1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ

ሰኞ፣ ጥቅምት 8 2014

ዛሬ ሥራ የጀመረው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ክልሉን ሲመሩ የነበሩት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ፕሬዝደንት፣ አቶ ኢብራሒም ኡስማን ምክትል ፕሬዝደንት አድርጎ ሾሟል። መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት አጠቃላይ 273 ወንበሮች 262ቱን ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል

https://p.dw.com/p/41npJ
Äthiopien Ibrahim Usman
ፎቶ፦ ከማሕደርምስል Mesay Tekelu/DW

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ባካሔደው ጉባኤ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ። ባለፈው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምርጫ በተካሔደበት የሶማሌ ክልል ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. መንግሥት ተመስርቷል። 

የሶማሌ ክልልን በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ ሲመሩ የቆዩት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር በፕሬዝደንትነት ለሚቀጥሉት አምስት አመታት እንዲያገለግሉ ዛሬ በይፋ ሥራ በጀመረው ምክር ቤት ተመርጠዋል። አቶ ኢብራሒም ኡስማን የክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው በምክር ቤቱ ሹመታቸው ጸድቋል። 

አቶ ሙስጠፌ የክልሉን ሥልጣን የጨበጡት ከሶስት ገደማ አመታት በፊት የቀድሞው ፕሬዝደንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ከተነሱ በኋላ ነበር። 

ከፕሬዝደንቱ እና ምክትል ፕሬዝደንቱ ሹመት ቀደም ብሎ አዲስ ለተመሠረተው የክልሉ ምክር ቤት ወይዘሮ አያን አብዲ አፈ-ጉባኤ አቶ ኢብራሒም ሐሰን አሊ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል። 

በመርሐ-ግብሩ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የሶማሊላንድ ምክትል ፕሬዝደንት አብዱረህማን አብዱላሂ ሰይሊኢ ታድመዋል።

የክልሉ መንግሥት የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤትን ጨምሮ 27 አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አሉት። ተቋማቱ የአደረጃጀት እና የስያሜ ለውጥ ማድረጋቸውን የሶማሌ ክልል ኮምዩንኬሽን ቢሮ ትናንት እሁድ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። 

መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት አጠቃላይ 273 ወንበሮች 262ቱን ብልጽግና ፓርቲ እንዳሸነፈ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

በአንድ ምርጫ ክልል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እና አንድ የግል እጩ በጋራ መቀመጫ እንዳገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። የሶማሌ ክልል በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን 23 መቀመጫዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ አሸንፏል።

ጅጅጋ ከተማ እና ሙዩሙሉቄ የተባሉ ሁለት የምርጫ ክልሎች የክልል ምክር ቤት የምርጫ ውጤቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ውጤት ውስጥ አልተካተቱም። 

በሶማሌ ክልል ለተካሔደው ምርጫ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ራሳቸውን በማግለል ሳይሳተፉ ቀርተዋል።