1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተጠናክሮ የቀጠለው የበልግ ዝናብ ጥቅምና ተግዳሮቱ

ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2015

በኢትዮጵያ በተለይም የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አከባቢዎች ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች አስከፊ የድርቅ ጊዜያትን አሳልፈዋል ። በዘንድሮ የበልግ ወቅት ግን መደበኛ እና ከመደበኛም በላይ እጅግ ከፍ ያለ ዝናብ ማግኘታቸው የተነገረ ነው ።

https://p.dw.com/p/4RE9r
Äthiopien | Überflutung in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

በ84 የአገሪቱ አከባቢዎች ከባድ ጎርፍ አስከትሏል

በኢትዮጵያ በተለይም የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አከባቢዎች ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች አስከፊ የድርቅ ጊዜያትን አሳልፈዋል ። በዘንድሮ የበልግ ወቅት ግን መደበኛ እና ከመደበኛም በላይ እጅግ ከፍ ያለ ዝናብ ማግኘታቸው የተነገረ ነው ። እንዚህ አከባቢዎች በአሁኑ ወቅት በቂ የውኃ አቅርቦት በማግኘታቸው ለግብርና እና ለእንስሳት መኖ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ባለሞያዎች ይገልጻሉ ። ይሁንና ዝናቡ ከወትሮ ጎልቶ የተስተዋለበት የዘንድሮ በልግ ወራት በ84 የአገሪቱ አከባቢዎች ከባድ ጎርፍ ከማስከተሉም አልፎ የበዛው ዝናብ ምርት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ማስከተሉ ተሰምቷል ። 

የበልግ ወቅት ዝናብ ዋነኛ የዝናብ ወራታቸው በሆኑባቸው እና ወቅቱ ሁለተኛ የዝናብ ጊዜያቸው በሆነባቸው አከባቢዎች ዘንድሮ በእጅጉ የተጠናከረ ዝናብ ትስፋፍቶ መጣሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንቢያ እና ቅድመ ማስጠንቀቅ ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ገልፀዋል፡፡ “በተለይም በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ እንደ ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቅ አማራ፣ የአፋር ክልል፣ መካከለኛ የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም መስራቅ ኢትዮጵያ ከየካቲት 17 ጀምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው ዝናብ አግኝተዋል፡፡ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነው እንደ ደቡብ እና ደቡብ አጋማሽ የአጋራችን ክፍል ደግሞ ከየካቲት 30 ጀምሮ የተስፋፋ ዝናብ ነበራቸው፡፡”

ጎርፍ መጥለቅለቅ የደረሰባት አዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ከርቀት
ጎርፍ መጥለቅለቅ የደረሰባት አዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ከርቀትምስል Seyoum Getu/DW

የአየር ትንበያ (ሜትሮሎጂ) ባለሞያው ከሰሜን እስከ ምስራቅ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በመካከለኛ እና በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አከባቢዎች መጠኑ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ በዚሁ የበልግ ወራት ውስጥ መጣሉን አመልክተዋል፡፡ “በአፋር፣ ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቅ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ የተወሰኑ የሶማሌ ክልል እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች ባጠቃላይም 84 ያህል የአገራችን አከባቢዎች መጠኑ እጅግ የበዛ ጎርፍም ያስከተለ ዝናብ ተከስቷል፡፡”

ይህን ተከትሎ በተለይም በከተሞች አከባቢ ቅጽበታዊ ጎርፍ ተከስቷል፡፡ አዲስ አበባ ሲኤምሲ እና ቦሌ ሚካኤል በሚባሉ አከባቢዎች በተለይም የከፋ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡ ደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ሌላው የከፋ ቅጽበታዊ ጎርፍ ማስተናገዱም ተነግሯል፡፡ በዚህም በተለይም ላለፉት አምስት የዝናብ ወራት ከመደበኛ በታች የሆነ እጅግ ዝቅተኛ ዝናብ ሲያገኙ በቆዩ የኢትዮጵያ ቆላማ ስፍራዎች አሁን ላይ በቂ ዝናብ በማግኘታቸው የመስኖ እና ውሃ አቅርቦት በእጅጉ መሻሻሉ ነው የተገለፀው፡፡ ይሁንና የበልግ ዝናብ ከፍ ብሎ መስተዋሎ ምርት ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው አከባቢዎችም ይገኛሉ፡፡ “የነበረው ዝናብ ከፍ ያለና በረዶም የቀላቀለ ከመሆኑ አንጻር አዝርት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳረፈበት አከባቢም ነበረ፡፡ ባጠቃላይ ግን ከቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ ተነስቶ ወደ አገራችን ሲገባ የነበረው እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ በተለይም የበልግ ዝናብን በእጅጉ ለሚፈልጉ የአገራችን አከባቢዎች በቂ ዝናብ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡”

የጎርፍ መጥለቅለቅ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተከስቷል
የጎርፍ መጥለቅለቅ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተከስቷልምስል Seyoum Getu/DW

የሜትሮሎጂ ባለሙያው ዶ/ር አሳምነው ተሾመ እንደሚሉት የተያዘውን የግንቦት ወር የሚያጠቃልለው የበልግ ወቅት ዝናብ ከደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አከባቢዎች በስተቀር በዚህ በተያዘው ወር በአብዛኛው የአገሪቱ አከባቢዎች መጠኑ እየቀነሰ እንደሚሄድ ነው የተናገሩት፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ