1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ጀዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎች መታሰራቸውን መንግሥት አረጋገጠ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012

የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው “በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የሚመራ ቡድን አስከሬኑን በመንጠቅ በመኪና ጭነው ስቴዲዮም አካባቢ ወደ ሚገኘው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ውስጥ አምጥተው በማስገባት አስከሬኑንና ቤተሰቦቹን ለእንግልት“ ዳርገዋል ብለዋል። በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ ፖሊስ መገደሉ ተገልጿል

https://p.dw.com/p/3ebPS
Äthiopien Addis Abeba Oppositionsführer Jawar Mohammed
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራር አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አረጋገጠ። የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጥምረት በሰጡት መግለጫ ወደ አምቦ በማቅናት ላይ የነበረውን የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ተደርጓል በተባለ “ግርግር” አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረባ መገደሉን ገልጸዋል።

አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ መታሰራቸውን ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ነበር። የቴሌቭዥን ጣቢያው በወቅቱ በፌድራል እና በኦሮሚያ የጸጥታ አስከባሪዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበርም ይፋ አድርጓል። ዛሬ ምሽት የፌድራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ጉዳዩን አረጋግጠዋል።

የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው እንዳሉት አቶ ጃዋርን ጨምሮ 35 ሰዎች የታሰሩት “የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ከጳውሎስ ሆስፒታል ወደ ትውልድ ሥፍራው ወደ አምቦ“ የሚያደርገውን ጉዞ በማቋረጥ ወደ አዲስ አበባ በመመለሳቸው ነው።

“በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የሚመራ ቡድን አስከሬኑን ከሚሔድበት በመንጠቅ በቀጥታ በአንድ መኪና ጭነው ስቴዲዮም አካባቢ ወደ ሚገኘው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ውስጥ አምጥተው በማስገባት አስከሬኑን እና ቤተሰቦቹን ለእንግልት“ ዳርገዋል ብለዋል።

የድምፃዊው ግድያ በቀሰቀሰው ቁጣ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች እና የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጆች የሐጫሉ አስከሬን በችኮላ ወደ አምቦ መወሰዱን አልተቀበሉም ነበር። ተደማጭነት ያላቸው አክቲቪስቶችን ጨምሮ በርካቶች የሐጫሉ ቀብር በአዲስ አበባ እንዲፈጸም ቢጠይቁም ተቀባይነት አላገኙም።  የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከአርቲስቱ ቤተሰቦች ጋር ጥብቅ ውይይት ተደርጎ ከስምምነት በመደረሱ ቀብሩ በትውልድ ቀዬው አምቦ እንዲከናወን መወሰኑን ተናግረዋል።

አስከሬኑ ወደ አምቦ ከማቅናቱ በፊት በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል መገደሉን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።  የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው “በጽህፈት ቤቱ በነበረ ግርግር በስፍራው በጥበቃ ላይ የነበረ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ ተገድሏል። ይኸ ፖሊስ የተገደለው አስከሬኑን ከዚያ ይዘው በመጡ ተሰብስበው ከነበሩ አካላት በተተኮሰ ጥይት መሆኑንም የቅድሚያ መረጃችን አረጋግጦልናል“ ብለዋል።

ስምንት ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ አምስት ሽጉጦ እና ዘጠኝ የመገናኛ ሬዲዮኖች “የአቶ ጃዋር አጃቢ ወይም ተከታዮች ከነበሩ ሰዎች“ መያዛቸውን ኮሚሽነር ጄኔራሉ ተናግረዋል። “ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም“ ያሉት እንዳሻው ምርመራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

ሐጫሉን ማን ገደለው?

ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ በማን እንደተገደለ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም። የኢትዮጵያ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው “የወንጀል ሁኔታው ሲበዛ ውስብስብ በተደራጀ መንገድ የተፈጸመ“ መሆኑን ዛሬ ማታ በብሔራዊው ቴሌቭዥን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።    

“ትናንት ሰኞ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም በሚባል አካባቢ  የግል መኪናውን እያሽከረከረ አንድ ቦታ አቁሞ ወርዶ ሲመለስ ከኋላ በተከተሉት ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል“ ብለዋል።  

“እስካሁን ባደረግናቸው ዋና ዋና ማጣራቶች የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በፍለጋ ላይ ነው የምንገኘው“ ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ ቀሪዎቹን “እንይዛቸዋለን የሚል ተስፋ አለን“ ሲሉ ተደምጠዋል።