1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሂደትና ስጋት

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2016

በ2014 ዓ.ም. ውስጥ ከምስረሰቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ በነበረው ግጭት ምክኒያት ተፈናቅለው አማራ ክልል መድረሳቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ አሁን የሚገኙበት አንደኛው ችግር የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የእርዳታ እጥረት ችግር ነው ይላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4gHRv
Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የተፈናቃዮች ስጋት

ከኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች በመልሶ ማቋቋም ሂደቱ አሁንም ስጋት እዳላቸው አስታወቁ፡፡

ከደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ መካነ ሰላም በሶስት የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት ተፈናቃዮች እንደሚሉት አሁንም ያፈናቀላቸው የጸጥታ ችግር ወደ መረጋጋቱ መመለሱ አጠራጣሪ ነው፡፡

በነዚህ የመጠለያ ጣቢያዎች አሁን ላይ አራት ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ይኖራሉ የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቋርጧል ያሉት የእርዳታ ምግብ ድጋፍ እና ክትትል ሌላው ፈታኝ የሆነባቸው ጉዳይ መሆንንም ያነሳሉ፡፡

በ2014 ዓ.ም. ውስጥ ከምስረሰቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ በነበረው ግጭት ምክኒያት ተፈናቅለው አማራ ክልል መድረሳቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ አሁን የሚገኙበት አንደኛው ችግር የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የእርዳታ እጥረት ችግር ነው ይላሉ፡፡ “አሁን የመጀመሪያው ችግራችን የምግብ እጥረት ነው፡፡  የሚመጣልን እርዳ የለም፡፡ እንደውም ለተፈናቃይ ተብሎ የሚመጣ እርዳ የለም እየተባልን ነው፡፡ እርዳታ ከመጣልን ሁለት ወራችን አልፏል፡፡ የመጠለያና ምግብ ድጋፍ ጥያቄውን ለአከባቢያችን ወረዳ ስናቀርብ መልስ የለም፡፡ አሁን በተለይም ሶስት ሰዎች በርሃብ ተጎድተውብናል” ይላሉ፡፡
ሌላው ተፈናቃዮችን ወደ ነባር ቀዬያቸው ለመመለስ ከተጀመረው ውጥን ጋር ተያይዞ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት አስተያየት ሰጪው ከዚህ ቀደም ወደ ቀዬያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች አሁንም ድረስ በብዛት መጠለያ ውስጥ መኖራቸውና ነባሩ ቀዬያቸው ወደ መረጋጋት አለመመለሱ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ “እኛ የመሄድ ፍላጎት የለንም፡፡ ነገር ግን አሁን እርዳታ እየቀረበልን አለመሆኑ ሰው እዚያው ተመልሰን ምንሆነውን ብንሆን ይሻላል የሚል ሃሳብ ይዘው ለጉዞው እየተመለሱ ነው” ም ብለዋል፡፡
ሌላው ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የተፈናቃዮች ካምፑን የተቀላቀሉት ተፈናቃይ በአስተያየታቸው አክለው፡ “እስካሁን ያገኘነውን ነግር እየተቀበልን፤ ያችኑን እየቆረጠምን ህይወታችን እና የልጆቻችን ህይወት ለማቆየት እየጣርን ነበር፡፡ እስካሁን ሲረዱን የነበሩ ድርጅቶችም ነበሩ፡፡ አሁን ግን የነሱም እርዳታ ለምን እንደተቋረጠ ለኛ ግልጽ አይደለም፡፡ በሶስት አራት ወር የሚያመጧት ያቺ እርዳታም እየተቋረጠች ነው” ብለዋል፡፡ “አሁን ተመለሱ ሲሉን ሰላሙ ባልተረጋገጠበት የአገር ማስታረቂያ ሊያደርጉን ይሆን” የሚልጥያቄ አጭሮብናልም ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፡፡
በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት ተወልደው ካደጉበትና ለ50 ኣመት ቤተሰብና ሀብት ካፈሩበት ከጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቅለው በካምፑ ውስጥ የሚገኙት ሌላው አስተያየት ሰጪም ተመሳሳይ ስጋታቸውን አከሉ፡፡ “አሁን እርዳታ እየመጣልን ስላልሆነ እንዴት እንሁን ነው፡፡ እርዳታ ሁለት ሶስት ወር እንኳ ቆይቶ መምጣት ማቆሙ አስግቶናል፡፡ የተፈናቀልንበት አገራችን ሰላም ቢሆን ወደዚያ መመለሱን ባልጠላን፡፡  አገር ሁሉ ነገር ያለበት የርሃብ ስጋት የማታሰብበት ነበር፡፡ ግን ደግሞ ከመመለሳችን በፊት ይረጋጋልን ነው እያልን ያለነው” ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ (አደጋ ስጋት መከላከል) ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢዴኤ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ዝግጁነት ቢኖረውም የተፈናቃዮች ፈቃደኝነት ላይ ግን ውስንነት አለ ብለዋል፡፡ “እኛ ለመመለስ ዝግጁ ነን፡፡ ፈቃደኝነቱ ላይ አንዳንዴ ቅድመ-ሁኔታ ማንሳት አለ፡፡ አሁን ከክልሉ ጋር ተወያይተው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን እናውቃለን” ብለዋል፡፡
በተያዘው ዓመት የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም ላይ ከተመካከሩ በኋላ 3000 ያህል ተፈናቃዮች በመንግስት ሲመለስ ቁጥራቸው ከዚያው ያላነሱ ተፈናቃዮች በግላቸው ስለመመለሳቸውም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር