1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የኮሮና ተኅዋሲ ሥርጭት በአማራ ክልል

ሐሙስ፣ መጋቢት 23 2013

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።በተኅዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ የሚያስከትለው ጉዳትም አስከፊ ሆኗል።ችግሩ በአማራ ክልልም እየሰፋና በተኅዋሲው ሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርምም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን በየአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባቶች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ተናግረዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3rTkl
Äthiopien | Coronavirus | Impfungen
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል አሳሳቢ የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ

አሳሳቢው የኮሮና ተኅዋሲ ሥርጭት በአማራ ክልል
በአማራ ክልል የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት አሳሳቢ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፤ ቢሮው የኮሮና መከላከያ ክትባት ለመስጠት የሚችሉ የጤና ባለሙያዎችን እያሰለጠነ ነው፣ ስለክትባቱ በህብረተሰቡ ዘንድ አሉታዊም አዎንታዊም አስተያየት ይሰጣሉ። 
የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።በተኅዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ የሚያስከትለው ጉዳትም አስከፊ ሆኗል።ችግሩ በአማራ ክልልም እየሰፋና በተኅዋሲው ሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርምም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን በየአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባቶች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ 
ለስርጭቱ መባባስ የህብረተሰቡ ቸልተኝነትና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ አለመጠቀም አንዱ ምክንያት እንደሆነ አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል።የክትባት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ባለፈው መጋቢት 4/2013 ዓም በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ጠቅላላ ሆስፒታል እንደተተከናወነ ያስታወሱት አስተባባሪው በጤናው ዘርፍ ለሚሰሩ በአጠቃላይ ከ80ሺህ በላይ ሰራተኞችን ክትባት ለመስጠት ስልጠና እየተሰጠ እነደሆነና በቀጣዩ ሳምንት ሁሉም የጤና ሰራተኞች ክትባቱን እንደሚወስዱም ገልጸዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንዳንድ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪዎች ክትባቱ ችግር አለበት ብለው ስለሚያምኑ ለመከተብ ፈቃደኛ አይደሉም።ሌላው አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ደግሞ ጤና ቢሮውም ሆነ የመገናኛ ብዙሐን ተገቢውን ግንዛቤ ስላልፈጠሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እንዳለ አመልክተው ቢሆንም ግን እርሳቸው ለመከተብ ዝግጁ ናቸው።ክትባቱ ወደፊት በአማራ ክልል ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑት ሁሉ እንደሚሰጥ የተናገሩት የክትባት አስተባባሪው አቶ ወርቅነህ ክትባቱ የሚያመጣው ችግር የለም፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ይሰራሉ ብለዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሚያወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአማራ ክልል እስከትናንትና ድረስ 255ሺህ 839 ሰዎች ተመርምረው 7ሺህ 899 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፣ 152ቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ