1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መስፍን አሻግሬና የፈረንሳይ ተሞክሮአቸው 

ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2012

አቶ መስፍን ፈረንሳይ የሄዱት እዚያ ለመኖር ፈልገው ወይም ተዘጋጅተው አልነበረም፤ባላሰቡት አጋጣሚ እንጂ።32 ዓመታት በኖሩባት በፈረንሳይ፣ አስተርጓሚ ናቸው።የሚያስተረጉሙትም ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ነው።ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለሌሎችም የውጭ ዜጎች  በሚሰጡት በዚህ አገልግሎት ደስተኛ ናቸው።በአውሮጳ የስደተኞች አሳዛኝ እጣ ሁሌም ይፈትናቸዋል  

https://p.dw.com/p/3Pk0q
Mesfin Ashagre
ምስል privat

ፈረንሳይኛ አስተርጓሚዉ መስፍን አሻግሬና ተሞክሮዋቸዉ

ለበርካታ ዓመታት በኖሩባት በፈረንሳይ፣ አስተርጓሚ ናቸው።የሚያስተረጉሙትም ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ነው።ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለሌሎችም የውጭ ዜጎች በሚሰጡት በዚህ አገልግሎት ደስተኛ ናቸው። የሃላፊነቱ ክብደት እና በተለይ በሥራቸው አጋጣሚ የሚሰሙት እና የሚያዩት የስደተኞች አሳዛኝ እጣ ግን ሁሌም ይፈትናቸዋል። ስሜታቸውንም ይነካል።
ከ30 ዓመት በፊት በሄዱባት በፈረንሳይ  በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋንቋውን አቀላጥፈው በመናገር እና በመረዳት ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው እዚያ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እና ሌሎች አፍሪቃውያንን መርዳት በሚችሉበት ሞያ ለመሰማራት በቅተዋል።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ አውሮጳ በብዛት ለገባው እና አሁንም እየገባ ላለው አፍሪቃዊ ስደተኛ ፣በትምሕርት ቤት በእስር ቤት እና በፖሊስ ጣቢያ እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ የፍትህ ተቋማት ለፈረንሳይ መንግሥት በአስተርጓሚነት ይሰራሉ ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ የፓሪስ ነዋሪ አቶ መስፍን አሻግሬ።
አቶ መስፍን ፈረንሳይ የሄዱት እዚያ ለመኖር ፈልገው ወይም ተዘጋጅተው አልነበረም።ባላሰቡት አጋጣሚ እንጂ።በዚህ ዓይነት አጋጣሚ የዛሬ 32 ዓመት ፈረንሳይ የሄዱት አቶ መስፍን ፣እዚያ ተምረዋል።ሕጋዊ አስተርጓሚ ከመሆናቸው በፊትም በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ አልፈዋል።እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት የሚያስደስታቸው አቶ መስፍን በሙያቸው ምክንያት የሚሰሙ እና የሚያዩዋቸው ለዐዕምሮ የሚከብዱ አሳዛኝ አሰቃቂ ክስተቶች ስሜታቸውን እንደሚነኩ አንዳንዴም እንደ ደሚፈታተኑዋቸው ይናገራሉ።ስደተኞች በአውሮጳ ይሄ ሁሉ ስቃይ እንደሚደርስባቸው ቢታወቅም አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩት ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም። ፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ይጠለሉበት የነበረውን ካሌ የሚገኘውን የስደተኞች የጫካ መንደር ከሦስት ዓመት በፊት ብታፈራርስም ስደተኛው በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሆኖ እድሉን መጠባበቅ ቀጥሏል። 

ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ