1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

«ተስፋ ሰጪ» የማሽላ ምርምር 

ረቡዕ፣ ጥር 13 2012

የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር የሀገር በቀል እዉቀቶችንና ፈጠራዎችን  ጥቅም ላይ ለማዋል ሁሉንም ባይሆን የተወሰኑትን በመደገፍ ላይ ይገኛል።ምንስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ ካደረገላቸዉ ሀገር በቀል ፈጠራና ምርምሮች መካከል አቶ ታለጌታ ልዑል የተባሉ የግል ተመራማሪ ያደረጉት የማሽላ  ምርምር አንዱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3WeGD
Äthiopien Addis Ababa Science and Technology Universität Maisforschung
ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology

አዲስ የተገኘዉ የማሽላ ዘር

 


በኢትዮጵያ በግል ከሚደረጉ ሀገር በቀል ፈጠራና ምርምሮች መካከል አቶ ታለጌታ ልዑል የተባሉ የግል ተመራማሪ ያደረጉት የማሽላ  ምርምር አንዱ ነዉ። ይህ የማሽላ ምርምር ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች የተግባር ሙከራ የተደረገበት ሲሆን አንዴ ተዘርቶ  በአመት እስከ ሶስት ጊዜ ምርት የሚሰጥ መሆኑንን ለግለሰቡ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኔዉ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር ገልጿል። 

ይህ የማሽላ ምርምር ከዚህ ቀደም በሁለት ቦታዎች የተግባር ሙከራ የተደረገበት ሲሆን አንዴ ተዘርቶ  በአመት እስከ ሶስት ጊዜ ምርት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል። 
አቶ ታለጌታ ልዑል በግላቸዉ የማሽላ ምርምር ማድረግ ከጀመሩ 18 ዓመታት ማስቆጠራቸዉን ይናገራሉ። የተማሩትና የሰሩት በጥርስ ህክምና ሙያ ላይ ቢሆንም በግል ምርምር ማድረግ የመረጡት ግን በግብርና ስራ ላይ ነበር ። ተወልደዉ ባደጉበት የሰሜን ሸዋ ዞን ፤መንዝ ቀያ ወረዳ እንዶ ጊዮርጊስ መንደር በግብርና ስራ ከሚተዳደሩት ወላጆቻቸዉ ይመለከቱት የነበረዉ የሰብል አመራረት ችግርና ከዕጅ ወደ አፍ ኑሮ ለዚህ ምርምር እንደገፋፋቸዉ ይናገራሉ። እናም ምርምራቸዉን በትዉልድ ቀያቸዉ  በስፋት በሚመረተዉና  ከልጅነት ጊዜያቸዉ ጀምሮ በሚያዉቁት የሰብል ምርት፤ በተለይም በማሽላ ላይ አተኮሩ።

ይህን ምርምር በሀሳብ የሚደግፏቸዉ ባለሙያዎች ቢኖሩም በገንዘብና ምርምሩን ወደ ተግባር እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ ግን ድጋፍ የሚሰጣቸዉ አካል አልነበረም። ተስፋ ባለመቁረጥም የደከሙበትን ሃሳብና ሙከራ ይዘዉ የተለያዩ ተቋማትን በር ማንኳኳትን ቀጠሉ ምላሽ የሚሰጣቸዉ ግን አላገኙም ነበር። ያም ሆኖ መፃህፍትን በማገላበጥና ባለሙያዎችን በማማከር በማሽላ ላይ የሚያደርጉትን የግል ምርምር ቀጠሉ።ቀስበቀስም ሃሳባቸዉ ተቀባይነት ማግኜት ጀመረ።
እድሉን ባያገኙም ከልጅነታቸዉ ጀምሮ በግብርናዉ ዘርፍ የመማርና የመስራት ፍላጎት እንደነበራቸዉ የሚናገሩት አቶ ሳለጌታ«በቴወሪ የሚሰጥ ትምህርት ወደ ተግባር ተቀይሮ የሰዉ ልጆችን ህይወት በተለይም የገበሬዉን ህይወት ማሻሻል አለበት» የሚል ፅኑ ፍላጎት አላቸዉ።ምርምራቸዉንም በዚሁ ስሜት በማካሄድ አንዴ ተዘርቶ ዳግም ሳይታረስና ሳይዘራ በአመት ለሁለትና ለሶስት ዓመታት ምርት የሚሰጥና በአማካኝ በሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዝርያ ማግኜታቸዉን ገልፀዋል። ይህንንም በአማካኝ ከዓምስት እስከ ሰባት ዓመታት መቀጠል እንደሚቻል አስረድተዋል።ይህንን ዉጤት በግል በሚኖሩበት አካባቢና ገጠር በሚገኙ ቤተሰቦቻቸዉ ማሳ ላይ ከሌሎቹ የማሽላ ዝርያዎች ጋር ጎን ለጎን በተደጋጋሚ በመሞከር ምርምራቸዉን ሙሉ ለማድረግ ጥረዋል።በዚህም ያገኙት የማሽላ ዘር አንዴ ምርት ከሰጠ በኋላ ተመልሶ በጎን በኩል ልክ እንደ ዛፍ የሚያቆጠቁጥና ፍሬ የሚሰጥ መሆኑን አረጋግጠዋል። ይህ የማሽላ ዘር ለገበሬዉ የሚሰጡዉ ጥቅም በርካታ መሆኑንም ያስረዳሉ።«አንዴ ተዘርቶ ህይወቱን አፈሩ ዉስጥ ማቆየቱ ገበሬዉ ድጋሚ ከማረስና በየጊዜዉ ከመድከም ይልቅ መሬት ላይ ሆኖ ብዙ ጊዜ መቆየቱ በጣም ብዙ ጥቅሞች አሉት።» ይሉና መዝራትን ያስቀራሉ፣ድካምን ያስቀራሉ፣ለገበሬዉ ትልቅ እፎይታ ነዉ የሚሰጡት።ሁለተኛ ደግሞ ገበሬዉ የምብ እጥረት ቢያጋጥመዉ እነኝህን ተጠቅሞ አመቱን ሙሉ ራሱን ከረሃብና ከችግር ተቆጣጥሮ የምግብ ዋስትናዉን ያረጋግጣል ማለት ነዉ።»በማለት ጥቅሙን ዘርዝረዋል።

Äthiopien Addis Ababa Science and Technology Universität
ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology
Initiative Seeds for Needs
ምስል Bioversity International/C. Fadda

የምርምር ዉጤቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር በበጋ ወቅት ለከብቶች የማይቋረጥ መኖ መስጠት የሚችልም ነዉ።ይህንን የምርምር ሃሳብ ተረድተዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰሩ ተማሪዎችና ከፍተኛ ተመራማሪዎች አብረዋቸዉ አሉ። የቀድሞዉ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር የአሁኑ ኢኖቬሽንና የቴክኖሎጅ  ሚንስቴርም ከበርካታ ዓመታት ጥረት በኋላ  ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት 5 ዓመታት ለግለሰቡ ምርምር ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።በምንስቴር መስሪያ ቤቱ የሚዲያና ኮሚንኬሽን ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለምነዉ ። 

«አንዴ ተዘርተዉ ለረጅም ጊዜ ሳይቋርጡ ምርት የሚሰጡ የማሽላ ዝርያዎች ለይቻለሁ የሚል ሃሳብ ይዘዉ መጡ።ሲመጡም በተለያዩ የግብርና ተቋማት ጭምር ሄደዉየሚያዳምጣቸዉ እንደሌለና ችግር ገጥሟቸዉ እንደነበረ ነዉ ለመስሪያ ቤታችን ያነሱት።»ካሉ በኋላ። በወቅቱ የነበሩት ሃላፊ ምርምሩን በማሳ ላይ ተሞክሮ እንዲረጋገጥ መፍቀዳቸዉን ገልፀዋል።ለሙከራዉም ሚንስትር መስሪያ ቤቱ የገንዘብና የምርምር ቦታ ጭምር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

በነዚህ ዓመታትም በተለያዩ የገበሬ ማሳዎች ላይ በምርምር የተገኜዉ ማሽላ አንዴ ከተዘራ በኋላ ምርት እየሰጠ መቀጠሉን ና የአቶ ታለጌታ ሀሳብ ትክክል መሆኑን በተግባርና በተቋሙ የቴክኖሎጅ  ባለሙያዎች ጭምር መረጋገጡን  ኃላፊዉ አመልክተዋል።ይህንን የምርምር ስራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  አባላትና ሳይቀር ጎብኝተዉታል። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩንቨርሲቲ አጠገብ ባለ ማሳ ለሶስተኛ ዙር ምርምሩ ቀጥሎ ጥሩ ዉጤት መገኜቱን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
ያም ሆኖ ግን ይህንን የማሽላ ዘር ተባዝቶ ወደ ገበሬዉ በማሰራጨት ረገድ እክል እንደገጠማቸዉ ተመራማሪዉ አስረድተዋል።እንደ አቶ ተስፋዬ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጅ ሚንስቴር  ምርምሩን ከመደገፍ ባለፈ ዘሩን አባዝቶ ወደ ገበሬዉ የማሰራጨት ሃላፊነት የለዉም። ስለሆነም የግለሰቡ የምርምር ዉጤት የሀገር ሀብትና ዕሴት በመሆኑ በዉጭ ምንዛሬ ተገዝተዉ ወደ ሀገር ከሚገቡ የምርምር ዉጤቶች ይልቅ ሀገር በቀል ዕዉቀቶችን በማበረታታትና የጎደለዉን በሙያ በመደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል የተሻለ ነዉ። በዚህ ረገድም የብዝሃ ህይወትና  የግብርና ምርምር ተቋማትን የመሳሰሉ የምርምር ዉጤቱ ተባዝቶ ወደ ገበሬዉ ለማሰራጨት  በቀጥታ የሚመለከታቸዉ ማዕከላት  ቢያስቡበት የተሻለ ነዉ።በመንግስት በኩልም ይህንን መሰሉን የግል የምርምር ስራ ሊስተናገድ የሚችልበትን  ግልፅ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ትኩተት ሊደረግበት ይገባል።

Äthiopien Addis Ababa Science and Technology Universität Maisforschung
ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ