1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ተወሰነ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 30 2014

በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ መሠረት በአቶ ጃዋር መሐመድ እና በአቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ የተከሰሱ በሙሉ ከእስር ይፈታሉ። አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ የታሰሩት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስድስት ከፍተኛ አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ መንግሥት ወስኗል።

https://p.dw.com/p/45HFZ
Äthiopien Jawar Mohammed
ምስል Tiksa Negeri/Reuters

የኢትዮጵያ መንግሥት የቀድሞ የህወሓት መሪና አንጋፋ አባል አቶ ስብሐት ነጋ እና የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ፖለቲከኞችን እንዲፈቱ መወሰኑን አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ዛሬ አርብ ምሽት በሰጠው መግለጫ "ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት" መፍታቱን ገልጿል። ለአንድ አመት ከስድስት ወር ገደማ በእስር ላይ የቆዩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከእስር መፈታታቸውን ፓርቲያቸው አረጋግጧል። በአቶ እስክንድር የክስ መዝገብ የተከሰሱ በሙሉ እንዲፈቱ መወሰኑን መንግሥት አስታውቋል። 

በዛሬው የመንግሥት ውሳኔ ከእስር በምሕረት ይፈታሉ ከተባሉት መካከል አቶ ጀዋር መሐመድ ይገኙበታል። የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ የታሰሩት ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ከተገደለ በኋላ የተቀሰቀሰውን ኹከት ተከትሎ ነው።

Deutschland Äthiopiens Oromo federalist congress |  Dejene Taffa
ለአስራ ስምንት ወራት ገደማ በእስር ላይ ከቆዩት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች መካከል አቶ ደጀኔ ጣፋ መፈታታቸውን ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል።ምስል Eshete Bekele Tekele/DW

ለአስራ ስምንት ወራት ገደማ በእስር ላይ ከቆዩት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች መካከል አቶ ደጀኔ ጣፋ መፈታታቸውን ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። የኢትዮጵያ መንግሥት በአቶ ጀዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ በሙሉ እንደሚፈቱ በመግለጫው ጠቁሟል። 

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ የታሰሩት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስድስት ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ውሳኔ እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው መካከል ናቸው። በውሳኔው መሠረት ከህወሓት መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ ከእስር ይፈታሉ።

ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚዓብሔር እና አቶ ኪሮስ ሐጎስ በምሕረት እንደሚፈቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ለእስረኞቹ የተሰጠው "ምሕረት ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን ይጨምራል" ብሏል። ውሳኔው "የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልህና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት" እና "ለሰላማዊ ፖለቲካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት" የተላለፈ መሆኑን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት አስታውቋል። 

እሸቴ በቀለ 
ነጋሽ መሐመድ