1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታላቊ የአድዋ ድል የአንድነት ተምሳሌት

እሑድ፣ የካቲት 28 2013

የአድዋ ድል፦ አፍሪቃ በአጠቃላይ በአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎ ነጻነት እና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት ልዩ ቀን ነው። የአድዋ ድል፦ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አሰባስቦ ለታላቅ ድል ማብቃቱ በአውሮጳውያን የታሪክ ተመራማሪዎች እና ሀገር አሳሾች ጭምር በተለያየ ጊዜያት ተመስክሮለታል።

https://p.dw.com/p/3qHYO
Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«አድዋ ማለት፦ በራስ መተማመን፤ ራስን መቻል፤ ነጻነትን መጠበቅ ነው።»

«የካቲት 23 ቀን፣ 1888 ዓ.ም በግሩም ስነስርዓት የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት የማይታሰበውን ፈጽሟል። በወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ በመትመምም የጣሊያን የአፍሪቃ ቅኝ ግዛት የጦርነት ወረራንም ድባቅ መትቷል። ምሕረት አልባ በነበረው የአውሮጳውያን መስፋፋት፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን በተሳካ መልኩ አስጠብቃለች» ሲል ይነበባል ዝነኛው የታሪክ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ዮናስ፦ «የአድዋ ጦርነት፤ በዘመነ ቅርምት የአፍሪቃ ድል» በተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ ካሰፈሩት ጽሑፍ የተቀነጨበው።

የአድዋ ድል፦ አፍሪቃ በአጠቃላይ በአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎ ነጻነት እና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት ልዩ ቀን ነው። የአድዋ ድል፦ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አሰባስቦ ለታላቅ ድል ማብቃቱ በአውሮጳውያን የታሪክ ተመራማሪዎች እና ሀገር አሳሾች ጭምር በተለያየ ጊዜያት ተመስክሮለታል።

Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ይህ፦ ጥቊር ከሰው በታች ነው የሚል አስተሳሰብ በነገሰበት ዘመን፤ ጥቊር የማይታሰበውን ማድረግ እንደሚቻል ያሳየበት ድል የዓለምን ታሪክ በሚደንቅ ሁኔታ ቀይሮታል።

የአድዋ ድል፦ ኢትዮጵያውያን «ነጻ የወጣንበት» ብለው ሳይሆን በኩራት የድል ቀናችን እያሉ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሩት ታላቅ ቀን ነው። የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከጥግ እስከጥግ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተምመው በንጉሠ ነገሥት ዳግማ አጤ ምንሊክና በእቴጌ ጣይቱ ስር በአንድ ጥላ እንዲሰባሰቡ ያደረገ ታሪካዊ ክስተትም ነው። ሳምንቱ የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት የተከበረበት ልዩ ጊዜ ነው። የዛሬው የእንወያይ መሰናዶዋችን የታላቊ የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የማሰባሰቡ አንደምታ ላይ ይጠነጥናል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ፣ አቶ ኤልያስ ወንድሙ እና አቶ አቤል ዋበላ ናቸው።

Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Solomon Muchie/DW

ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ፦ ታሪክነክ በሆኑ በሃይማኖት ይልቁንም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ በፖለቲካ፣ እንዲሁም በአስተዳደርና በመሬት ይዞታ ጉዳዮች ላይ አያሌ መጣጥፎችን ጽፈዋል። የፍልስፍና ማዕርግ ጥናታቸውን ያካሄዱት የኢጣሊያን የቅኝ አገዛዝ ሥሪትን በመዳሰስ ሲሆን፣ የቄሣር መንግሥት ግንባታ ከ1935 እስከ 1941 ዓም የተካሄደው የኢጣሊያን የመሬት ሥሪት በኢትዮጵያ በመርህና በተግባር [ሲፈተሽ]፤የሚል እና ሌሎች በርካታ ጽሑፎችንም አበርክተዋል።

Äthiopien Adwa  125. Unabhängigkeitstag
ምስል Solomon Muchie/DW

አቶ ኤሊያስ ወንድሙ፦ በዩናይትድ ስቴትስ ሎስ አንጀለስ ሎዮላ ማሪማውንት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው ፀሐይ አሳታሚ ድርጅታቸው በኩል የአድዋ ድልን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ታሪክን የሚቃኙ አያሌ መጻሕፍትን በሀገሪኛ እና በውጭ ቋንቋዎች አሳትመዋል።

የመገናኛ አውታር ባለሞያ እና የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚሰጡት አቶ አቤል ዋበላ ደግሞ አዲስ ዘይቤ በተሰኘው ድረ ገጻቸው በኩል የአድዋ ድልንም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለአንባቢያችሁ ያደርሳሉ።

ሦስቱ ተወያዮች ያንጸባረቊትን ሙሉ ሐሳብ በድምፅ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ