1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  «ሕዝቡ የስርዓት ለዉጥ ይፈልጋል።»

ሰኞ፣ መስከረም 12 2012

ከዓለም የ10ኛ ደረጃ የያዘዉን ግዙፍ  ጦር የአዛዥነት ሥልጣንን ድንገት የተረከቡት አስ ሲሲ ስልጣን በያዙ በሰባተኛዉ ወር ለጦሩ ያስተላለፉት መልዕክት ግን ሰዉዬዉ የመሰሉትን እንዳልሆኑ፣ የታመነቱን እንደማይጠብቁ፣ ምናልባትም ለፍትሕ ዴሞክራሲ ሥፍራ እንደሌላቸዉ ጠቋሚ ሆነ

https://p.dw.com/p/3Q7Ge
Ägypten Kairo | Anti-Regierungsproteste
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

ግብፅ፣ ከ6 ዓመት ዕረፍት በኋላ ሌላ ተቃዉሞ

ስዊድናዊቷ ታዳጊ ወጣት ግሬታ ታንበርግ የቀሰቀሰችዉ የዓለም ሕዝብ የዓየር ንብረት እንዲጠበቅ ባለፈዉ አርብ ተሰለፈ።በአምስት መቶ ከተሞች በየአደባባዩ የጎረፈዉ ሰልፈኛ አራት ሚሊዮን ተገምቷል።ግብፆችም  አርብ ማምሻ በየከተማቸዉ አደባባይ ወጥተዉ ነበር።መልዕክት፣ ፍላጎት ዓላማቸዉ ግን ተፈጥሮን ማስጠበቅ አልነበረም።መብትን እንጂ።

                      «ተናገር።አትፍራ።ሲሲ (ከስልጣን) መወገድ አለባቸዉ»

አብድል አል ፈታሕ ሰዒድ ሁሴይን ቻሊ አስ-ሲሲ።እንደ ሆስኒ ሙባረክ ሁሉ ለሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት የቅርብ ሸሪክ፣ለዋሽግተኖች ታማኝ አገልጋይ፣ ለመብት ተሟጋቾች፣ለዴሞክራሲ አቀንቃኞች አምባገነን፣ለሕዝባቸዉ ፈላጭ ቆራጭ እና አሁን ደግሞ ሙሰኛ ናቸዉ።የ2019 መስከረም (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)  የ2011 ጥርን ያስታዉሰን ይዟል።የ2011 ይደገም ይሆን? ላፍታ የሆነዉን እየጠቃቀስን የሚሆነዉን እንጠይቅ።

 ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲ ነሐሴ 12 2012 ጄኔራል አብደል ፈታሕ አስ ሲሲን በመከላከያ ሚንስትርነትና በጠቅላይ ኤታመማዦርነት ሲሾሙ ጦሩን በሕዝባዊ አብዮት ከስልጣን ከተወገዱት ከሆስኒ ሙባረክ ታማኞች የማፅዳት ርምጃ ተደርጎ ነበር።በርግጥ ከአብዛኞቹ የጦር ጄኔራሎች ወጣቱ፣ መስጊድ አዘዉታሪዉ፣ስለፖለቲካ ብዙም የማያዉቁ፣የማይታወቁትም ጄኔራል የነናስርን ፖለቲካዊ አስተምሕሮ ከጦሩ አርቀዉ ወታደሩን በወታደርነቱ ብቻ እንዲያገለግል የሚቀርፁ በዉጤቱም ለጅምሩ ዴሞክራሲዊ ስርዓት ፅናት የሚታትሩ መስለዉም ነበር።

Ägypten Anti-Regierungsproteste in Kairo
ምስል Reuters/A. A. Dalsh

መንግስት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎችም «አብዮታዊ አስተሳሰብ ያላቸዉ የጦር አዛዥ»  እያሉ አንቆለጳጵሰዋቸዉ።ከዓለም የ10ኛ ደረጃ የያዘዉን ግዙፍ  የጦር አዛዥነት ሥልጣንን ድንገት የተረከቡት አስ ሲሲ ስልጣን በያዙ በሰባተኛዉ ወር ለጦሩ ያስተላለፉት መልዕክት ግን ሰዉዬዉ የመሰሉትን እንዳልሆኑ፣ የታመነቱን እንደማይጠብቁ፣ ምናልባትም ለፍትሕ ዴሞክራሲ ሥፍራ እንደሌላቸዉ ጠቋሚ ሆነ።ሲና ከእስራኤል አገዛዝ ነፃ የወጣችበት በዓል ሚያዚያ 28 2013 ሲከበር ባደረጉት ንግግር «ግብፃዉያንን የሚጎዳ የማንኛዉ ኃይል እጁ ይቆረጣል» ነበር ያሉት።መልዕክቱ ግብፃዉያንን አከራክሮ ሳያበቃ አይናፋሩ ጄኔራል የሾሙ የሸለሟቸዉን፣ ያመኑ-ያስጠጓቸዉን ከሁሉም በላይ በሕዝብ የተመረጡትን የፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን የስልጣን ገመድ በጥሰዉ ጣሉት።

                                  

«ይሕ ፍኖተ ካርታ የሚከተሉትን ያካትታል።ሕገ መንግስቱ ለጊዜዉ ታግዷል።የሐገሪቱ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ አስቸኳይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዲደረግ ያዉጃሉ።አዲስ ፕሬዝደንት እስኪመረጥ ድረስ የሕገ-መንግስታዊዉ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የመንግስትን የዕለት ከዕለት ስራ ያከናዉናሉ።»

ኃምሌ 3 2013።መፈንቅለ መንግስቱ፣ ጅምሩ ዴሞክራሲ መጨናገፉን የሚያረጋግጥ፣ ትልቂቱን፣ የረጅም ታሪክ ባለቤቲቱን አረብ-አፍሪቃዊት ሐገር ከ1952 ጀምሮ ወደነበረችበት ወታደራዊ አገዛዝ እንደሚመልስ የተናገሩ፣ያስጠነቀቁ፣ ባደባባይ የተቃወሙትም ብዙ ነበሩ።«እዚሕ አደባባይ የወጡት ሰዎች የግብፅ የመጀመሪያዉ ዴሞክራሲ ገና ሲወለድ መጨናገፉን የሚቃወሙ ናቸዉ።ወታደራዊዉ መፈንቅለ መንግስት ሕገ-መንግስቱንም የሚፃረር ነዉ።»

የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ ብዙም የለም።በተለይ የርዕሠ ከተማ ካይሮ ነዋሪዎች ከዓመት በፊት በአብላጫ ድምፅ የመረጧቸዉ ፕሬዝደንት ከስልጣን መወገዳቸዉን ደግፈዉ ባደባባይ ቦረቁ።የመፈንቅለ መንግሥቱን መሪና አስተባባሪ የጄኔራል አሲሲን  ፎቶ ግራፍ አንግበዉ ያደንቁ፣ያወድሱ፣ያሞግሷቸዉ ገቡ።

አስ ሲሲ ባጣሙን ገማል አብድናስርን፣ በጥቂቱ አንዋር አሳዳትን መሆናቸዉን አረጋገጡ።የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር መሪዎችን፣አባላትን እና ደጋፊዎችን እያስለቀሙ ወሕኒ ወረወሯቸዉ።የማሕበሩን መገናኛ ዘዴዎች፣ፅሕፈት ቤቶች፣የርዳታ ድርጅቶች፣ትምሕርት ቤቶችን በሙሉ ዘጉ።

አስ ሲሲ ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን ኃምሌ መጀመሪያ ላይ ከስልጣን ለማስወገዳቸዉ የሰጡት ሰበብ ሰኔ ላይ የሙርሲን አገዛዝ ባደባባይ ሰልፍ ለመቃወም የወጣዉን ሕዝብ የሙርሲ ደጋፊዎች አጥቅተዋል የሚል ነበር።

ጄኔራሉ የመሩትን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም አደባባይ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን በጅምላ አስረሸኑ።ሺዎችን አሰሩ።የሙስሊም ወንድማማቾችን ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራትን፣ ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን ዘጉ። መንግስታቸዉ ሳይፈቅድ የአደባባይ ሰልፍ እንዳይደረግ አገዱም።

ለራሳቸዉ ግን የማርሻልነት ማዕረግ ደረቡ።

የአሲስን ርምጃ ቀድመዉ የደገፉት ሕዝባዊዉ አመፅ እንደ ሙባረክ፣እንደ ቤን ዓሊ እንደ ሙባረክ ለዘመናት ከቆዩበት ቤተ-መንግስት አሽቀንጥሮ ይጥለናል ብለዉ የፈሩት የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት ኤሚሬቶች ነግስታትና ብጤዎቻቸዉ ነበሩ።

ሁለቱ ሐገራት የማርሻሉን የአፈና ርምጃ ለማጠናከርም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ካይሮ ያንቆረቁሩ ገቡ።ሌላ ሐገር የሚደረግ መፈንቅለ መንግስትን ለማዉገዝ ሰዓታት የማይፈጅባቸዉ የዋሽግተንና የብራስልስ ፖለቲከኞችም (ከያኔዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በስተቀር)  የአሲሲን መፈንቅለ መንግስት ባይደግፉት እንኳን በይፋ አላወገዙትም።   

አሲሲ የማርሻል ማዕረጋቸዉን አዉልቀዉ በኮት-ከራባት ፕሬዝደንት ከሆኑ በኋላ እንኳ ተቺዎቻቸዉን እያሳደኑ ማሰር-ማስፈረዱን አላቋረጡም።ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምስንስቲ ኢንተርናሽናል አንደዘገበዉ የአሲሲ መንግስት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ፖለቲከኛ፣ጋዘጠኛና የመብት ተሟጋቾችን አስሯል።

የመብት ተሟጋቹ የአልሲሲን አፋኝ፣ጨቋኝነት በይፋ በሚያወግዙበት ወቅት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በክብር እንግድነት ጋበዟቸዉ።መስከረም 2017።ዋይትሐዉስ።«የግብፁ ፕሬዝደንት አስ ሲስ ዛሬ እዚሕ በመምጣታቸዉ ታላቅ ክብር ተሰምቶኛል።በተለያዩ መስኮች ለረጅም ጊዜ ጠንካራ ሥራ አከናዉነናል።ብዙ ዉጤትም አግኝተናል።ላደረጉት በሙሉ አመሰግናለሁ።አደንቃለሁም።እኛም የሰራነዉን እንደሚያደንቁ አዉቃለሁ።ግንኙነቱ በጣም ጥሩ ነዉ።»

ትራምፕ አስ ሲሲንና ስራቸዉን ሲያደንቁ ቢያንስ 12 የአሜሪካ ዜጎች ግብፅ እስር ቤቶች ዉስጥ ይማቅቁ ነበር።አስ ሲሲ ግብፅን እስከ 2034 ድረስ መግዛት የሚያስችላቸዉ ሕገ-መንግስት ያስረቅቁ ነበር።17 የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች (ሴናተሮች) ፕሬዝደንቱ የግብፁን አምባገነን እንዳያነጋግሩ፣ካነጋገሩም የአስ ሲሲን ጭቆና እንዲቃወሙ ይጠይቁ ነበር።ሴናተር ፓትሪክ ሌሒ አንዱ ናቸዉ።

Abdel-Fattah el-Sissi Rede
ምስል picture alliance/AP Photo

«አሁን ባለዉ ፕሬዝደንት አመራር ግብፅ በጣም አደገኛ ጎዳና እየተከተለች ነዉ።ፍፁም ጨቋኝ አምባገነን ሥርዓት ነዉ።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሴናተሮቻቸዉን ተቃዉሞ፣የመብት ተሟጋቾችን አቤቱታ፣የፖለቲካ ተንታኞችን ብያኔን ምናልባት ፈጥነዉ አዉቀዉት ይሆናል።በይፋ የተናገሩት ግን ባለፈዉ ነሐሴ ቢያሬትስ-ፈረንሳይ በተሰመየዉ የቡድን 7 ጉባኤ ላይ ነበር።ትራምፕ ከግብፁ መሪ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ወደያዙበት ክፍል ሲገቡ «የምወደዉ አምባገነን የታለ?» ብለዉ ጠየቁ አሉ እዚያ የነበሩ።

ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበዉ ትራምፕ ያሉትን ሲሉ የግብፁን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጨምሮ የሁለቱ ሐገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይሰሙ ነበር።የቀድሞዉ ማርሻል የሰሙት ግን ቁልምጫዉን ነዉ።

«ፕሬዝደንት አስ ሲሲ መጀመሪያ ካገኘኋቸዉ ጊዜ ጀምሮ በጣም ከምቀራረባቸዉ ሰዎች አንዱ ናቸዉ።መጀመሪያ ያወቅኋቸዉ በምርጫ ዘመቻዬ ወቅት ነዉ።ፕሬዝደንት አሲሲ በጣም አስቸጋሪ በሆነ-ሁኔታ በርካታ አስገራሚ ስራዎችን ሰርተዋል።ከግብፅ እና ከግብፅ ሕዝብ ጎን እንደቆመች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ትደግፋችኋለች።ክቡር ፕሬዝደንት ለርስዎ ማለት እመፈልገዉ ዩናይትድ ስቴትስና ከኔ ጠንካራ ድጋፍና ወዳጅነት አላችሁ።»

Ägypten Kairo | Anti-Regierungsproteste
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

በፕሬዝደንት ትራምፕ አገላለፅ ዩናይትድ ስቴትስ ከጎኑ የማትለየዉ የግብፅ ሕዝብ ከ6 ዓመታት ትዕግስት፣አፈና፣መከራ፣ፍራቻ በኋላ የአስ ሲሲን አገዛዝ ባደባባይ ተቃወመ።ባለፈዉ አርብ በየከተማዉ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ቁጥር የሚሊዮኖችን ሰልፍ ለለመደችዉ ግብፅ በርግጥ ትንሽ ነዉ።በመቶ የሚቆጠር።ኢምንቶች ሚሊዮኖች እንደሚሆኑ ግን ከራስዋ ከግብፅ፣ ከ2011ዱ ሰልፍ ሌላ የተሻለ ምሳሌ በርግጥ የለም።

ከካይሮዉ ተሕሪር አደባባይ፣እስከ ሜድትራንያን ባሕር ጥጓ ከተማ አሌክሳንደሪያ፣ ከቀይ ባሕሯ ዳርቻ ስዊዝ እስከ ዓባይ ዳርቻዋ ማሐላ በየስፍራዉ የተሰለፈዉ ሕዝብ ያቀነቀናቸዉ መፈክሮችም የሚደርስበትን ጭቆና፣ያለበትን ፍራቻ በግልፅ መስካሪ ነዉ።«ተናገር።አትፍራ።ሲሲ (ከስልጣን) መወገድ አለባቸዉ።»

የአስ ሲሲ መንግስት ተቃዋሚ ሰልፈኛን አሸባሪ እያለ ባደባባይ ሲረሽን፤እያፈሰ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ ያየ፣ ሰልፍ እንዳይደረግ በሕግ መታገዱን የሚያዉቅ ግብፃዊ መፍራቱ አያስወቅሰዉም።የሰልፈኛዉ ቁጥርም ካነሰባቸዉ ምክንያቶች አንዱ ፍራቸዉ ነዉ።

Biarritz G7-Gipfel Donald Trump, Abdel Fattah al-Sisi
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Harnik

የተቃዉሞዉ መነሻ ፕሬዝደንቱና የጦር አዛዦቻቸዉ በሙስና ተዘፍቀዋል መባሉ ነዉ።ከሐገሩ ተሰድዶ ስጳኝ የሚኖር አንድ ግብፃዊ አንዳጋለጠዉ አስ ሲሲና የጦር አዛዦቻቸዉ ከመንግስት ካዝና በሚወስዱት ገንዘብ የየግላቸዉን ቤተ-መንግስት አከል ቤት እየገነቡ፣ኑሯቸዉን እያቀማጠሉ፣ዘመድ ወዳጆቻቸዉን እያበለፀጉ ነዉ።

የግብፅ የጦር ጄኔራሎች በሙስና የተዘፈቁ፣የትላልቅ የንግድ ድርጅቶችና ተቋማት ባለቤቶች መሆናቸዉ ለግብፅ ሕዝብ በርግጥ እንግዳ አይደለም።

ስጳኝ የተሰደደዉ ግብፃዊ  በመሐበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያሰራጨዉ መልዕክት ግን ግብፃዊዉ ወትሮም በየቤቱ የሚያብሰለስለዉን ሐቅ ባደባባይ ያፈጋ፣ የሕዝብን የጋራ ብሶት ያጋለጠ በመሆኑ ጋር ከ2013 ወዲሕ እርስ በርሱ የሚጠራጠረዉን ወጣት በጋራ ማቆም፣ በቀላሉ ማሳደም ችሏል።

                                        «ሕዝቡ የስርዓት ለዉጥ እንዲደረግ ይፈልጋል።»

ፕሬዝደንት አስ ሲሲ ሕዝብን ለተቃዉሞ ስላሳደመዉ ሙስና በቀጥታ ያሉት ነገር የለም።ባለፈዉ ሳምንት ካይሮ ዉስጥ ለተሰበሰቡ ወጣቶች ባደረጉት ንግግር ግን ጦር ሠራዊታቸዉ በሙስና መታማት፣መተቸት የለበትም በማለት አሳስበዋል።ለግብፅ ጦር በየዓመቱ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ የምታስታጥቀዉ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከግብፅ ሕዝብ ጎን እንቆማለን ሲሉም አብነት የተጠቀሱት አፋኝ አምባገነን ገዢ፣ ሙስኛ ጄኔራሎች ለሚያዙት፣ ግብፃዉያንን በተለይ ሲናዎችን አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ የአሸባባሪ ተባባሪ እያለ  ለሚገድለዉ ጦር አሜሪካ የምታስታጥቀዉን ጦር መሳሪያ ነዉ።

«የጦር ኃይላችንን ከዚሕ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ እየገነባን ነዉ።የተዋጊ ጄቶች ግዢ ትዕዛዝ፣የመርከቦች ትዕዛዝ፣የአዉሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ትዕዛዝ፣ የጦር ኃይላችን በጣም እያዘመነን እያደረጀን ነዉ።በዚሕ ባለንበት ወቅት ከምግዜዉም በላይ የሚያስፈልገን ይኽ ነዉ።»

የአርቡ ተቃዉሞ ሰልፈኛ የሚለዉ አስ ሲሲ በቁን «ሒዱልን ነዉ።» ፍትሕ፣ዴሞክራሲ ይስፈን ነዉ።ትራምፕ ግን ዳቦ፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ ለሚለዉ ሕዝብ የጦር መሳሪያ መድሐኒት ያዙለታል።የአርቡ ሰልፍ ሲደረግ አሲስሲ ስለተፈጥሮ ጥበቃ መከበር በሚመክረዉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደ ኒዮርክ እየተጓዙ ነበር።ሕዝባቸዉ ፍትሕ፣የስርዓት ለዉጥ እየጠየቃቸዉ፣ ዛሬ በተጀመረዉ ጉባኤ ላይ የከባቢ አየር መከበር አለበት ይሉ ይሆናል።

Bildkombo Ägypten Präsidenten | Abdel Fattah al-Sisi & Gamal Abdel Nasser

ጥር አጋማሽ 2011 ተሕሪር አደባባይ ብቅ ያሉት ወጣቶች ቁጥር ሲበዛ አነስተኛ ነበር።ብዙም ሳይቆዩ ፀጥታ አስከባሪዎች በተኗቸዉ።የሰልስፈኛዉ ቁጥር ማነስ፣ባጭር ጊዜ ከመበተኑ ጋር ተዳምሮ ሰልፉ ለትላልቆቹ መገናኛ ዘዴዎች ዘገባ እንኳን አልበቃም ነበር።የመጀመሪያዉ ሰልፍ በተደረገ በሁለተኛ ሳምንቱ ግድም ታሕሪር አደባባይ በሰልፈኛ ተጥለቀለቀ።ጥር 25 2011።ዘንድሮ አርብ መቶዎች ብልጭ ብለዋል።በፀጥታ ኃይሎች አስላቅሽ ጢስ ታጥነዉ፣ተበትነዋል። እንደ 2011ዶቹ ይደምቁ ይሆን? ወይስ ብልጭ እንዳሉ ይከስሉ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ