1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታንዛንያ ከማጊፉሊ ዘመን ልትላቀቅ ይገባል

ማክሰኞ፣ ሰኔ 29 2013

የታንዛንያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ከጆን ማጉፉሊ ድንገተኛ ሞት በኋላ ሥልጣኑን ከተረከቡ በዚህ ሳምንት 100ኛ ቀንን ደፍነዋል። ፕሬዚዳንትዋ በመንበረ ሥልጣኑ መቶኛ ዓመትን ይድፈኑ እንጂ ፖለቲካዊ ርምጃቸዉ ቀዳሚያቸዉ ይሰሩበት የነበረዉን መመሪያ ይዘዉ ነዉ እየተባሉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3vxCx
Tansania | Amtseinführung Präsidentin Samia Suluhu Hassan
ምስል AP Photo/picture alliance

ታንዛኒያ ዛሬ አዲስ ህገ መንግስት ያስፈልጋታል

የታንዛንያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ከጆን ማጉፉሊ ድንገተኛ ሞት በኋላ ሥልጣኑን ከተረከቡ በዚህ ሳምንት 100ኛ ቀንን ደፍነዋል። ፕሬዚዳንትዋ በመንበረ ሥልጣኑ መቶኛ ዓመትን ይድፈኑ እንጂ ፖለቲካዊ ርምጃቸዉ ቀዳሚያቸዉ ይሰሩበት የነበረዉን መመሪያ ይዘዉ ነዉ እየተባሉ ነዉ። ይሁንና ፕሬዚዳንትዋ ለለዉጥ እና አዲስ ርምጃን እንዲራመዱ ዜጎች አሁንም ጉጉት እንዳላቸዉ የዶቼቬለዋ ታንዛንያዊ ጋዜጠኛ ሲልቪያ ምሁዚ ሐተታ ጽፋለች።

ባለፈዉ መጋቢት ወር ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ድንገተኛ ሞትን ተከትሎ ወደ ታንዛንያ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የመጡት ሳሚያ ሶሉሁ ሀሰን ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ መጀመሪያ ካፀደቁዋቸዉ መመሪያዎች ውስጥ አንዱ በቀደምታቸዉ ፕሬዚዳንት በፕሬስ ተቋማት እና በነፃ ጋዜጠኝነት ላይ የተጣሉ እገዳዎችን ማንሳት ነበር። ፕሬዚዳንትዋ ሚዲያን በጉልበት ማገድ አንችልም ሲሉም ተደምጠዋል።

የመጀመርያዋ የምስራቅ አፍሪቃ ሴት ፕሬዚዳንት በዚህ ሰላማዊ መግለጫዉ ተወድስዋል። ሳምያ ይህን ይናገሩ እንጂ በታንዛንያ የታገዱት መጽሔቶች፤ ጋዜጦች እና ሌሎች አዉታሮች አሁንም እንደተዘጉ ናቸዉ። የሳምያ መንግሥት በታንዛኒያ አፋኝ የመገናኛ ብዙኃን ሕጎችን በመገምገም ያለ ዛቻ እና ማስፈራራት ያለ ሳንሱር ማለትም ቅድመ ምርመራ ተግባራቸውን መወጣት መቻል አለባቸዉ። ከጋዜጠኞች የሚነሱ ቅሬታዎችም መፍትሄ ማግኘት  ይኖርበታል።

ፕሬዚዳንቷ ስለ ኮሮና ወረርሽን ጉዳዮች ያላቸዉ አመኔታ እና ተቀባይነት ከቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ከማጉፉሊ በፍፁም የተለየ እና ተቀባይነት ያላቸዉ ናቸዉ።

Weltspiegel 18.03.2021 | Tansania Kariakoo | Presse, Tod John Magufuli
ምስል AFP/Getty Images

ይሁንና ታንዛኒያውያን አሁንም ሟቹ ፕሬዚዳንት ማጊፉል ባወጡት መመርያ ላይ ነዉ እየሰሩ የሚገኙት። ታንዛንያ ዛሬም የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመግታት አዳዲስ መመሪያዎችን በጉጉት እየጠበቁ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ሳሚያ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት ከሕዝባቸዉ ጋር በግልፅ መነጋገር እና ሕዝቡ ሕግጋቶችን እንዲከተሉ ማዘዝ ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ ለማጉፉሊ ታማኝነት ሳይሆን የጤና ባለሥልጣናት ይፋ ያደረጉትን ሕጎች እና መመሪያዎች ማክበር ነው።

ፕሬዚዳንትዋ ስልጣናቸዉን እንደተረከቡ በታንዛንያ በርካታ እስረኞች መለቀቃቸው እና በማጉፉሊ ስር የተነሱ በርካታ ጉዳዮችን መሰረዝ እና ማሻሻልን ተከትሎ ታንዛኒያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሕጎች ልትመለስ እንደምትችል አዎንታዊ ምልክቶች ታይተዋል።  ይህ ርምጃ መቀጠል ይኖርበታል። የክልል ባለሥልጣናት ከመጠን በዘለለ ኃይልን መጠቀም መኖር የለበትም። በታንዛንያ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የማክበር እና መብትን የማስተዋወቅ ብሎም  የዘፈቀደ እስራት እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊ ሙከራዎች ሁሉ መቆም አለባቸው።

በታንዛንያ በአሁኑ ወቅት ያለዉ ትልቁ ጥያቄ  አዲስ ህገ-መንግስትን የመመስረት ጥያቄ ነዉ። ፕሬዚዳንት ሳሚያ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መልስ መጀመርያ ኤኮኖሚያችን እናሻሽል ከዝያ ሌላዉ ጥያቅያችን ይከተላል የሚል መልስን ከሰጡ በኋላ በሃገሪቱ አዲስ ክርክርን ቀስቅሰዋል።   

ታንዛኒያ ዛሬ አዲስ ህገ መንግስት ያስፈልጋታል።  ኢኮኖሚው እስኪያድግ ድረስ አዲስ ህገ-መንግስት ከማርቀቅ የሚያግድ ነገር የለም፡፡ ታንዛኒያ ነፃነትዋን ካገኘች ከ 60 ዓመታት ወዲህ በታንዛንያ ኢኮኖሚን መገንባት የሚል ተመሳሳይ መዝሙር ሲዘመር መስማት እጅግ ያሳዝናል።

DW Kisuaheli | Sylvia Mwehozi
ምስል Sylvia Mwehozi/DW

የታንዛንያ የአሁን  ሕገ-መንግስት ዜጋዉን አያገለግልም፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎችም ውጤታማ ባለመሆናቸው ሕዝቡን ተጠቃሚ አላደረጉትም፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ለታንዛኒያ አዲስ ሕገ መንግሥትን በመስጠት ቅርሷቸዉን ሊያጠናክሩ የሚችሉበት እድል አላቸዉ።  

ታንዛኒያን ወደ ጥሩ መንገድ መልሰዉ እንደሚጓዙ አምናለሁ -እንድያም ሆኖ በጎርጎረሳዉያን 2025 ታንዛንያ ምርጫ ከማካሄድዋ በፊት ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በምርጫዉም ከተቃዋሚዉ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ ጠንካራ ተቃውሞ እና ፉክክር ሊያጋጥማቸዉ ይችላል። የፕሬዚዳንት ሳሚያ ተግዳሮቶች ብዙ ናቸው ፣ የለውጡም መንገድ ረጅም ነው፡፡ ለጊዜው የፕሬዚደንትዋ  ትልቁ ፈተና ታንዛንያን ለማስተዳደር ስላላቸዉ ችሎታ የሚታዩ ጥርጣሬዎችን ሁሉ መፍታቱ ላይ ነዉ።

አዜብ ታደሰ / ሲልቪያ ምሁዚ

ነጋሽ መሐመድ