1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በሱዳን፤ የዩጋንዳ ወታደሮች በኮንጎ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 25 2014

ሱዳን ውስጥ የጦር ኃይሉ ከመንግሥት ሥልጣን ይውጣ የሚለው የሕዝብ ተቃውሞ ቀጥሏል። የተመድ እና የአፍሪቃ ሕብረት ተቃውሞው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩሉ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አማፂ ቡድን ለመውጋት ዩጋንዳ ወታደሮቿን ልካለች። ርምጃዋ ሌሎች ጎረቤት ሃገራትን እንዳይጋብዝ ስጋት አለ።

https://p.dw.com/p/43niQ
Proteste gegen die Machübernahme des Militärs im Sudan
ምስል Marwan Ali/dpa/AP/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ

ሱዳን መረጋጋት ርቋታል። ከሁለት ዓመት በፊት ሚያዝያ ወር ላይ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሀገሪቱን የገዙት ኦማር አልበሽር በሕዝባዊ ተቃዋሞ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተሰናበቱ ወዲህ ሱዳን በወጉ መረጋጋት አልቻለችም። ወትሮም የጦር ኃይሉን በሙስና እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰው የሀገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ ከወራት በፊት ሲቪል አስተዳደር የተጣመረበትን የሽግግር መንግሥት የጦር ኃይሉ ዳግም ማስወገዱን አጥብቆ ተቃውሟል። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የተጠናከረበት ተቃውሞ ፋታ የነሳው መፈንቅለ መንግሥት ያካሄደው የጦር ኃይል በቁም እስር ያሰነበታቸውን የሽግግር መንግሥቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ቦታቸው ቢመልስም የሕዝቡ ተቃውሞ ግን አሁንም ቀጥሏል።  

በሺህዎች የሚገመቱ የተቃውሞ ሰልፈኞች ባሳለፍነው ማክሰኞ በዋና ከተማዋ ተሰባስበው ወደ ፕሬዝደንቱ ቤተ መንግሥት በመሄድ ላይ ሳሉ የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለመበተን ሞክረዋል። የህክምና ባለሙያዎች የጸጥታ ኃይሎች ሕይወት ሊያጠፋ የሚችል ኃይል ተጠቅመዋል በሚል ቢከሱም ፖሊስ በበኩሉ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ኃይል ነው የተጠቀምኩት በማለት ክሱን ውድቅ አድርጓል። የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን ከተነሱበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ቢያንስ ለ43 ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ተጠያቂ መሆናቸው እየተነገረ ነው። ሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮስም ሆነ ከፍተኛ ኃይል ከመጠቀም ጋር በተገናኘም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ የፖሊስ አዛዡን እና ምክትላቸውን በዚህ ሳምንት ከኃላፊነት ማሰናበታቸው ተሰምቷል። ካለፉት ጊዜያት በተለየም ባለፉት ቀናት ፖሊሶች ለተቃውሞ በቤተመንግሥት አካባቢ የተሰባሰቡ ዜጎችን በመግረፊያ ሲያሳድዱ ታይተዋል። በሱዳን ከተሞች አደባባይ የሚወጡት ሰልፈኞቹ «ጉድኝት የለም፤ ድርድር የለም፣ ሕጋዊነት የለም» የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት የጦር ኃይሉ ከሲቪል አስተዳደር እጁን እንዲያወጣ አጥብቀው በመጠየቅ ላይ ናቸው።      

Proteste gegen die Übergangsregierung im Sudan
በሱዳን የቀጠለው የህዝብ ተቃውሞምስል El Tayeb Siddig/REUTERS

የሱዳን ከፍተኛው ጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሀን ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክን የቁም እስረኛ በማድረግ የመንግሥት ሥልጣንን ለጥቂት ሳምንታት ለመያዝ ሞክረዋል። ለአንድ ወር ርምጃቸውን አጥበቀው ከተቃወሙ ወገኖች ጋር የገቡበትን ፍጥጫ ያረገበው ሀምዶክን በስምምነት ወደ ቦታቸው መመለሳቸው ነበር። ምንም እንኳን የውጭ ኃይሎች ርምጃውን በአዎንታዊነት ለመመልከት ቢሞክሩም ስምምነቱ ቀደም ሲል ለሽግግር መንግሥት ምሥረታ ያበቃውን ውል የጣሰ ነው በሚል ሱዳናውያን አልተቀበሉትም። ሀምዶክ ከመፈንቅለ መንግሥት መሪዎች ጋር ባደረጉት ስምምት ጦር ኃይሉ ሉአላዊ ምክር ቤቱን እንዲቆጣጠር እንዲሁም በባለሙያዎች የተዋቀረውን ካቢኔም በቅርበት እንዲከታተል ፈቅደዋል። ሆኖም ይኽን ውል እሳቸውን የዛሬ ሁለት ዓመት ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ለኃላፊነት የመረጣቸው የነጻነት እና ለውጥ ኃይሎች የተባለው የፓርቲዎች ስብስብ አልተቀበለውም።  እንደውም ሀምዶክን እንደ ከሀዲ አስቆጥሯቸዋል። ይኽም ሱዳናውያንን ከየቤታቸው በየዕለቱ በቁጣ ወደ አደባባይ እንዲወጡ እና ሀገሪቱም ሰላም እንዲርቃት ማድረጉ እየታየ ነው።  

የቀጠለው የሱዳን ተቃውሞ ያሳሰባቸው የተመድ እና የአፍሪቃ ሕብረት በሀገሪቱ የተጀመረው የዴሞክራሲ ሽግግር ፈር እንዲይዝ ሕዝቡና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ተቃውሞውን አቁመው በጦሩ ጀነራሎች እና በሀምዶክ መካከል የተደረሰውን ስምምነት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል። ኒውዮርክ ላይ ከሚካሄደው አምስተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት እና የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ጎን ለጎን የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እና የአፍሪቃ ሕብረቱ ሞሳ ፋኪ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በስምምነቱ መሰረት በ18 ወራት ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ የተወሰነውን ለማጽናት ማቻቻል ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የአፍሪቃ የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤትም ወደ ኻርቱም በመሄድ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ከሚሳተፉ ልዩ ልዩ አካላት ጋር የሽግግር ሂደቱን አጠናቅቆ ምርጫ ወደማካሄድ የሚያደርስ ማግባቢያ ለማመቻቸት እንደሚወያዩም ሙሳ ፋኪ ጠቁመዋል። አክለውም፤  

Moussa Faki Afrikanische Union
የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪምስል Mahmoud Hjaj/picture alliance/ AA

«ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ ሱዳን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የታጠቀው ክፍል፣ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ክፍሎች፤ ወደ አንድ መድረክ መጥተዋል፤ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ደግሞ ሊባክን አይገባም የሚል እምነት አለኝ።» 

ነው ያሉት። ጉተሬሽ በበኩላቸው የሱዳን ህዝብን ስሜት እንደሚረዱ በመግለጽ ምንም እንኳን የተደረገው ውል እንከን አልባ ነው ባይባልም ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር የተሳካ እንዲሆን ስለሚያግዝ እንዲቀበሉት ጠይዋል።  ስምምነቱን ውድቅ ማድረጉም ለሱዳን መረጋጋት አደጋ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ለሱዳን ሕዝብ እና ለተለያዩ ኃይሎች ባቀረቡት ጥሪም በቀጣይ ርምጃዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክን በመደገፍ ሱዳን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ እንድትሸጋገር እንዲያደርጉም ተማጽነዋል።  

ዋና ከተማ ኻርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የሱዳን ከተሞች በሚካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ የሀገሪቱ ዜጎች ግን አሁንም ጥያቄያቸው አንድ ነው። 

«ለእኛ የጦር ኃይሉን ከፖለቲካው ሜዳ አውጥቶ ወደ ሲቪል ሕይወት የማያስገባ ማናቸውም ስምምነት ተቀባይነት የለውም። የጦር ኃይሉ ወደ ምሽጉ እንዲመለስ እንፈልጋለን። ሥልጣን የሕዝብ ነው፤ የጦር ኃይሉ ደግሞ ወደ ምሽጉ መመለስ አለበት።» 

Demonstrantin im Sudan
ምስል DW

ነው የምትለው ከሰልፈኞቹ አንዷ ወጣት። ተቃዋሚዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክም ከሽግግር መንግሥቱ ሥልጣን በኃይል አንስቶ ከሳምንታት የቁም እስር በኋላ ወደ ቦታቸው በመለሷቸው ጀነራሎች ሃሳብ ተስማምተው የሚቀጥሉ አይመስልም። ሮይተርስ የቅርብ ምንጮቼ ነገሩኝ እንዳለው ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው ተመልሰው በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ የሚቆዩት የዛሬ ሁለት ዓመት ከተደረገው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የተደረሰው ስምምነት በሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ እና ይኽም በተለያዩ የፖለቲካ ክፍሎች ተቀባይነት ካለው ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።  

 

ዩጋንዳ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ወታደሮች ማስገባቷ 

በተፈጥሮ ማዕድን ሀብት የታደለችው ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ የበርካታ ታጣቂ ኃይሎች መፋለሚያ በመሆንም ትታወቃለች። በተለይ ኮንጎ በምሥራቃዊ  የሀገሪቱ ክፍል ያላት የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ለዜጎቿ ከበረከቱ ይልቅ መርገምነቱ ከፍቶባቸዋል። በዚህ አካባቢ በስፋት የሚንቀሳቀሰው የዩጋንዳ መንግሥት ተቃዋሚ የሆነው የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በእንግሊዝና ምህጻሩ ADF የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ማድረሱ በየጊዜው ይዘገባል። በጎርጎሪዮሳዊው 1990 ዓ,ም የተለያዩ የዩጋንዳ ታጣቂ ቡድኖች ተሰባስበው የመሠረቱት ADF አሜሪካ እንደምትለው እራሱን እስላማዊ መንግሥት ከሚለው የሽብር ቡድን ጋር ይፋዊ ትስስር አለው። ቡድኑ በተመሠረተ በአምስት ዓመቱ መንቀሳቀሻ ስፍራውን ከዩጋንዳ ወደ ምሥራቃዊ የኮንጎ ግዛት ሩዋንዞሪ ተራሮች ለወጠ። IS ከታጣቂው ቡድን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳየት ሲልም ከዛሬ ሁለት ዓመት ጀምሮ የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማወጅ ጀምሯል።  ADF በተጠቀሰው አካባቢ ሰሜን ኪቩ እና ኢቱሪ ክፍለ ሃገራትም እንቅስቃሴውን አስፋፍቶ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ግዛቶቹን በከበባ ውስጥ ከትቷል እየተባለ ነው። ሁኔታው ያሰጋው የኮንጎ መንግሥት የአካባቢውን የመንግሥት ሲቪል ሠራተኞች በወታደራዊ መኮንኖች ለመተካት መገደዱም ነው የተሰማው። ባሳለፍነው ሳምንትም ቡድኑ  ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር ከ20 በላይ የሚሆኑትን መግደሉ ተነግሯል። በዚህ ጊዜም የኮንጎ ፕሬዝደንት ፊሊክስ ቼሴኬዴ የዩጋንዳ መንግሥት ወታደሮቹን እንዲያስገባ ፈቃድ መስጠታቸው ተሰማ። የዩጋንዳ ወታደሮችን ወደ ኮንጎ መግባት ግን ሩዋንዳ ዝም ብላ ትቀበላለች ማለት እንዳይደለ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የቤኒ ግዛት ነዋሪው አውግስቲን ካምባሌ ሌላ የጦርነት ግንባር እንዳይከፈት ይሰጋል። 

Afrika, Mount Stanley
በዩጋንዳ እና ዴሞክታሪክ ኮንጎ ድንበር አካባቢው የሚገኙት የሩዋንዞሪ ሠንሰለታማ ተራሮችምስል Getty Images/P. Martell

«የዩጋንዳ ወታደሮች ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ቢገቡ ሩዋንዳ ደግሞ ወደግዛታችን የራሷን ወታደሮች መላኳ አይቀርም። ስጋቴ ደግሞ በእኛው ግዛት ሁለቱ ሃገራት ሌላ የጦር ግንባር እንዳይከፍቱ ነው።»  

የካምባሊ ግምት መነሻ አለው። በጎርጎሪዮሳዊው 2000 ዓ,ም የሩዋንዳ እና የዩጋንዳ መደበኛ ሠራዊቶች በሰሜናዊ ምሥራቅ በማዕድን በበለጸገችው ኪሳንጋኒ በተባለችው የኮንጎ ግዛት በባድ መሣሪያ ተታኩሰው በርካቶች ተገድለዋል በመቶዎች የሚቆጠሩም ተጎድተዋል። በዚያም ላይ የተመ ተቋማት እና የርዳታ ድርጅቶች በየጊዜው ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ ምሥራቃዊ ጎንጎ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ በሚል ይከሷቸዋል። ዩጋንዳ በቅርቡ በግዛቷ ለደረሱ ሁለት የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች ADFን ተጠያቂ አድርጋለች። ሩዋንዳ በበኩሏ ባለፈው ጥቅምት ወር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ጥቃት ለማድረስ አቅደው ነበር ያለቻቸውን 13 የADF አባላት አስሬያለሁ ብላለች። የሁለቱ ሃገራት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የውስጥ ጉዳይ መነካካት መፍትሄ ሳያገኝ የዩጋንዳ ጦር ወደዚያ መግባት የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ እንዳያናጋው ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የጸጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ስቴፋኒ ዋልተርስ ስጋት አላቸው። 

Afrika Uganda Edward Katumba Wamala
ምስል AFP via Getty Images

«ይኽ ሊሆን የሚችልበት አማራጭ ሰፊ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ ግንኙነት በጣም ተበላሽቷል፤ ሁለቱ ሃገራት በኦኮኖሚ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በበርካታ ምክንያቶች ኮንጎ ውስጥ በጠላትነት ነው ስለሚተያዩ ይኽ ዋናው ስጋት ነው።» 

በዚህ መሀል ግን የዩጋንዳ ወታደሮች ወደ ምሥራቃዊ የኮንጎ ግዛት ገብተው በአየር እና በምድር ጥቃት መክፈታቸው ተሰምቷል። ለሁለት ዓመታት በቡድኑ ላይ ጥቃት ከፍተው ምንም ውጤት ያላገኙት የኮንጎ ባለሥልጣናትም ከዩጋንዳ ጦር ጋር በመሆን ቡድኑን ለመውጋት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። በአንጻሩ የዩጋንዳ ወታደሮች በአካባቢው ለምን ኃይል ጊዜ እንደሚቆዩ ግልጽ አይደለም የሚሉ ዜጎች አሉ። በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም የሰላም ኖቤል የተሸለሙት የዴሞክራቲክ ኮንጎ የማህጸን ዶክተር ዴኒስ ሙክውጌ በኮንጎ እና በዩጋንዳ መካከል የተደረገው ይኽ ስምምነት ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት። ለ25 ዓመታት የዘለቀ የጅምላ ወንጀል እንዲሁም የሀብት ዝርፊያ በጎረቤቶቻችን ተፈጽሟል ሲሉም ቅሬታቸውን በትዊተር ገጻቸው አስነብበዋል። ሌሎች ታዋቂ የሀገሪቱ ዜጎችም እንዲሁም ምክር ቤት ሳይስማማበት ሌላው ቀርቶ ቼሴኬዴ በይፋ ሳይናገሩ መደረጉ ግልጽነት ይጎድለዋል ሲሉ ተችተዋል። የመንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ ግን በሃገራት መካከል ግንኙነቶች እንደሚሻሻሉ ጠቁመው የዜጎቻቸውን ስጋት ቢረዱትም ወደፊለት መራመድ መምረጣቸውን ገልጸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ