽኙ ጠንካራ የጤና ስርዓት ያላቸዉን ሀገራት ሳይቀር የተገዳደረ በመሆኑ በኢትዮጵያም የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ። 
«ቫይረሱ በአንድ ሀገር ውስጥ 40 እስከ 60 በመቶ ያለውን ህዝብ ያጠቃል።ትልቁ ማለት ነው።ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በጣም የሚታመሙ ናቸው። አምስት በመቶ ደግሞ ፅኑ ህክምና የመተንፈሻ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።በኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ይህን ችግር ካየነውና በና የጤና ተቋማት የብቃት ደረጃ ካየነው በዚህ ደረጃ ከመጣ ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነውየሚሆነው።» ካሉ በኋላ የጥንቃቄ መንገዶችን መተግበር በሽታውን ለመከላከል ቀላሉ መንገድ መሆኑን አመልክተዋል። 
 የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የበሽታውን የመከላከያ ክትባት እስካልተገኘና ጥቅም ላይ እስካልዋለ ድረስ ማናችንም ቢሆን በወረርሽኙ የመያዝ አደጋን መቀነስ የምንችለው በባለሙያ የሚሰጡ የጥንቃቄ መንገዶችን በመከተል ነው። በሌላ በኩል እነዚህን ጥንቃቄዎች ለመተግበር ከዕጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮም ሌላው ፈተና ነዉ።ስራና ደሞዝ የተቋረጠበት ፣ገበያ የተቀዛቀዘበት፣በኢኮኖሚ ችግር ሊጨነቅ ይችላል።ሞትን መፍራትና ስለ በሽታው የሚሰጡ መረጃዎችም የራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው። ከዚህ ባሻገር ከቤት ሆኖ መሥራት፣ ለጊዜው ሥራ አጥ መሆን፣ የልጆችና የወላጆች ሙሉ ቀን ቤት መዋል፣ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር አለመዝናናትም ሆነ ዘመድን አለመጠየቅ ከዚህ በፊት ከነበረው የአኗኗር ዘይቤ የተለየ በመሆኑ ለሥነ-ልቡና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። በመሆኑም የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል ከሚደረጉ ተግባራት ባሻገር አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራትን ማከናወንም እንደ ባለሙያው ጠቃሚ ነው።  ከነዚህም መካከል በተቻለ መጠን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በርቀት በስልክና በሌሎች ዘዴዎች ማህበራዊ ትስስሮች መቀጠል ለአካላዊ ጤንነታችን ብቻ ሳይሆን ለሥነ-ልቦናዊ ደህንነታችንም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ 
 ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚደረገው ጥንቃቄ ጎን ለጎን በቂ እንቅልፍ ማግኘት ፣ ጤናማ አመጋገብና ከሱስ አምጪ ነገሮች መቆጠብ የልብ፣ የደም ቧንቧና የስኳር በሽታዎችን፣ ከመጠን በላይ ዉፍረትን እንዲሁም እንደ ድብርት እና ጭንቀት ያሉ የሥነ-ልቡና ችግሮችን ለመቀነስ ወሳንኝ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።ለዚህም ከዚህ ቀደም በምዕራብ አፍሪቃ የኢቮላ በሽታ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ሁሉም ነገር ትኩረቱ ኢቮላ በሽታ ላይ ስለነበር ከወረርሽኙ ይልቅ በተዘነጉ ሌሎች በሽታዎች ሰዎች የበለጠ መጎዳታቸውን አስታውሰዋል። 
 በሌላ በኩልም ወረርሽኙን ለመግታት ከተጣሉ ገደቦች ጋር ተያይዞ በቤት ዉስጥ የሚደርስ ጥቃት መጨመር አንዱ ችግር መሆኑንም የዓለም የጤና ድርጅት ዘገባ ያሳያል።በኢትዮጵያም ይህንን ታሳቢ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤቶች ስራ ቢያቆሙም በአስቸኳይ ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኗል።በአጠቃላይ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችንና የሥነ-ልቡና ጫናዎችን ለመቀነስ ከባለሙያ ምክር በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች መምከርና ማስተማር እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል።የኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስም ግለሰቦችና ባለሀብቶች የተቸገሩትን መረዳትና መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።በመንግስት በኩል የተጀመሩ የእርዳታ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠልም ተገቢ ነው። 
 ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኑን ለመከላለል በባለሙያ የሚመከሩ ቅድመ ጥንቃቄዎችን መተግበር ሥነ-ልቡናዊ ጫናን ለማስወገድና በሽታውን ለመከላከል ዋናው መፍትሄ መሆኑን ዶክተር አስቻለው አስምረውበታል።  ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። 

Nicaragua Bufalo Boxen
ምስል Reuters/O. Rivas
Gaza Palästina Karate Lehrer Khaled Sheikh al-Eid  Corona-Krise
ምስል picture-alliance/dpa/A.R. Khatib


 ፀሐይ ጫኔ