1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪው መረጃ መንታፊ ሶፍት ዌር «ፔጋሰስ» እና ርዋንዳ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 17 2013

አፍሪካዊቷ ሀገር ርዋንዳ ሰሞኑን ፔጋሰስ ሶፍት ዌር በመጠቀም የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ስትሰልል ነበር መባሉ በደቡብ አፍሪካ መንግስት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። በሌላ በኩል በአንድ ሳምንት ውስጥ ታዋቂ ጋዜጠኛ አስራ ሌላ በእስር ላይ የነበሩትን የለቀቀችው ግብጽ ድርጊት አነጋጋግሯል።

https://p.dw.com/p/3xyd4
Symbolfoto Pegasus Projekt
ምስል Jean-François Frey//L'ALSACE/PHOTOPQR/MAXPPP7/picture alliance

የሐምሌ 17/2013 ዓ/ም የትኩረት በአፍሪካ ዝግጅት

ከሰሞኑ ዓለማቀፍ ትኩረት ያገኘው እስራኤል ሰራሹ የመረጃ መንታፊ «ፔጋሰስ» ሶፍት ዌር የአፍሪካውያን መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ስለማግኘቱ ተሰምቷል ። አፍሪካዊቷ ሀገር ርዋንዳም ከዚህ ከዚህ የመረጃ መንታፊ ሶፍት ዌር ጋር ስሟ ተነስቷል ። የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ታምራት ዲንሳ ነኝ አብራችሁን ቆዩ።
«ፔጋሰስ» የተሰኘ ሶፍት ዌር እስራኤል ሀገር በሚገኝ እና በእንግሊዝኛ ምጽሃሩ NSO ተብሎ የሚታወቅ አንድ ኩባንያ ምርት ነው።በዚህ ሶፍት ዌር አማካኝነት የዓለማችን ታዋቂ መሪዎች፣ የዝነኞችን እንዲሁም የቀድሞ የሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸውን  ጨምሮ ቁጥራቸው ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች ስልካቸው ሳይጠለፍ እንዳልቀረ ከሰሞኑ ዓለም አቀፍ  የመገናኛ ብዙኃን ተቀባብለውታል። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የስልክ ቁጥሮች በሶፍት ዌሩ ከተጠለፉት ዝርዝር ውስጥ መገኘቱ ደግሞ እነዚሁ የመገናኛ ብዙኃን ርዕሰ ጉዳያቸውም አድርገውት ነበር። 
ርዕሰ ጉዳዩን ከመነጋገሪያነት ባሻገር አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ ያሉ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሰላዩ ሶፍት ዌር ኢላማ መሆናቸው ነው። 
ስልካቸው ለስለላ ተጋልጧል የተባሉት እነዚሁ 50,000 ሰዎች የፔጋሰስ አምራች ኩባንያ NSO ምርት ደንበኞች ናቸው። ለስለላው የተጋለጡ ሰዎችን የስም ዝርዝር ይዞ ሾልኮ እንደወጣ የተነገረለት መረጃው እንደሚያመለክተው ቶጎ ፣ሞሮኮ እና ርዋንዳን ጨምሮ በጥቂቱ 7 የአፍሪካ ሀገራት ሰለባ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ነው።  
ከእነዚህ ሃገራት በተለይ በርዋንዳ ፔጋሰስ ሶፍት ዌርን በመጠቀም ተፈጽሟል የተባለው  የስለላ ተግባር ደግሞ ለየት ባለ መልኩ አነጋጋሪ ሆኗል። የፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ መንግስት ከጎርጎርሳውያኑ 2016 ጀምሮ 3,500 በሚሆኑ የስልክ ቁጥሮች ላይ ስለላ ሲያካሂድ እንደነበር ሾልኮ የወጣው መረጃ አመልክቷል። በስለላው የስልክ ጥሪዎችን መቅዳትን ጨምሮ የአጭር መልዕክቶችን እና ኢሜይሎችን ማንበብ፤ ፎቶ ግራፎችን መፈተሽ ፤ የይለፍ ቃሎችን መበርበር እንዲሁም አለፍ ብለው መቅረጸ ድምጾች እና የቪዲዮ ካሜራዎችን በድብቅ እንዲሰሩ ድምጽ እና ምስል ይቀዱ እንደነበር ተገልጿል። 
ነገር ግን የርዋንዳ መንግስት የፔጋሰስ ሶፍት ዌርን አልተጠቀምኩም ሲል አስተባብሏል። 
ይህንን በተመለከተ የርዋንዳ መንግስት በሰጠው ምላሽ ፤  «የሐሰት ውንጀላዎቹ በሩዋንዳ እና በሌሎች ሀገሮች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር እና የርዋንዳን ስም በሀገር ውስጥ እና በተቀረው ዓለም የማጠልሸት ዘመቻ አካል ናቸው » ብሏል።
ርዋንዳ ሰላዩን ሶፍት ዌር በመጠቀም ስትሰልላቸው ነበር ተብለው የስም ዝርዝራቸው ከወጣው መካከል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከፊት ተጠቃሽ ሆነዋል። 
መረጃው ከወጣ በኋላ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለፈው ረቡዕ በፍጥነት መልስ በመስጠት የፕሬዚዳንቱ የእጅ ስልካቸው ተጠልፎ ከነበረ በሚል  አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉ ለስለላ ተቋሞቻቸው ትዕዛዝ መሰጠቱ ተነግሯል። 
በፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት ተጠባባቂ ሚንስትር ኩምብዱዞ ሻቬኒ የመንግስትን አቋም እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል። 
«በዚህ ጉዳይ ዒላማ መደረጋችን በእርግጥ አያስደስተንም ምክንያቱም ጉዳዩ ከፕሬዚዳንቱ የግል ጉዳይ መጣስ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቷ የሌሎች ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋት የራሷን ጉዳይ በራሷ እንዳትወጣ ብሎም ውሳኔዎቿን ላለማክበር እና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈ,ር የተደረገ ነው ብለን እናምናለን ።» 
የደቡብ አፍሪካ መንግስት መረጃ ለማግኘት ከዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ይልቅ «ተቀባይነት የሌላቸውን መንገዶች » እንደማይቀበል ሻቬኒ ተናግረዋል። 
ነገር ግን የሳይበር ደህንነት ባለሞያው አንዲ ማሻሌይ የደቡብ አፍሪካን የደህንነት ጥንቃቄዎች ተችተዋል። ባለሞያው ለደቡብ አፍሪካው SABC ቴሌቪዥን ባለፈው ሐሙስ በሰጡት ቃለምልልስ እንዳሉት «የፕሬዚዳንቱ የቅርብ ረዳቶች ማንነት በደንብ መታወቅ ነበረበት» ።
ለመሆኑ የፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ የእጅ ስልክ ቁጥር እንዴት ወጣ ? ለጥያቄው መልስ ለመሻት በፔጋሰስ የስለላ ፕሮጀክት ላይ በሚደረገው ምርመራ  አጋር የሆነው የጋርዲያን ጋዜጣ ዘገባን መመልከት ይገባል። ጋዜጣው በምርመራ ዘገባው እንዳለው የፕሬዚዳንት ስሪልራማፎዛ የእጅ ስልክ በሩዋንዳ ለስለላ የተመረጠው በጎርጎርሳውያኑ 2019 ነው። 
ከ2019 በፊት የሩዋንዳ እና የደቡብ አፍሪካ ግንኙነት ለዓመታት የሻከረ ነበር። ለዚህ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር በዋነኛነት እንደምንያት የሚጠቀሰው ደግሞ በጎርጎርሳውያኑ 2014 የቀድሞው የርዋንዳ የስለላ ኃላፊ የነበሩት ፓትሪክ ካሬጌያ በጆሃንስበርግ በሚገኝ በአንድ የሆቴል ክፍል ውስጥ ታንቀው ተገድለው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።  
ከዚያ በኋላ ባሉ ግዜያት ርዋንዳ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረው የዲፕሎማሲ መሻከር  ወደ ውጥረት ተሸጋግሮ ቆይቷል። 
ነገር ግን በዚህ ዓመት ባለፈው የሰኔ ወር የሁለቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ፕሪቶርያ ውስጥ ተገናንተው ግንኙነታቸውን ማደስ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።
እንደዚያም ሆኖ አሁንም ድረስ ግልጽ ያልሆነው ርዋንዳ የፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳን የእጅ ስልክ በመሰለል ልታገኘው የፈለገችው መረጃ ምንነት ነው። 
በጉዳዩ ላይ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የደቡብ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሼኒላ መሐመድ SABC ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ  
«ሩዋንዳ በስለላው ምን እንደፈለገች ወይም ለምን ለምን ይህን ተግባር እንደፈጸሙ ለመናገር በእውነት ለእኛ ከባድ ነው ነገር ግን ዋናው ጉዳይ ሩዋንዳ ከNSO ግሩፕ ደንበኞች መካከል አንዷ መሆኗን ማወቃችን ነው ፡፡» ብለዋል።
«የሀገር መሪዎች እና መንግስታት ለህዝብ ይፋ የማይደረጉ ጉዳዮች እንዳሏቸው መዘንጋት የለበትም» ሲሉ ሼኒላ ስለላውን ተችተዋል።
ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ብርቱ ውጥረት ውስጥ ሳሉ ስለላ ሲደረግባቸው እንደነበር መረጃ መውጣቱ ሌላ ራስ ምታት እንደሆነባቸው ነው የተነገረው። ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞውን ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማን መታሰር ተከትሎ በሀገሪቱ ለበርካቶች ሞት እና የንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው ነውጥ ቀድሞ የታቀደበት ነበር መባሉ ነውጡን አስቀድሞ  ባለማወቁ የሀገሪቱን የስለላ ተቋማት ውድቀት ያሳየ ነበር መባሉ ነው። 
የሀገሪቱ የደህንነት ሚንስትሩ አይንዳ ድሎድሎ ግን የሚቀርበውን ብርቱ ትችት ለማለሳለስ በሞከሩበት ንግግራቸው እንዳሉት « ደቡብ አፍሪካውያን እንዲረዱ እና ልባቸውን እንዲያሳርፉ የምፈልገው ሊደርስ ከነበረው የደረሰው ጥቂት መሆኑን ነው። ችግሩን ለመግታት ብዙ ጥረናል ፤ የተመለከትነው ሊደርስብን ይችል ከነበረው ከፊሉ ነው የሆነው።  የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያቤት ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል፤ ፖሊስም ቢሆን በተመሳሳይ እያደረገ ነው ፤ እነዚህን ነገሮች እየተወጣን ያለነው ሀገሪቱ በእጅጉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።» ብለዋል። 
በተያያዘ የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ከቀድሞው ፕሬዚደንት ዙማ ጋር ግንኙነት የነበራቸው የቀድሞ የስለላ ሰራተኞች በሀገሪቱ በተነሳው ነውጥ ውስጥ እጃቸው ይኑር አርኑር እየተመረመረ መሆኑ ነው የተነገረው። 
የደቡብ አፍሪካ  የስለላ ባለሞያዎች እና ተንታኞች በቅርቡ የተከሰተው ነውጥ ሆን ተብሎ ራማፎሳን «ለማዳከም» ሳይሆን እንዳልቀረ ይገላጻሉ።
ርዋንዳ የፔጋሰስ ሶፍትዌርን በመጠቀም ስትሰልላቸው ነበር ከተባሉ ሰዎች ውስጥ ተጠቃሽ የሆነችው የዝነኛው ሆቴል ርዋንዳ ባለቤት ፓዉል ሩሴሳባጊና ሴት ልጅ የሆነችው ካሪኔ ማኒምባ መሆኗን በሶፍት ዌሩ ላይ የተደረገው ምርመራ ያሳያል። አባቷ በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል። በሶፍት ዌሩ ላይ የሚቀርቡ ክሶች በርካታ ናቸው ። ምናልባትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ  ሀገራትን ሳይዳስስ እንዳልቀረ የሚጠቁሙ መረጃዎችም እየወጡ ነው ። ምን እና መቼ በሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች ሲደ,ርሱ እንመለስባቸዋልን። የፔጋሰስ ሶፍት ዌርን ያመረተው NSO ኩባንያ  ሶፍትዌሩን ያመረትኩትና የምሸጠውም ለወታደራዊና ደኅንነት ጉዳዮች ነው ሲል የመረጃ ምዝበራውን አልያም ስለላውን ያስተባብላል። የእስራኤል ባለስልጣናት በበኩላቸው ክሱን እናጣራለን እያሉ ነው ። 
ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ስናልፍ ደግሞ ጋዜጠኛ አስራ ጋዜጠኛ የፈታችውን ግብጽን ይመለከታል። በድጋሚ መልካም ቆይታ
ግብጽ ባለፈው ማክሰኞ በመላው ዓለም የተከበረውን የዒድ አልድሃ ወይም የአረፋን በዓል ምክንያት በማድረግ 40 እስረኞችን መልቀቋ ተሰምቷል። ከታሳሪዎቹ ውስጥ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና ሶስት የማህበራዊ አንቂዎች ወይም አክቲቪስቶች እንደሚig,ኙበትም ተገልጿል። የታሳሪዎቹ መፈታት ግብጽ በተለይ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶችን እያሳደደች ታስራለች የሚል ወቀሳ እየደረሰባት ባለበት ወቅት መሆኑ እንደመልካም ዜና ቢወሰድም ታሳሪዎቹ ዳግም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ መባሉ ግን ጉዳዩ  በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል። ከእስር ከተፈቱት ውስጥ የፌስ ቡኳ ልጅ ተብላ የምትታወቀው እና በአንድ ወቅት የዓለም የሰላም ኖቤል ዕጩ የነበረችው ኢዛራ አብደል ፋታህ ትገኝበታለች። ኢዛራ ጸረ መንግስት ሀሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተሻል በሚል ነበር ያለፉትን ሁለት ዓመታት በእስር ያሳለፈችው። ከእርሷ ጋር ከእስር የተፈታው ሌላው ታዋቂ የቴሌቪዢን ጋዜጠና እና የፌስ ቡክ እድምተኛ ጋማል ኤልጋማል አንዱ ነው። ጋማል በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ለአራት አመታት ከሰራበት ቱርክ ወደ ግብጽ እንደመጣ ነበር በዚህ ዓመት በቁጥጥር ስር የዋለው። በዋሽንግተን ዲሲ የመካከለኛ  ምስራቅ ጉዳዮች ጥናት ተ,ቋም የሆነው የታህሪር ተቋም  ዋና ዳይሬክተር ራሚ ያኩብ የታሳሪዎች መፈታትን በበጎ ጎን ጎን  እንሚመለከቱት ለዶይቼ ቬለ በስልክ የገለጹት። 
«የታሳሪዎቹ መለቀቅ አስደስቶኛል ፤ ከእነርሱ ውስጥ ሁለቱን ከአስር ዓመታት በላይ አውቃቸዋለሁ። ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ ልነግራችሁ አልችልም። ነገር ግን የመፈታታቸውን ጉዳይ ዘላቂ ነው ብዬ አላምንም። እነዚህ ሰዎች እንዲፈቱ ብናደርግም ገና በርካቶች በእስር ላይ አሉ» ብለዋል። ግብጽ ሰሞኑን ከእስር የፈታቻቸው ጋዜጨኞች እና የመብት ተሟጋቾች ሰሞኑን በተመሳሳይ ድርጊት ተሳትፈዋል ብላ ካሰረቻቸው ድርጊት ጋር የሚቃረን ሆኖ ነው የተገኘው። በዚሁ ሳምንት የታዋቂው ዕለታዊ ጋዜጣ አል አሕራም የቀድሞ ዋና አዘጋጅ አብደል ናስር ሰላማ ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት እና ሐሰተና መረጃ በማሰራጨት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል። የሀገሪቱ ከፍተኛ የወንጀል ችሎት የሚታይበት ፍርድ ቤት ደ,ግሞ ባለፈው ሳምንት የቀድሞውን የሕግ አርቃቂ ዚያድ ኤል ኤላይኒን ጨምሮ በስድስት ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች ላይ የከፈተውን ምርመራ አጠናክሮ ቀጥሏል። 
ይህ ብቻ አይደለም ግብጽ በጎርጎርሳውያኑ 2013 በሽብርተንነት በፈረጀችው እና የሙስሊም ወንድማማቾች ለሚባለው ድርጅት አባላት ምህረት የላትም።  
ባለፈው የሰኔ ወር  ሰኔ በ12 የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባላት ላይ የሞት ፍርድ ፈርዳለች። ይህንኑ ተከትሎም  የፍርደኛ  ቤተሰቦች ፍርዱን በመቃወም እና ዓለማቀፍ ትኩረት ይስብልናል ያሉትን  #StopEgyExecutions ሀሽታግ የሞት ፍርድ ይቁም የሚል የማሕበራዊ ዘመቻ ከፍተዋል። 
በዚህ የሞት ፍርድ ውስጥ ከተካተቱት አንዱ በጎርጎርሳውያኑ 2011 በግብጽ በተካሄደ አብዮት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዱ የነበረው  መሐመድ ኤል ቤልታጊ ነው። የመሐመድ ባለቤት ሳና አብደል ጋዋድ የግብጽ መንግስት የባለቤቴን መሰረታዊ የሰብአ,ዊ መብት ጥሷል ብላ የከሰሰችበትን ደብዳቤ አንዱን  ኮፒ ለዶይቸ ቬለ ልካለች። ሳና በደብዳቤዋ ካሰፈረቻቸው እንዲህ የሚለው ይገኝበታል። «ወታደራዊው መንግስት በመጨረሻ በባለቤቴ ላይ ሞት ፈረደበት ፤ ባለቤቴ እና ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሪዎች ለዓመታት መሰረታዊ እና በህይወት የመኖር መብቶቻቸውን ተነፍገው በሂደት እንዲሞቱ ከማድረግ ያልተናነሰ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል።» ብላለች። 
በአሁኑ ወቅት ከ60,000 በላይ የፖለቲካ እስረኞች  በግብጽ እንደሚገኙ የሰብአዊ መብት ተከታታዩ ድርጅት አስታውቋል። አምንስቲ ኢንተርናሽናል በጎርጎርሳውያኑ 2020 በርካታ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ ከተደረገባቸው ሀገራት መካከል ግብጽን ተጠቃሽ አድርጓታል። በ2019 32 ሰዎችን በሞት የቀጣችው ግብጽ በተከታዩ የ2020 107 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች ። 
እንግዲህ አድማጮች በሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው የዕለቱ የትኩረት በአፍሪካ ዝግጅታችንም ተጠናቋል ጤና ይስጥልን። 
 

Symbolbild Ägypten Gefängnis
ምስል picture-alliance/AA
Ägypten Journalisten protestieren gegen Festnahme zweier Kollegen in Kairo
ምስል Reuters/Staff
Ägypten Blogger Alaa Abdel-Fattah mit Schwester Sanaa Seif
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ammar
Südafrika ehemaliger Präsident Jacob Zuma
ምስል Michele Spatarii/AP Photo/picture alliance
Zypern | Pegasus Spyware | Webseite NSO Group
ምስል Mario Goldmann/AFP/Getty Images
Kombobild Cyril Ramaphosa und Paul Kagame
ምስል Jerome Delay/AP Photo/Stephane Lemouton/ABACAPRESS.COM/picture alliance
Indien Kalkutta | Protest gegen Pegasus Überwachung
ምስል Vishal Kapoor/Pacific Press/picture alliance
Ruanda | Emmanuel Macron in Kigali
ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images
Israel | NSO Group
ምስል Jack Guez/AFP/Getty Iamges