1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በአመጽ የሚታጀብባት ደቡብ አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 10 2013

የ79 ዓመቱ ዙማ ለፖሊስ እጃቸውን ላለመስጠት ሲያንገራግሩ ጠንካራ ይዞታቸው እንደሆነ በሚነገርለት በኳዙሉ ናታል ግዛት ደጋፊዎቻቸው ለእሳቸው ከለላ ለመስጠት መንቀሳቀስ ጀመሩ። ለቀናት በዘለቀው ዘረፋ እና የንብረት ቃጠሎ፤ ከ200 የሚበልጡ የገበያ ማዕከሎች ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል፤ ከ500 የሚበልጡ መጋዘኖች ተቃጥለዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

https://p.dw.com/p/3waz9
Südafrika, Durban | Brennendes Warenhaus nach Ausschreitungen
ምስል Rogan Ward/REUTERS

በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የነበረው የአፓርታይድ ሥርዓትን ዘረኝነት በመቃወማቸው ለ10 ዓመታት ታስረዋል። ቀጠሉና በዚሁ የዘመን ቀመር በ1975 ዓ,ም ከሀገራቸው ተሰደዱ። በስደት ዓለም የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በእንግሊዝኛው ምህጻሩ ANC የስለላ ኃላፊ ሆነው ቆዩ። ከ16 ዓመታት የስደት ቆይታ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ተመለሱና ውለው አድረው በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ለሀገሪቱ ፕሬዝደንትነት በቁ። የነጻነት ታጋዩ ጄኮብ ዙማ በፕሬዝደንትነት ዘመናቸው ነበር ከሙስና ጋር በተገናኘ ስማቸው መጠልሸት የጀመረው። ከፕሬዝደንትነታቸው ቀደም ብሎ በ2005 ዓ,ም የቤተሰባቸው ጓደኛ የሆኑ ሴትን አስገድዶ በመድፈር ክስ ቀረበባቸው፤ ሆኖም በዓመቱ ክሱ ተቋረጠ። በዚሁ ዓመት በጎርጎሪዮሳዊው 1999 ፈጽመውታል በተባለ ከጦር መሣሪያ ንግድ ውል ጋር የተያያዘ የሙስና ወንጀልም ተከሰው ነበር፤ ነገር ግን ክሱ ተቋርጦ ከአራት ዓመታት በኋላ ዙማ የሀገሪቱ መሪ ሆኑ። በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም ፍርድ ቤት የመንግሥትን ገንዘብ የግል መኖሪያ ቤታቸውን ለማሳደስ በማዋል ሀገርን በታማኝነት ለማገልገል የገቡት ቃል አፍርሰዋል ሲል ጥፋተኛ አላቸው። እሳቸውም የመንግሥትን ገንዘብ መለሱ። ሆኖም ከ15 የሚበልጡ ከሙስና ጋር የተገናኙ ጥፋቶችን ዘርዝሮ ክስ መሥርቶባቸዋል። በተለይም በደቡብ አፍሪቃ በንግዱ ዘርፍ በስፋት ከተሰማራው የጉብታ ቤተሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት በማመልከት አቃቤ ሕግ ምርመራ እንዲካሄድ አጥብቆ ሲጠይቅባቸው ቆይቷል። የዛሬ ሦስት ዓመትም የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ የአቃቤ ሕግ ባለሥልጣን ዙማ ማጭበርበር እንዲሁም ሁለት የሙስና ጉዳይ ያካተቱ 12 ክሶችን አቀረበባቸው። ዙማ የተከሰሱበትን በሙሉ አልፈጸምኩም ሲሉ ክደዋል። ባለፈው ወር ፍርድ ቤት ቀርበው በክሶቻቸው ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠሩ አሻፈረኝ በማለታቸው የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው።  

Südafrika , Durban | Plünderungen nahe eines brennenden Warenhauses
ምስል Rogan Ward/REUTERS

የ79 ዓመቱ ዙማ ለፖሊስ እጃቸውን ላለመስጠት ሲያንገራግሩም ጠንካራ ይዞታቸው እንደሆነ በሚነገርለት በኳዙሉ ናታል ግዛት ደጋፊዎቻቸው ለእሳቸው ከለላ ለመስጠት መንቀሳቀስ ጀመሩ። ተቃውሞ በአመጽ በሚታጀብባት ደቡብ አፍሪቃ የደጋፊዎቻቸው እንቅስቃሴ ያሳሰባቸው የመሰሉት ዙማ በማግስቱ እጃቸውን ለፖሊስ በፈቃዳቸው ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስነገሩ። በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጾች መሠረት የእስራት ጊዜያቸው ሊቀነስ እንደሚችል ተስፋ ቢያደርጉም የእሳቸው ደጋፊዎች የቀሰቀሱት ተቃውሞ ያስከተለው ጥፋት እና ውድመት ያንን የማግኘት ዕድላቸውን ጠባብ እንዳደረገው የሕግ ባለሙያዎች ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።

ጄኮብ ዙማ ከታሰሩ በኋላ በቶሎ እንዲለቀቁ የተመኙት ደጋፊዎቻቸው የደቡብ አፍሪቃን የኤኮኖሚ የደም ስሮች የሚባሉ ወሳኝ መንገዶችን በመዝጋት በኳዙሉ ናታል እንዲሁም የኤኮኖሚ ወደብ በሆነችው ጓተንግ ግዛት በግለሰብ እና መንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል። የሀገሪቱ ፖሊስ አመጹን የቀሰቀሰው በትዊተር የተሰራጨ የሀሰት መረጃ ነው በሚል እያጣራ ነው። በተለይም የዙማ ሴት ልጅ ዱዱዚሌ ዙማ ግንባር ቀደም ተጠርጣሪ መሆኗን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። በዚህ ወቅትም ለቀናት በዘለቀው ዘረፋ እና የንብረት ቃጠሎ የደቡብ አፍሪቃ የድርጅት ባለቤቶች ማሕበር ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ይፋ እንዳደረገው፤ ከ200 የሚበልጡ የገበያ ማዕከሎች ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል፤ ከ500 የሚበልጡ መጋዘኖች ተቃጥለዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአልክሆል መጠጥ ኢንደስትሪው በአመጹ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው በኩዋ ዙሉ ናታል እና ጉዋንግ ግዛቶች ብቻ ከ200 የሚበልጡ የመጠጥ መሸጫ መደብሮች መዘረፋቸውን አስታውቋል። ትላልቅ የንግድ ተቋማት እንደ ሚስተር ፕሪንስ ያሉ ታዋቂ የልብስ መሸጫዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ መጋዘኖቻቸው ሙሉ በሙሉ በመዘረፋቸው ለጊዜው ለመዝጋት መገደዳቸው ተሰምቷል። 

Südafrika Ausschreitungen Zuma Soldaten
ምስል Themba Hadebe/AP Photo/picture alliance

አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በአነስተኛ፣ በመካከለኛ እና በጥቃቅን የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ለፍቶ አዳሪዎች የመድህን ዋስትና የሌላቸው በመሆኑ የመንግሥት ሥልጣናቸውን በኃላፊነት ስሜት በአግባቡ  ባለመጠቀማቸው የተከሰሱት ዙማ ደጋፊዎች ባነሱት አመጽ የደረሰባቸውን ኪሳራ የሚያካክሱበት መንገድ ግልጽ አይደለም።

«እኛ አነስተኛ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማራን ወገኖች ማንም ዋስትና ሊሰጠን አይፈልግም» ይላል ከፍተኛ ስጋት ባለበት አካባቢ እንደሚኖር የሚገልጸው ኦኩይ ዑቼንዱ። ጆሃንስበርግ የሚኖረው የመኪና ሻጭ ባለፈው የውጭ ዜጎች ጥላቻ መዘዝ አገሬው ባደረሰው ጥቃት 53 መኪናዎችን አጥቷል። ይኽ ጉዳት ከደረሰበት ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ከሰሞኑ በእኩለ ሌሊት ስልክ ተደውሎለት የመኪና መሸጫው በእሳት መያያዙ ተነገረው። «የምናገረው ጠፋኝ» ይላል የ45 ዓመቱ ዑቼንዱ በእሳት ከከሰሉት 58 መኪናዎች ፊት ለፊት ቆሞ። ራሱን ለማጥፋት እስከመመኘት መድረሱን የገለጸው ነጋዴ ኑሮውን የሚመራበት በመውደሙ የሚያደርገው ጠፍቶት ተቀምጦ ከማልቀስ ሌላ አማራጭ ማጣቱን ለሮይተርስ ገልጿል። በተመሳሳይ ተሾመ ርሴ ከደቡብ ኢትዮጵያ ከከንባታ ጠንባሮ ዞን አደሮ ከሚባል ቦታ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከገባ 10 ዓመት ሆኖታል። የደርባን ነዋሪ መሆኑን የገለጸልን ተሾመም በንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። በእነዚህ ዓመታት ለፍቶ ካደራጃቸው አምስት ሱቆች ሦስቱን አጥቷል። 

Südafrika - Proteste und Gewalt nach Verurteilung von Jacob Zuma
ምስል Siphiwe Sibeko/Reuters

ወታደሮች መሰማራታቸውን ተከትሎ መረጋጋት እየታየ መሆኑ በሚነገርባት ደቡብ አፍሪቃ ሳምንት ለዘለቀው እና ከፍተኛ ውድመት ላስከተለው አመጽ በአስተባባሪነት የተጠረጠሩ 12 ሰዎች መያዛቸውን መንግሥት አመልክቷል። ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ኩዋ ዙሉ ናታል ግዛትን በጎበኙበት ጊዜም ይኽ ሁሉ አመጽ ቀድሞ የታቀደ መሆኑ እንደተደረሰበት ተናግረዋል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክፉኛ በተጠቃችው አፍሪቃዊት ሀገር በሽታው ካሳደረው ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ባሻገር በአንድ ሳምንት የደረሰውን ውድመት ለማካካስ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚነገረው። በተለይም ሱቆችና መጋዘኖችን ያወደሙ እጆች ውሎ አድሮ ገበያ ላይ የሚሸመተው ሲስተጓጎል ለሌላ አመጽና ብጥብጥ እንዳይዘረጉ ስጋታቸውን ከወዲሁ የሚናገሩ አሉ።

ሸዋዬ ለገሠ