1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ቴክኖሎጂን ለግብርና መጠቀም በኡጋንዳ እና ቡርኪናፋሶ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2011

በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለማቃለል ቴክኖሎጂን ከግብርና ጋር ለማጣመር ይጥራሉ። በኡጋንዳ ያለች የኮምፒውተር ባለሙያ የተክል ተባዮች እና በሽታዎችን ለመከላከል የሚያግዝ መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ለአገልግሎት አውላለች። በቡርኪናፋሶ ደግሞ የጠብታ መስኖ ገበሬዎች ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/35BxT
Burkina Faso Landwirtschaft
ምስል DW

ቴክኖሎጂን ለግብርና መጠቀም በኡጋንዳ እና ቡርኪናፋሶ

ዊሊያም ማቶቮ በማዕከላዊ ዩጋንዳ የሚኖሩ ቡና አምራች አርሶ አደር ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቡና ተክሎቻቸው ላይ በሚያስተውሉት ነገር ስጋት ገብቷቸዋል። በቡና ችግኞች ላይ የሚታዩ ምልክቶች ተክሎቹ በአዲስ በሽታ ሳይጠቁ አልቀረም ብለው እንዲጠረጥሩ አድርጓቸዋል። 

“አሁን እያየነው ያለው ነገር ከዚህ ቀደም በፍጹም ያልታየ ነው። በአያቶቻችን እና በአባቶቻችን ጊዜ ይታዩ እንደነበሩት የቡና ችግኝ ተባዩች አይነት አይደለም። አዲስ በሽታ ነው። የማናውቃቸውን ብዙ ነገሮች እያየን ስለሆነ መንግስት ሊረዳን ይገባል” ይላሉ ማቶቮ።  

ቡና ኡጋንዳ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ዋነኛ ምርቷ ነው። ከአፍሪካ ሀገራት ቡናን በብዛት ወደ ውጭ በመላክ ከኢትዮጵያ ለጥቃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኡጋንዳ በጎርጎሮሳዊው 2017 ብቻ 554 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘላትን የቡና ምርት ለዓለም ገበያ አቅርባለች። እንደ ማቶቮ ያሉ የቡና ገበሬዎች ችግር ሲገጥማቸው በሀገሪቱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የተገነዘበችው ወጣቷ ሜሪ አራች መፍትሄ ያለችውን አበጅታለች። ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ያጠናቸው ሜሪ ገበሬዎች በተክሎቻቸው እና አዝመራዎቻቸው ላይ ችግር ሲከሰት የሚያሳውቁበት መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ሰርታ ለአገልግሎት አውላለች። መተግበሪያውን ኢዚ አግሪክ የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች። “ተክሎች እና እንስሳትን በማጥቃት የሚታወቁ ሁሉንም ተባዮችን እና በሽታዎችን ከሰበሰብን በኋላ በቀላሉ እንዲገኙ አንድ ላይ አድርግናቸው። ስለ እነሱ ማንበብ ወይም ፎቶዎችን መመልከት ትችላለህ። የበሽታዎችን ምልክቶችን ማየት እና ህክምናውን ማግኘት ትችላለህ። ምልክቶቹን በቅጡ መረዳት ካቃተህ ደግሞ የአግሮኖሚስት ባለሙያችንን መገናኘት ትችላለህ” ትላለች ሜሪ።  

Indonesien Kaffee aus Exkrementen von Fleckenmusangs Alamid-Bohnen
ምስል Getty Images/N. Loh

በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የምትኖረው ሜሪ የማቶቮ ማሳ ከሚገኝበት 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ብትገኝም ውሎዋ ከገበሬዎቹ የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመተነትን የተጣበበ ነው። እርሷና በሙያው የተካኑ ባልደረባዎቿ ለየችግሮቹ መፍትሄ ያፈላልጋሉ። መፍትሄውን ያገኙ ጊዜም ገበሬዎቹን የሚያማክር ባለሙያ ወደ ቦታው ይልካሉ። የቡናው ነገር የሚያሳስባቸው ማቶቮም በዚህ አይነት መልኩ ችግሩ እንደሚቀረፍላቸዉ ተስፋ አላቸዉ። “በፊትም ቢሆን ቡናችንን እንከባከባለን።ነገር ግን አሁን ይበልጥ እንክብካቤ እያደረግን እንገኛለን። ምርት ጨምሯል፤ ክብደቱም እንደዚያው። ይህን ቴክኖሎጂ ውጤት ያላገኙ ገበሬዎች ብዙ ነገር ጎድሎባቸዋል። በተዘዋዋሪ መንገድ ያጡትን ነገር አያውቁትም” ይላሉ አርሶ አደሩ። 

ሜሪ የሰበሰበችዉ መረጃ እንደሚጠቁመዉ ከጎርጎሮሳዊው 2015 ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው የቴክኖሎጂ ውጤቷ 60 ሺህ ገደማ ገበሬዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ መተግበሪያዋ ከ500 በሚልቁ ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ መጫኑንም ትናገራለች። ገበሬዎች ኢዚ አግሪክ መተግበሪያን መረጃዎቸውን ለማጠራቀም፣ ገበያ ለማፈላለግ እንደዚሁም የግብርና ግብዓቶችን ለማግኘትም ጭምር ይጠቀሙበታል።

Kolumbien Kaffeanbau
ምስል picture-alliance/Zuma Press

“ግብዓቶችን በተመለከተ ተመሳስለው ለተሰሩት መፍትሄ አስቀምጠንለታል። በመተግበሪያው ላይ የሚገኙት ሁሉም ግብዓቶች ትክክለኛ ምርቶች ናቸው። እኛ የምንሰራው ጥብቅ የሆነ የተበላሸ ምርት የመመለስ ፖሊሲ ካላቸው ሀቀኛ አቅራቢዎች ጋር ነው። ገበሬው ግብዓቱ እንደማይሰራ ቅሬታ ካቀረበ አቅራቢውን ተጠያቂ እናደርጋለን” ስትል ሜሪ ታስረዳለች። 

ገበሬዎች እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥማቸውም ሆነ ሌላ እርዳታ ሲያሻቸው በየመንደራቸው እየተዘዋወሩ ለሚሰሩ ወኪሎች ይነግሯቸዋል። ከገበሬዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩት የእነዚህ ወኪሎች ቁጥር 450 ደርሷል። ሜሪ በኡጋንዳ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ እና የኢንተርኔት ሽፋኑም እየጨመረ ሲመጣ በርካታ ገበሬዎችን ለመርዳት ሀሳብ አላት። ገበሬዎች የተሻለ ምርት ሲያገኙ እና ገቢያቸው ሲያድግ መመልከት የሁልጊዜም ምኞቷ ነው።

ከምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ በምዕራብ አፍሪካ ወደ ምትገኘው ቡርኪናፋሶ ስንሻገር የሀገሪቱ መንግስት ገበሬዎችን እንዴት በቴክኖሎጂ እያገዘ እንደሚገኝ እንመለከታለን።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ በሚያጋጥማቸው ድርቅ አሳር መከራቸውን ያያሉ። በእነዚህ ሀገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውሃ ውድ የተፈጥሮ ሃብት እየሆነ መጥቷል። ለዚህም ይመስላል አሁን በብዙ የአፍሪካ ሀገራት በአነስተኛ መጠንም ቢሆን ውሃን በቁጠባ የመጠቀም ቴክኖሎጂ እየተዘወተረ የመጣው። ሰማንያ ስድስት በመቶው ህዝቧ በግብርና በሚተዳደርባት እና ውሃ አጠር በሆነችው ቡርኪናፋሶም እንዲህ አይነቱ ቴክኖሎጂ በመንግስት አማካኝነት ለገበሬዎች እንዲዳረስ እየተደረገ ነው።

Kenia - Eine Frau auf dem Maisfeld
ምስል CC-BY-SA-cimmyt

የቡርኪናፋሶ የግብርና ሚኒስቴር በመላው ሀገሪቱ እያስፋፋው ያለው ቴክኖሎጂ አዲስ የተፈጠረ አይደለም። ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ጥቅም ላይ እያዋለ ያለውን «የጠብታ መስኖ» ገበሬዎች ይበልጥ እንዲጠቀሙ እያበረታታ ይገኛል። ለዚህም በዋናነት የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበርን ይጠቀማል። 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚደገፉ 23 የጠብታ መስኖ ፕሮጀክቶች መካከል ማጉሌሌ በተሰኘው የሴቶች ህብረት ስራ ማህበር የሚከናወነው ይገኝበታል። የማጉሌሌ አባላት ቢባ በተሰኘችው የቡርኪናፋሶ ከተማ አቅራቢያ በቆሎ ያመርታሉ። የህብረት ስራ ማህበር አባላቱ የጠብታ መስኖ ለመጀመር የሚያስችላቸውን መስመሮች ያስዘረጉት ባለፈው ዓመት ነበር። ውጤቱን ለማየትም ብዙ መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። የማህበሩ መሪ ካድያ ቱቶ “ፕሮጀክቱ ለሴቶች ትልቅ ጠቀሜታ አለው። አሁን ተጨማሪ የእርሻ መሬቶች ማረስ ይፈልጋሉ። በማህበሩ ውስጥ 215 አባላት አለን። ያ ማለት ብዙ ነው። ያለን ማሳ ለቡድናችን በጣሙኑ ያንሳል” ይላሉ። 

የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመሩት የማህበሩ አባላት በዓመት አራቴ ምርት ያገኛሉ። ለመስኖው የሚያገግሉ ዕቃዎችን ከግብርና ሚኒስቴር የገዙት በገበያ ከሚሸጥበት 20 በመቶ በቀነሰ ዋጋ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባገኙት ሁለት ሄክታር የእርሻ መሬት ላይም አትክልቶች ማምረት ጀምረዋል። አትክልቶቹን ውሃ የሚያጠጡት የውሃ መርጫ ጀሪካን ተጠቅመው ነው።

እንዲህ ጉልበታቸውን አፍስሰው ከሚንከባከቧቸው አትክልቶች ምርት የሚያገኙት ግን በዓመት ሁለቴ ብቻ ነው። የጠብታ መስኖ ተጠቃሚ የሆነው የበቆሎ ማሳቸው በመጠን በግማሽ ያነሰ ቢሆንም በአትክልቱ ከሚያገኙት እጥፍ ያተርፉበታል። “ያን ያህል ገንዘብ ኖሮኝ አያውቅም።  አሁን ግን የልጆቼን የትምህርት ወጪ መሸፈንም ሆነ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት እችላለሁ። በዚህ ኩራት ይሰማኛል” ይላሉ ካድያ ቱቶ።

eco@africa - terra preta
ምስል DW

የቡርኪናፋሶ የግብርና ሚኒስቴር የማጉሌሌ የህብረት ስራ ማህበር የውሃ ጉድጓድ፣ በጸሀይ ብርሃን የሚሰራ የውሃ ፓምፕ እና የውሃ ማጠራቀሚያ እንዲያገኙ አድርጓል። በመላው ሀገሪቱ ተመሳሳይ ድጋፍ እያገኙ ካሉ 1300 ገበሬዎች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። ይህን መሰሉን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ድጋፍ የሚያስተባብሩት ሱሌማኔ ካቦሬ የማጉሌሌን ማህበር በወር ሁለቴ ይጎበኛሉ። ለጠብታ መስኖ የሚገለሉባቸው መሳሪያዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ። “ውሃ ማስተላለፊያ ጎማው ወይም የመስኖ ስርዓቱ ቢቋረጥ አሊያም በጸሀይ ሀይል ብርሃን የሚሰጠውን መሳሪያ ቢበላሽ በመንደር ውስጥ ጥገና ሊያከናውን የሚችል ሰው ሊኖር ይገባል። ለዚያም ነው በየአካባቢው ያሉ ሰራተኞችን ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ የምንጥረው” ሲሉ ሱሌማኔ አስተባባሪው በመንግስት በኩል ስለሚሰጠው እገዛ ያስረዳሉ። 

እንዲህ አይነት ተጨማሪ ክህሎቶች ከቀሰሙት ውስጥ ካድያ ቱቶም ይገኙበታል። ፕሮጀክቱ የእርሻ ስራቸውን እንዲያሻሽሉ ከማገዙም ባሻገር የሰጣቸውን ጠቀሜታ እንዲህ ያስረዳሉ። “ምስጋና ለመስኖው ፕሮጀክት ይሁንና ለሽንኩርቶቼ የሚሆን መጋዘን ራሴ መገንባት ችያለሁ” ይላሉ። 

የጠብታ ውሃ ቴክኖሎጂው ለካድያ ቱቶ እና ቤተሰባቸው መልካም ነገር ይዞ መጥቷል። ገበሬዋ በቴክኖሎጂው እገዛ ያመረቱትን ተጨማሪ ምርት ለገበያ ማቅረብ በመቻላቸው ገቢያቸው ደርጀቷል። የተሻለ የሚባለውን ኑሮን ምንነትም ማጣጣም ጀምረዋል።

ተስፋለም ወልየስ 

ነጋሽ መሐመድ