1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ነውጠኞቹ የአልጄሪያውያን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች በፈረንሳይ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2011

ትላንት ምሽት የተጠናቀቀው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በፈረንሳይ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ ሰንብቷል። ፈረንሳይ ቀድሞ በቅኝ ግዛት ይዛቸው የነበረቻቸው አልጄሪያ እና ሴኔጋል ለትላንቱ ፍጻሜ ውድድር መድረሳቸው የዋንጫ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል። የአልጄሪያውያን ደጋፊዎች ነገርም ፈረንሳውያንን አሳስቦ ነበር።

https://p.dw.com/p/3MQVD
Ägypten Africa Cup of Nations 2019 | Finale Algerien gegen Senegal | Jubel
ምስል Reuters/B. Tessier

ነውጠኞቹ የአልጄሪያ ደጋፊዎች በፈረንሳይ

በግብጽ አስተናጋጅነት ላለፉት 29 ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ትላንት ምሽት ካይሮ ላይ ሲጠናቀቅ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል። አልጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው ከ29 ዓመታት በኋላ ነበር። 

አልጄሪያውያን የፍጻሜው ተጋጣሚ በነበረው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ላይ ገና ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ድንገት ያስገቡት ግብ ከረጅም ዓመታት ድልን እንዲቀዳጁ አድርጋቸዋለች። ድሉ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውጥረት ላይ ለከረሙት አልጄሪያውያን ከፍተኛ ደስታን ያጎናጸፈ እንደሆነ ተነግሯል። በፈረንሳይ ፓሪስ እና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ አልጄሪያውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተው አድረዋል።የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ለግማሽ ፍጻሜ ማለፉን ተከትሎ በፈረንሳይ የሚገኙ የተወሰኑ የቡድኑ ደጋፊዎች ረብሻ በማስነሳታቸው የፈረንሳይ ፖሊስ የትላንትናውን ጨዋታ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ አስገድዶታል። ስጋት ውስጥ የገባው የፈረንሳይ ፖሊስ በተለያዩ ከተሞች የጸጥታ ኃይሎችን አሰማርቷል። የሀገሪቱ ፖሊስ ትላንት ምሽት ረብሻ ለመፍጠር ሞክረዋል ያላቸውን 200 የሚጠጉ ደጋፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስታውቋል።

Ägypten Africa Cup of Nations 2019 | Finale Algerien gegen Senegal | Jubel
ምስል Reuters/S. Salem

በፈረንሳይ መነጋገሪያ ስለሆኑት የአልጄሪያ ደጋፊዎች የፓሪሷ ዘጋቢያችን ሃይማኖት ጥሩነህ ያጠናቀረችውን ሙሉ ዘገባ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ሃይማኖት ጥሩነህ

ተስፋለም ወልደየስ