1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተመርቀው ሥራ ያጡ የሲዳማ ወጣቶች ሮሮ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 7 2014

በኢትዮጵያ የወጣቶች ሥራ አጥነት ስለመስፋፋቱ መስማት የተለመደ ኾኗል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ በርካታ የሲዳማ ክልል ወጣቶች የሥራ ዕድል እጦት እንዳማረራቸው ይገልጣሉ። አስተያየት ሰጪ ወጣቶች በሥራ እድል ፈጠራ ማኅበራት አደረጃጀትን ጨምሮ በሠራተኛ ቅጥር አፈጻጸሞች ላይ በዘመድና በአድሎ የመሥራት ሁኔታዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ 

https://p.dw.com/p/49zz9
Äthiopien | Teilnehmer Jugenddialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«በዘመድና በአድሎ ይሰራል »

ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱን ባስቆጠረው የሲዳማ ክልል በበርካታ ወጣቶች ዘንድ የሥራ አጥነት ችግር መስማት የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ ሥራ አጥነት አለምአቀፋዊና አገራዊ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥትና የዜጎች ተግዳሮት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ እንደኢትዮጰያ ባሉ በድህነት አረንቋ ውስጥ በሚገኙ ሕዝቦች ዘንድ ችግሩ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ያለገቢ መኖር ይቅርና በሥራ ላይ የሚገኙ ዜጎች የኑሮንና ጫና ተቋቁሞ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ፈተና ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለዓመታት ያለሥራ የተቋመጡ የሲዳማ ክልል ወጣቶችን ለተለያዩ የሥነ ልቦና ጉዳቶች መዳረጉ አልቀረም፡፡

የሲዳማ ክልል ወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የውይይት መድረኮችና ምክክሮች ተካሄደዋል፡፡ በውይይት መድረኮቹ ላይ የክልሉ መንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና የገዢው ብልጽግና ፖርቲ ተወካዮች የወጣቶቹን ጥያቄ ለመመለስ በመንግሥት በኩል ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን በሂደት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሥራ እጥነትን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ሥለመኖራቸው በገዢው የሲዳማ ብልጽግና ፖርቲ የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ሃላፊ ወጣት አክሊሉ ዓለሙ ይናገራል፡፡

አስተያየት ሰጪ ወጣቶች በበኩላቸው በሥራ እድል ፈጠራ ማኅበራት አደረጃጀትን ጨምሮ በሠራተኛ ቅጥር አፈጻጸሞች ላይ በዘመድና በአድሎ የመሥራት ሁኔታዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡
ወጣቶቹ ባነሷቸው ቅሬታ ላይ የሚስማሙት የገዢው ብልጽግና ፖርቲ የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ሃላፊው ወጣት አክሊሉ በዚህ ረገድ በሚመለከታቸው አካላት በኩል የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ይላሉ፡፡

በእርግጥ የሲዳማ ወጣቶችን ጨምሮ የአብዛኞቹ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነው የሥራ አጥነት ችግር የራሱ መነሻ ምክንያቶችና የመፍትሔ አማራጮች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በሀዋሣ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ደገላ ኤርገኖ በኢትዮጵያ የሥራ አጥነት መነሻዎች በዋናነት የህዝብ ቁጥር መጨምርና በሥራ ላይ ያለን የተዛባ አመለካከት ነው ይላሉ፡፡ 

ዶክተር ደገላ የሥራ አጥነትን ምጣኔ ለመቀነስ የግል ኢንቨስትመንት ማጠናከርና ፣ በሥራ ፈጠራ የሚሰማሩ ወጣቶችን በክሀሎት ፣ የፋይናንስ ብድርና የሥራ ቦታዎችን በማመቻችት መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ