1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት ያላገኘዉ በቤንሻንጉል የቀጠለዉ ግድያ

ሐሙስ፣ ኅዳር 10 2013

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በንፀሀን ዜጎች ላይ የሚፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ትኩረት አላገኘም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት በበኩሉ በመተከል ዞን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በታጣቂዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/3lYuW
Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

በሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ሊቆም አልቻለም

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በንፀሀን ዜጎች ላይ የሚፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ትኩረት አላገኘም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት በበኩሉ በክልሉ መተከል ዞን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በታጣቂዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብሏል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ በዞኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀመው ተደጋጋሚ ጥቃት አካባቢውን የትርምስ ቀጠና እንዳያደርገው ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡።

መንግስት ትኩረቱን በትግራይ ክልል ባለው ህግ የማስከበር ስራ ላይ በማድረጉ በክልሉ በሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ሊቆም አልቻለም ይላሉ፡፡ ታጣቂዎች መረጃ ቶሎ ስለሚደርሳቸው ካሉበት ቦታ በፍጥነት ወደሌላ ቦታ ይዛወራሉ ያሉት አስተያየት ሰጪው የክልሉ መንግስት በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮችን መፈተሸ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር በመተከል የትራንስፖርት አገልግሎት መቆሙንም አብራርተዋል፡።

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ሰላማዊ በሆኑ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ከስጋት በመነሳት አካባቢያቸውን ለቀው ጫካ መግባታቸውንም አስረድተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዝብ ደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋሳ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነና እስካሁንም 20 ታጣቂዎች ተገድለዋል፣ 11 ደግሞ ተማርከዋል ብለዋል።

በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የዓለም አቀፍና የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያም በበኩላቸው በመተከል በኩል ያለው አቃቂ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት በጊዜ በቁጥጥር ስር ካልዋለ በሌሎች አካባቢዎች ከሚታዩ ግጭቶች ጋር ተዳምሮና አድጎ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ይወስደናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። የአማራ ክልል መንግስት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጠን ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።


ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ