1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማዞኖች: የዳሆሜ ሴት ተዋጊዎች

Rodrigue Guezodje
ሐሙስ፣ ግንቦት 19 2013

ዳሆሜ ( በዛሬይቷ ቤኒን) ይገኝ የነበረ በአፍሪቃ በጣም ጠንካራ ሥርወ መንግሥት ነው። 15 ነገስታት ተፈራርቀውበታል። ነገር ግን በንጉሳዊ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ስለ ሴቶች ኮታ እንብዛም የለም። አሁን ላይ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሴቶች መሳተፋቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። አንዲት ሴት እንደውም ሥርወ መንግሥቱን መርተዋል።

https://p.dw.com/p/3tiP8
African Roots | Dahomey-Amazonen | Porträt

የመጀመሪያዋ የዳሆሜ አማዞን ማን ነበሩ?
እንደ የታሪክ ምሁር ቢያንቬኑ አኮሀ ከሆነ የመጀመሪያዋ አማዞን ታሲ ሀንግቤ ናቸው። እሳቸውም የዳሆሜ ሥርወ መንግሥት መስራች የሆኑት የንጉስ ሁዊግባጃ ሴት ልጅ  እና የንጉስ አካባ መንትያ እህት ናቸው። ሀንግቤ ከወንድማቸው ሞት በኋላ  እጎአ በ 1708 በአደባባይ ሳይታወጅ የጦሩ አዛዥ ሆነው ተሾመዋል። በይፋ የዳሆሜ ንግሥት ተብለው የተሰየሙት ግን ከወታደራዊ ዘመቻው ሲመለሱ ነው።
ታሲ ሀንግቤ በአገዛዝ ጊዜያቸው ምን አይነት አስተዋጽዎ ነበራቸው?
ምንም እንኳን ታሲ ሀንግቤ ለሶስት አመታት ብቻ የነገሱ ቢሆንም በሴቶች ላይ ትኩረት ለመሳብ በቂ ጊዜ ነበራቸው። እሳቸውም ሴቶች አደን እንዲወጡ እና በግብርና ስራ እንዲሳተፉ ያበረታቱ ነበር። ከዚያ ቀደም በእንደዚህ አይነት ስራ የሚሳተፉት ወንዶች ብቻ ነበሩ። 
ከዚህም ሌላ የግብርናውን ዘርፍ ማዳበር እና ለሁሉም ታዛዦቻቸው በነፃ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ እንደቻሉ ይነገራል።

አማዞኖች: የዳሆሜ ሴት ተዋጊዎች

የዳሆሜ አማዞኖችን ምን የለያቸዋል?
ታሲ ሀንግቤ እንደፈልጉት መምራት እንዲችሉ ከሴቶች ብቻ የተውጣጣ ጦር ማደራጀቱ ጥሩ እንደሚሆን አመኑ። ስለሆነም አማዞን በመባል የሚታወቁትን የሴት ተዋጊዎች አደራጁ። ቡድኑ በፎን ቋንቋ  አጉድጂዬ ይባላል። ትርጓሜውም ንጉሱ ዘንድ ከመደረሱ በፊት መታለፍ ያለበት የመከላከያ ኃይል እንደማለት ነው። »  አማዞኖች የተመለመሉት እና የሰለጠኑት ገና በልጅነት እድሜያቸው ነው። ይህ ትጋታቸውም ከወንዶች የበለጠ ቀልጣፋ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ግዛታቸውን ሲያስፋፉ የሚቃወሟቸውን ማንኛውንም ሰው አንገቱን ከመቅላት ወደኃላ የማይሉ እና ርህራሄ የሌላቸው እንደነበሩ ይነገራል።  ከታሲ ሀንግቤ የተወሰኑ አሥርተ አመታት በኋላ ንጉስ ጌዞ የዳሆሜ ንጉስ ሆኑ። እሳቸውም አማዞኖችን ከጎናቸው ማድረጉ ጥቅም እንደሚኖረው ወዲያው ተረዱ። በዚያን ወቅት  የቡድኑ መሪ ሴህ ዶንግ ሆንግ ቤህ የተባሉ ወጣት ሴት ነበሩ።  እርሳቸውም ወደ ብራዚል በባርነት የሚሸጡ እስረኞችን ለንጉሱ ያቀርቡ ነበር። በምትኩ ደግሞ የጦር መሣሪያ፣ ትምባሆ እና መጠጥ ያገኛሉ። ይህ ንግድ ትርፋማ ስለነበረ የዳሆሜ ሥርወ መንግሥትን ማጠናከር ተችሏል። 
የዳሆሜ አማዞኖች የታሪክ ቅርስ ምንድን ነው?
እጎአ በ 1882 ንጉስ ቤሀንዚን  የግብይት መብታቸውን ለማስጠበቅ ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ። ነገር ግን አማዞኖች በደንብ የታጠቀውን የፈረንሳይ ኃይል መቋቋም አልቻሉም። ስለሆነም ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸው ተሸነፉ። ዛሬ የጦር ወንጀል የሚባል አይነት ወንጀሎችን እንደፈፀሙ የሚነገረው አማዞኖች እንደዛም ሆኖ  የሴቶች የደፋርነት እና የማጎልበቻ ምልዕክት ተደርገው ይታያሉ። ከዚህም ሌላ ለረዥም አመታት ተዘንግተው ለነበሩት ታሲ ሀንግቤ ማስታወሻ እንዲሆን በቤኒን ታሪካዊ ከተማ አቦኒ ውስጥ ቤተ መዘክር እየተገነባ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የታሲ ሀንግቤ ተወላጆች እኝህን ሴት በሙዚቃ ድግሶች እና ውዝዋዜ ያወድሳሉ። 

የዳሆሜ አማዞኖች

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።