1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት 

ዓርብ፣ መስከረም 16 2012

ዓላማው«የተማሪዎችን እና የትምሕርት ተቋማትን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ተማሪዎች ተረጋግተው በመማር የሚጠበቅባቸው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ፣ለሚያጠፉት ጥፋትም ሆነ ለሚያደርሱት ጉዳት እነርሱም ሆነ ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ሃላፊነት መውሰድ ግዴታቸው በመሆኑ ተጠያቂ መሆናቸውን ለማስገንዘብ እና ኃላፊነት እንዲወስዱም ለማድረግ»መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3QMEt
Haramaya Universität Äthiopien
ምስል DW/G. Godae

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰሞኑን ሲነሱ ሲጣሉ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ያዘጋጀው የውል ሰነድ ነው። በዚህ ሳምንት ይፋ የደተደረገው እና በሀገር ውስጥ የመገናኛ አውታሮች የማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተያያዘው ጽሑፍ በዚህ ዓመት ዩኒቨርስቲ የሚገቡ አዳዲስ ተማሪዎች እና ነባር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ትምሕርት ከመጀመራቸው በፊት ከሚኖሩበት ወረዳ ጽሕፈት ቤት ጋር ውል መፈጸም እንደሚኖርባቸው ያሳስባል። በዚሁ መሠረት ተማሪዎቹ እና ወላጆቻቸው በየወረዳቸው ትምሕርት ጽሕፈት ቤት የውሉን ፎርም ይሞላሉ ፤በውሉ ላይም ፊርማቸውንም ያሰፍራሉ። መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው የውሉ ዓላማ «የተማሪዎችን እና የትምሕርት ተቋማትን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ ተማሪዎች ተረጋግተው በመማር የሚጠበቅባቸው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ፣ ለሚያጠፉት ጥፋትም ሆነ ለሚያደርሱት ጉዳት እነርሱም ሆነ ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ሃላፊነት መውሰድ ግዴታቸው በመሆኑ ተጠያቂ መሆናቸውን ለማስገንዘብ እና ኃላፊነት እንዲወስዱም ለማድረግ»መሆኑ መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው በተማሪዎች በወላጆች እና በዩኒቨርስቲ መካከል የሚገባ የኃላፊነት መውሰጃ ውል ላይ ሰፍሯል። ይህ አዲስ ውል ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ሲያነጋግሩ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ነበር።
ወዲ ዓስቡ በሚል የፌስ ቡክ ስም በዚህ ጉዳይ ላይ የሰፈረው አስተያየት ጥያቄ ያስቀድማል።«እድሜው18 ዓመት እና ከዛ በላይ የሆነ ልጅ ወላጅ አባት እንዴት ይጠየቃል?ራሱ ላጠፋው ጥፋት እራሱ መጠየቅና ፣መመለስ አለበት እንጂ ምስኪን አባት ለምን ሁለት ጊዜ ይበደላል? 1ኛ ተቸግሮ ለራሱ ሳይሆን ለልጁ ብዙ ወጪ እያወጣ እያስተማረ ነው 2ኛ ደግሞ ልጁ ባጠፋው ጥፋት አባት ተጠያቂ ሲሆን ጉዳት ነው ለወላጅ ።» በማለት አጠፋ የተባለው ተማሪ እንጂ፣ ወላጅ በምን እዳው ኃላፊነት ይውስድ  ሲል ውሉ ወላጆችንም ኃላፊነት ውስጥ መክተቱን ተቃውሟል።
ራሂመት ያሲን የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጭም በዚህ ይስማማሉ «እውነታቸውን ነው። ማንም ቤተሰብ ልጃቸው ጠንክሮ እንዲማር እና ጥሩ ውጤት እንድያመጣ አብረውት ከሚማሩ  ጋራ በሰላም በፍቅር ተከባብረህ ተማር ብሎ ልጁን መክሮ አደራ ብሎ ይልካል እንጂ ዱላ ይዘህ ተደባደብ ፈንትክ ግደል ከሞትክም እሬሳህን ተቀብየህ በክብር በጀግና ሰይሜህ አስቀብርሃለሁ፤ ብሎ አይደለም ። በትምህርት ቤቱ በሚከሰተው ችግር ምክንያት ቤተሰብ ልጄ ከአሁን አሁን ምን አድርገውት ይሆን ገለውት ይሆን በማለት የሚጨነቁት እና የሚያስቡት አንሶ በምን ኃጢያታቸው ነው ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ የሚሆኑት ?» ብለው መስሪያ ቤቱ በምን መነፀር አይቶት ነው ይሄን መግለጫ ያወጣው ? ሲሉ ሐሳባቸውን በጥያቄ ደምድመዋል። 
በውሉ ቅጽ ላይ የተማሪው ሙሉ ስም፣ አድራሻ፣ የትምሕርት መስኩ እና የሚማርበት ዩኒቨርስቲ፣ ስልክ ቁጥሩ የተማሪው አባት እና እናት ሙሉ ስም ይሞላል። የወላጅ ወይም አሳዳጊ ሙሉ ስም አድራሻም ይጻፋል። «በዩኒቨርስቲው በሰላማዊ መንገድ ትምሕርቱን ለመማር ከተማሪዎች ጋር ተግባብቶ ለመኖር በዩኒቨርስቲው ንብረት ላይ ችግር እንዳይፈጠር የበኩሉን ለመወጣት፣ ችግሮች ሲከሰቱ መረጃ ለመስጠት ቃል ገብቶ በምንም ሁከት እና አመጽ የማይሳተፍ መሆኑን አረጋግጦ ይህን ባያደርግ ግን ለሚፈጠረው ችግር ሕጋዊ እርምጃ ዩኒቨርስቲው ሊወስድ የሚችል መሆኑን በመረዳት ለሚጠፋው ሁሉ በሃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን በመቀበል በውሉ ሰነድ ላይ መፈረም ይጠበቅበታል።በተመሳሳይ ወላጅም ወይም አሳዳጊ ካለ በኋላ ልጅ በሚፈጠሩ ግጭቶች እና ጥፋቶች በግልም ይሁን በቡድን እንዳይሳተፍ ተባባሪም እንዳይሆን እና የዩኒቨርስቲውን የዲሲፕሊን መመሪያ አካዳሚያዊም ሆነ አስተዳደራዊ ሕጎችን እና ደንቦች እንዲያከብር መምከራቸውን ፣ ነገር ግን ከዚያ ውጭ በጥፋቶች ተሳታፊ እና ተባባሪ በመሆን ለሚያደርሰው ጉዳት ለሚወሰድበት እርምጃ በሕግ ተጠያቂ እንደሆነ ማስገንዘቡን በፊርማ ማረጋገጥ አለበት ይላል። 
ታዬ ቢ ደምሴ በፌስቡክ የውሉን ትክክለኛነት ለማስረዳት ሞክረዋል። «በዩኒቨርስቲ የምታስተምር ከሆነ አስፈላጊነቱን ታውቃለህ። እስካሁን የተባለው ለብዙ ዓመታት ተሞክሯል፤ ውጤት ግን አላመጣም። በግሌ ቢሞከር እደግፋለሁ» በማለት።
ዘውዱ ጂ ደግሞ መንግሥት ዜጎቹ ያለፍርሃት እና ስጋት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በነጻነት እንዲዘዋወሩ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና ተግባራዊም ማድረግ አለበት ይላሉ።

MStudenten auf dem Campus der Universität Addis Abeba
ምስል DW

«እኔ፣ ትክክል፣ አይደለም፣ ነው፣ እምለው» ብለው አስተያየታቸውን የሚጀምሩት ላስታና ሰቆጣ የሚል ስም ያላቸው አስተያየት ሰጭ በዚህ ጉዳይ ላይ መምህራንም ተጠያቂ ያደርጋሉ። «መንግስት፣ ገፊዎቹን፣ ነው፣ መያዝ፣ ያለበት፣ የዩኒቨርስቲ፣ መምሕራንም ናቸው የሚያስረብሹት» ሲሉ። 
የናቡቴ ይመር አስተያየት ደግሞ  «ፖለቲካውን ለመቆጣጠር ነው። ሰጥ ለጥ አርጎ ለመግዛት ነው ሌላ ምንም አይደለም! ወጣትን ለማኮላሸት የሚሰጥህን አርፈህ ብላ ! ሥራም ስትመደብ ኮብል ስቶንም ቢሆን ሥራ ለማለት ነው» ይላል።
«የሃይማኖት፣መሪዎች፣ስራቸውን፣እረስተዋል፦መንግስት፣ባጠፋው፣ጥፋት፣በየጊዜው፣የድሃልጅ፣እርስ፣በእርሡ፣ያልቃል፣የዩኒቨርስቲ፣ተማሪ፣የየሃይማኖቱን፣ሕግ፣ቢያከብር፣ችግር፣አይፈጠርም፣ነበር» የሚለው ደግሞ የገብረ ሥላሴ ቢራራ መልዕክት ነው። 

ሌላው በሳምንቱ የተለያዩ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት ጉዳይ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ባለፈው ቅዳሜ ያወጣው መግለጫ ነው። መስሪያ ቤቱ ከሸፉ ስላላቸው የሽብር ጥቃት ሙከራዎች ባወጣው በዚሁ መግለጫ  በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ለማድረስ በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉ የሶማሊያው አሸባብ እና ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው የአይ ኤስ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። በመግለጫው፣ ሁለቱ ቡድኖች፣ያሰማሯቸው ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ  አካባቢዎች ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፤ ሆቴሎች፤ በመንግስትና በግል ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት ክብረ ባዓላት በሚከበርባቸው ስፍራዎች የሸብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ገልጿል። ይህን በተመለከተ በፌስቡክ  ከሰፈሩት አስተያየቶች  ነብየ  ልዑል ሙሉጌታ በአጭሩ «ደስ ይላል በርቱ በመረጃ ደህንነቱ ኮርተናል » በማለት አድናቆታቸውን የገለጹበት  አንዱ ነው።

Karte Äthiopien englisch

ሁሌ አዲስ ፣የተባሉ አስተያየት ሰጭ  «አሁን ይህ ዜና እውነት ከሆነ ጥሩ ግን» ይሉና  «የኢትዮጵያ መረጃ እና ደህንነት ይህን ያክል አቅም እና ብቃት ካለው እነ ጀነራል ሰዓረ ጀነራል ገዛዒን ዶክተር አምባቸውን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን ያኔ በብቃቱ ከሞት ለምን አላተረፋቸውም?» ሲሉ ጠይቀዋል። 
ዋሲሁን ተስፋዬ በትዊተር  ገጽ መልእክታቸው ያሰፈሩት ጽሑፍ፦ «የተያዙት የአይሲስና የአልሸባብ ሰዎች ፡ በቁጥጥር ስር ባይውሉ ኖሮ  ብሄር ለይተው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ ብቻ ነበር በጅምላ የሚፈጁህ» ካለ በኋላ። ዘረኛን አይደለም ሌላ አይሲስ እንኳን ይበልጠዋል። ሲሉ መግለጫውን አስታከው ዘረኞችን ጎንጠዋል።
እነዚሁ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ለሽብር ጥቃት ሲዘጋጁ ተያዙ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ፣በኦሮምያ እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው በቅዳሜው መግለጫ  የተነገረው። ተስፋዬ ውብሸት «እነዚህን አሸባሪዎች ባለፉት 27 ዓመታት ነበሩ፡፡ ግን ለምን እንዳሁኑ ሊደፍሩን ቻሉ ብንል በ27 ዓመታቱ የነበረ አሁን ስለሌለ ነው፡፡»ካሉ በኋላ ምክንያቱን ሲዘረዝሩ «መንግስት መፍረስ በመጀመሩ፣ የደህንነት መ/ቤቱን ጨምሮ ሌሎቹ የጸጥታ ተቋማት በመፈራረስ ላይ ስለሆኑ ብንል አልተሳሳትንም፡፡ የሀገሪቱ ከፍተኛ መኮንኖችና ሲቪል ባለስልጣናትን እንዲሁም የመላ ህዝባችንን ደህንነት መጠበቅ ያልቻለ መንግስት ማን ሊፈራው ይችላል?ሲሊ ይጠይቁ እና « ማንም»በማለት ከመለሱ በኋላ«የጠ/ሚኒስቱሩ የ18 ወራት ስራ የአፄ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት እድሳት መቆጣጠርና መምራት እንጂ የኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዩ ስላልነበረም ነው» ብለዋል።
በዕውቀቱ አለልኝ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ መንግሥት አቋሙ ልፍስፍስ መሆኑን አይቶ ነው። ሲሉ ሃሳባቸውን በአጭሩ አስቀምጠዋል።
የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ህዝቡ የነዚህን ቡድኖች ዝግጅት በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ እንዲሰጥም ጠይቋል። 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ