1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

"አከተመ በቃ" የኤልያስ መልካ የቀድሞ መምህር

እሑድ፣ መስከረም 25 2012

መምህራኑ ጭምር «በልጅነቱ የነበረው ችሎታ የሚገርም ነበር» ሲሉ የሚመሰክሩለት ኤልያስ መልካ በ42 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከ40 በላይ አልበሞች ከ400 በላይ ሙዚቃዎች እንደሰራ የሚነገርለት ኤልያስ ባለሙያዎች ፍትኃዊ ክፍያ ያገኙ ዘንድ እስከ ዕለተ ሞቱ ሲታገል ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/3QmUL
Äthiopien Musiker Elias Melka
ምስል Privat

ኤልያስ መልካ ከአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትን ሲቀላቀል ቼሎ ያስተማሩት አቶ ገዛኸኝ ኃይሌ የሰሙትን ማመን አቅቷቸዋል። «ኤልያስ መልካ ከተማሪዎቼ አንዱ ነበረ። በጣም የምኮራበት እና የምመካበት ልጅ ነበረ። ምክሬን የሚቀበል፤ የምመክረውን የሚሰማ፣ ትምህርቱን የሚያከብር ጎበዝ እና ታታሪ ተማሪ እንደነበር አውቃለሁ» ሲሉ ይገልጹታል።

«ኤልያስ በቼሎ ብቻ ሳይሆን በፒያኖም ጎበዝ ነው። በጊታርም ጎበዝ ነው፤ ሜጀሩ ቼሎ ነው፤ ነገር ግን በአገር ባሕል የሙዚቃ መሳሪያ፣ በፒያኖ እና በጊታር ተከታታይ ትምህርቶች ነበሩት። በዚህ ሁሉ ኤልያስ ጉብዝና ነበረው፣ ስሜትም ነበረው። ለሙዚቃ ዋናው ስሜት ነው» የሚሉት መምህር የሞቱ ዜና ግን አልተዋጠላቸውም። የኤልያስ መልካ ሞት ከቀድሞ መምህሩ ባሻገር ለሥራ ባልደረቦቹ፣ ለሙዚቃ ባለሙያዎች እና የሙዚቃ ወዳጆች አስደንጋጭ ሆኗል።

የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ጊታሪስት የዜማ እና ግጥም ደራሲ የነበረው ኤልያስ ትናንት መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የኩላሊት እና የስኳር ሕመም የነበረበት ኤልያስ ትናንት ምሽት ሕመሙ ጠንቶበት በአዲስ አበባ ወደሚገኘው ኢትዮ-ጠቢብ ጠቅላላ ሆስፒታል ተወስዶ በዚያው ሕይወቱ ማለፉን የቅርብ የሥራ ባልደረቦቹ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ላለፈው አንድ አመት ገደማ በሳምንት ሶስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት ሕክምናውን እየተከታተለ የነበረ ቢሆንም አዳዲስ የሙዚቃ አልበሞች ዝግጅትን ጨምሮ በበርካታ ሥራዎች ጫና ውስጥ መቆየቱ በጤናው ላይ ጫና እንዳሳደረበት በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።

ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ለሶስት አመታት የለፋበት እና በቅርቡ ሥራ ላይ በዋለው አውታር የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በገበያው እምብዛም ቦታ ያላገኙ ማኅበረሰቦችን ሙዚቃዎች ለሽያጭ ለማብቃት ግፊት በማድረግ ላይ ነበር።

ድምፃውያንን ጨምሮ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከሥራዎቻቸው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም የነበረው ኤልያስ፤ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) እና ዳዊት ንጉሴ ከተባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ባቋቋመው አውታር መልቲሚዲያ በኩል አውታር የተባለውን መገበያያ ሥራ ላይ አውሏል።

የሙዚቃ ሥራዎች ለሽያጭ ሲቀርቡ ድምፃዊ፣ የግጥም ጸሐፊ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማ ደራሲ ጨምሮ ሁሉንም ባለሙያዎች እኩል ተጠቃሚ ያደርጋል ብሎ ያመነበትን የአውታር መገበያያ ሥርዓት ለማጠናከር ከባልደረቦቹ ጋር ጥረት ላይ ነበር።

በአዲስ አበባ በተለምዶ አብነት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ታኅሳስ 1 ቀን 1970 ዓ.ም. የተወለደው ኤልያስ በልጅነቱ እግር ኳስ መጫወት ይወድ የነበረ ቢሆንም ወደ ሙዚቃ የማዘንበል ፍላጎት ያሳይ ነበር። ይሁነኝ ብሎ ከአስራ አንደኛ ክፍል ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከማምራቱ በፊት በቤተ ክርስቲያን ሙዚቃ ተጫውቷል።

በ1987 ዓ.ም. ሙዚቃን ለመማር ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲያመራ «በፍላጎት፣ በፍቅር እና በተሰጥዖ» እንደነበር በመዲና ባንድ አብረውት ሙዚቃ የተጫወቱት ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ ያስታውሳሉ። በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በዋናነት ያጠናው ቼሎ ተብሎ የሚጠራውን የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ከዚያ ባሻገር ክራር እና ፒያኖ ተምሯል። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ በያኔው መዲና ባንድ ለሶስት አመታት ጊታር ተጫውቷል።

 «እኔ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እያስተማርኩ ከጓደኞቼ ጋር መዲና ባንድ የሚባል ነበረን። እዚያ ጊታር እንዲጫወት ወስደንው ነበር። በልጅነቱ የነበረው ችሎታ የሚገርም ነበር። በሚሰራቸው ሥራዎች ጓደኞቼም እኔም በጣም ነበር የምናደንቀው። ጎበዝ ልጅ ነበር» ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ ስለ ኤልያስ ይመሰክራሉ።

ኤልያስ ቦሌ አካባቢ ያቋቋመው በገና ስቱዲዮ ላለፉት አመታት የበርካታ ሙዚቀኞች ቀልብ ማረፊያ ሆኖ ቆይቷል። ባለሙያዎች እንደሚሉት ኤልያስ ባለፉት 18 ገደማ አመታት ከ40 በላይ አልበሞች እና ከ400 በላይ ሙዚቃዎች ሰርቷል። ሙዚቃ ካዘጋጀላቸው መካከል ቴዎድሮስ ካሳሁን፤ሚካያ በኃይሉ፣እዮብ መኮንን፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ኤደን ገብረ ስላሴ፣ ትዕግስት በቀለ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ዘሪቱ ከበደ ይጠቀሳሉ።

«ኤልያስ ባጨዋወቱ የራሱ የሆኑ ነገሮችን ማሳረፍ ችሏል። ቅንብሮቹን ትለያቸዋለህ» የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ ሥራዎቹም ቢሆኑ ስኬታማ ሆነዋል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

«ጊታር፣ ኤሌክትሪክ ቤዝ፣ ክራር እና ፒያኖ ኪቦርድ ላይ ያለውን ጥንካሬ ስታይ ፖፕ አርት ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባል ሙዚቀኛ ነበር ማለት እችላለሁ። በሰራቸው ሥራዎች ትልልቅ አሻራ ማሳረፍ የቻለ ወጣት ሙዚቀኛ ነበረ፤ ባለ ተሰጥዖ ሙዚቀኛ ነበረ» የሚሉት አክሊሉ ኤልያስ እና መሰል ባለሙያዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ ጫና የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

«ባለፈው የፋና ቴሌቭዥን የባለ ተሰጥዖዎች ውድድር ተብሎ ተጋብዤ እዛ ሳገኘው በጣም ነው ያዘንኩት» ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ «የለሊት ሥራ በጣም ከባድ ነው፤ ያላቸውን ኃይል ሁሉ የሚጨርሱበት አይነት ነው« ብለዋል።  

የኤልያስ መልካ ሞት የቀድሞ መምህራኑን፣ የሥራ ባልደረቦቹን እና የሙዚቃ ወዳጆችን አስደንግጧል። ባለፉት ሳምንታት አብረውት በስራ ላይ የነበሩ የሕመሙን መባባስ በቅርብ ቢያውቁም በሞቱ ደንግጠው በቅጡ መናገር ተስኗቸዋል።  «እኔ እኮራበታለሁ» የሚሉት የቀድሞ መምህሩ አቶ ገዛኸኝ ኃይሌ ከእንባቸው እየተናነቁ «አከተመ በቃ የምለው የለኝም» ብለዋል። በመዲና ባንድ አብረውት ሙዚቃ የተጫወቱት አክሊሉ ዘውዴ በበኩላቸው «በልጅነቱ ነው የሔደው፣ ትንሽ ልጅ ነበር። ገና ብዙ በሚሰራበት ዕድሜ ነው። ተቀጨ» ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።  በመጪው ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ኤልያስ መልካ በተማረበት ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሽኝት ሊደረግለት መታቀዱ ተሰምቷል።

 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ