1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ችግር

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ነሐሴ 9 2010

በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር 2.8 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ፣ ዩኒሴፍ ባወጣዉ ዘገባ አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/33E2s
IOM hat einen Appell für 22.200.000 USD gestartet, um auf die Vertreibungskrise in den Gedeo- und West-Guji-Zonen in Südäthiopien zu reagieren
ምስል Fana Broadcasting Corporate/EBC

Displaced people reached 2.8 million - MP3-Stereo

ከኦሮሚያ ፤ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ከኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል በርካታ ሰዎች በግጭትና በድርቅ ምክንያት ከቀያቸዉ በመፈናቀል ላይ መሆናቸውን  ዘገባዎች ይጠቁማሉ። የተፈናቃዮቹ ቁጥር በጥር ወር ዉስጥ 1,6 ሚሊዮን እንደነበረ የሚናገሩት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጁሊየን ሜልሶፕ አሁን ቁጥሩ ባጠቃላይ 2,8 ሚሊዮን መድረሱን ገልፀዋል።

ለቁጥሩ መጨመር ይላሉ ጁሊየን ሜልሶፕ፣ «ይህም የሆነበት ምክንያት በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ በነበረዉ ግጭቶች ነዉ። ይህ ግጭትም ከ800 ሺህ በላይ ከቀያቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኖዋል። ከዚህም ዉስጥ በጣም የተጎዱት ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉ። ተፈናቃዮቹ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው ተጥለለው የሚገኙት። በጠባብ ቦታዎች ውስጥ በአንድ ላይ ተጠባብቀው ነዉ የሚኖሩት። መሰረታዊ አገልግሎቶች የሉም። የዉሃ እጥረት ስላለ ፣ የፅዳት ጉድለት የበሽታ ወረርሽኝ ያስከስታል የሚል ስጋትም አለ።»

ከኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ሰብዓዊ ቀውሱ ላይ እየሰራን ነዉ ያሉት የዩኒሴፍ ተወካይ ጁሊየን ሜልሶፕ ከጥር ወር ጀምሮ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጠማቸዉ 140,000 ሕፃናቶችን ኢየረዱ እንደሆነ ገልፀዋል። ተፈናቃዮች የግል ፅዳታቸውን እንዲጠብቁ፣ ከቤተሰቦቻቸዉ የተለያዩት ዳግም እንዲገናኙ ትምህርታቸዉን ያቋረጡት በመስከረም ወር ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ዩኒሴፍ ኢየሰራ መሆኑን ጂሊያን ገልፀዋል።

ድርጅቱ ለሰብዓዊ ቀውሱ መፍትሄ ለመስጠት የገንዘብ ርዳታ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፣ «በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያ የተጠየቀዉ ሰብዓዊ ርዳታ 112 ሚሊዮን ዶላር ነዉ። ግን የኛ የገንዘብ ርዳታ በአሁኑ ሰዓት 72 ሚሊዮን ዶላር ነዉ። ተጨማሪ ሃብቶች በጣም ያስፈልጋሉ። አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ በጣም ኢየለገሱ ናቸው።»

ለጋሽ አገሮች በሚፈለገዉ መጠን የሰብአዊ ርዳታዉን ለማድረግ ወደ ኋላ ያሉበት ምክንያት ለምን ይሆን ለሚለዉ ጥያቄ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጂሊያን ሜልሶፕ ሲመልሱ፣ «ለጋሽ አገሮች ድጋፍ ለመስጠት ወደ ኋላ ያሉ አይመስለኝም። ግን ለጋሽ አገሮች ለሰብአዊ ርዳታ የሚመድቡት ገንዘብ በየቦታዉ ላለዉ ሰብአዊ ቀዉስ ስለሚከፋፈል ነዉ። በኢትዮጵያ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በጣም ቡዙ ነው። እውነቱን ለመናገር ብዙ ገንዘብ ያስፈልገናል። መንግስትም ሆነ ለጋሽ አገሮች የተፈናቀሉትን ለመርዳት የተቻላቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።»

በክረምት ወራት በአገሪቱ ሊከሰት በሚችል የጎርፍ መጥለቅለቅም 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ይጎዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በዘገባዉ ተጠቅሷል። ይህም የተፈናቃዮቹን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች መሠረታዊ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ሰብዓዊ ፍላጎት ለማሟላት በቂ አይደለም ስሉ የኬር እንቴርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ምክትል ተጠሪ ፍሬድ ማክሪ ባለፈዉ ሳምንት ለሮይቴርስ አስተያየታቸዉን ፅፈዋል። እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ርዳታ እንዲለግስ ጠይቀዋል።

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ