1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦረና፤ ከክረምት ማግስት ድርቅ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 9 2014

ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ በቦረና ዞን ሰባት ወረዳዎች ባለፉት ሁለት የዝናብ ወቅቶች በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ መከሰቱ ተሰምቷል። የአካባቢው ነዋሪዎች አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው ጉዳቱ የከፋው ለጊዜው የኑሯቸው መሠረት በመሆኑት ከብቶቻቸው ላይ ነው። ነዋሪዎቹም ለምግብና ውኃ እጥረት መጋለጣቸው ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/41rBB
Äthiopien | Dürre in Borena
ምስል Firaol Wako/PHD

«ከብቶቻቸው እየሞቱ ነው»

«ዝናቡ በተፈለገው ጊዜ ባለመዝነቡ ከባድ ድርቅ አስከትሎብናል። ከብቶች ፍየሎች እና ግመሎች በድርቁ ጉዳት ደሶባቸዋል።  ከብቶቻችን ግን በተለየ ሁኔታ እየሞቱብን ነው፤ ግመሎቻችን ሰውነታቸው በጣም ከስቷል። በድርቁ ምክንያት እስካሁን ከአካባቢያችን ይኸን ያህልከብቶች ሞተዋል ብዬ መናገር አልችልም። የኔ የራሱ ሁለት ከብቶች ሞተውብኛል። ዘመዶቼም አምስት ስድስት የሚሆኑ ከብቶቻቸው ሞተውባቸው አንስተዋል። » 

የቦረናው አርብቶ አደር ዲባ ዲዳ። የቦረና ሰማይ ዝናብ ከራቀው ወራት መቆጠራቸውን ነው አርብቶ አደሩ የነገሩን። በቀደመው ዓመት የዝናብ ወራት በቂ መኖ አለመዘጋጀቱ ጉዳቱን እንዳባባሰው የገለጹልን የዞኑ የእንስሳት ሃብት ቢሮ ባልደረባ የተከሰተው የውኃ እጥረት በኗሪው ኅብረተሰብ ላይም ችግር ማስከተሉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን አርብቶ አደሮች የኑሯቸው ዋልታ ከሆኑት ከከብቶቻቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት ቀረብ ብለው ያስተዋሉ ያውቁታል። አሁን በቦረና ዞን ሰባት ቦታዎች ላይ ድርቅ ያሳረፈው ጨከን ያለ በትር እንደ የአርብቶ አደር ዲባ ዲዳ ሁሉ የብዙዎችን ከብቶች እስትንፋስ ጸጥ እያደረገ ነው። በቦረና ዞን ዳስ ወረዳ የእንስሳት ሃብት ቢሮ ባልደረባ ዶክተር ፍራኦል ዋቆ እንደሚሉት በሺህዎች የሚገመቱ ከብቶች በድርቁ ሞተዋል፤ በርካታ ሺህዎቹም ለመንቀሳቀስ እንክ አቅም አጥተዋል።  

«እስከ ትናንትናው ዕለት ባለው መረጃ መሠረት እስከ 9,679 ከብቶች ሞተዋል፤ 21,000 አካባቢ ከብቶት ያለሰው ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በዞኑ ሪፖርት መሰረትም እስካሁን ድረስ 500 ሺህ የሚሆን ሕዝብ የውኃ እጥረት አጋጥሞታል፤ 17 ሺህ ሰው ደግሞ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል።»

ዶክተር ፍራኦል በእንስሳቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት ድርቁ ዋነኛ መንስኤ ቢሆንም አስቀድሞ በቂ የመኖ ዝግጅት አለመደረጉሩ ችግሩን እንዳባባሰውም አዕንኦት ሰጥተዋል።

«ድርቁ የተከሰተው ባለፉት ሁለት ወራት ይሆናል ይኼ ጉዳት መድረስ ከጀመረ፤ ይኽ የሆነበት ዋነኛው ምክንያትም የመኸር ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመዝነቡ ከእሱም ቀድሞ የበልግ ዝናብ ባለመዝነቡ ነው። ሆኖም ግን ዋነኛ ምክንያቱ ምንድነው በበጋ ወቅት ላይ በመንግሥት በኩል ሊከሰት የሚችል የመኖ እጥረትን ለመከላከል አስቀድሞ በቂ ዝግጅት አልተደረገም።»

የበልግ እና የመኸር ዝናብ ባለመጣሉ በቦረና ሰባት አካባቢዎች ድርቅ በከብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ነው የተነገረው። የአካባቢው ነዋሪ አርብቶ አደር ዲባ ዲዳ ዎች ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ባለመዝነቡ ከብቶች እና ግመሎቻቸው ክፉኛ እየተጎዱ መሆኑን ይናገራሉ። ከብቶቻቸው በመብዛታቸውን ግን በእነሱ አቅም አስፈላጊውን ለማቅረብ ከአቅም በላይ ሆኖባቸዋል።

BG Dürre | Äthiopien
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

«እኛ በግላችን የቻልነውን ያህል ስንጥር ቆይተናል፤ የከብቶቻችን ብዛት ግን ለመንከባከብ ከአቅማችን በላይ ሆነውብናል። አንዳንድ ሰዎች እንጨት በመፈቅፈቅ ጭምር ከብቶቻቸውን ሊታደጉ ጥረት አድርገዋል። አንዳንዶች ቀደም ሲል አከማችተው የነበረውን ድርቆሽ ሰጥተው ጨርሰዋል። በመንግሥት በኩል ግን እስካሁን የተደረገልን አንዳችም ድጋፍ የለም። ከሞት የተረፉት ደግሞ ለጊዜው አሉ ።»

በተወሰኑ ወረዳዎች ዝናብ መዘግየቱ ያስከተለው የመኖ እጥረት መኖሩ እና ከእሱም ጋር ተያይዞ ለሰዎችም ለከብቶችም የውኃ እጥረት ማጋጠሙን የገለጹልን በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፤ በበኩላቸው ድርቁ ቀስበቀስ እየተባባሰ መምጣቱን ይናገራሉ።   ችግሩ ከተሰማ ጊዜ አንስቶም ተገቢውን ርዳታ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል። የዝናብ እጥረት በቦረና ሰባት ዞኖች ያስከተለው ጉዳት ከተሰማ በኋላ አሁን አስፈላጊውን ርዳታ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያረጋገጡት ዶክተር ፍራኦል፤ አቅርቦቱ ግን በቂ አይደለም ነው የሚሉት።

በሰሜን ኬንያ የተከሰተው ድርቅ በርካታ ሺህ ኗሪዎችን ለምግብ እጥረት ማጋለጡን ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ባለፈው ሳምንት ማለቂያ ላይ ይፋ አድርገዋል። ሰሜን ኬንያ አካባቢ ከደቡብ ኢትዮጵያ ግዛት ከመጎራበቱም በላይ የአየር ሁኔታውም ተመሳሳይ በመሆኑ የሁለቱም ሃገራት የድንበር አቅራቢያ ነዋሪዎች በአርብቶ አደርነት ይታወቃሉ። በሁለቱም ወገን ባሉ አካባቢዎች የኅብረተሰቡ የኑሮ መሠረት የሆኑት ከብቶች ለከፋ ጉዳት ተጋልጠዋል። ሕይወታቸው ከከብቶቻቸው ጋር የተሳሰረው የቦረናው አርብቶ አደር ዲባ ዲዳ በዚህ ድርቅ ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸው ከብቶቻቸው ቢሆኑም የውኃ እጥረቱ ችግሩ ሰዎችም ላይ እየደረሰ በመሆኑ የባሰ ሳይደርስ ድረሱልን ነው የሚሉት።   

Äthiopien | Dürre in Borena
ምስል Firaol Wako/PHD

« እኔ ከብቶቻችንን በተመለከተ ማለት የምፈልገው ዉሎ ባደረ ቁጥር ከብቶቻችን ለእልቂት እየተዳረጉ ስለሆነ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግልን ፤ ችግሩ ሰዎች ላይም ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ  በዓለማቀፍ ደረጃ ማሳወቅ ካስፈለገም አሳውቆ መፍትሔ እንዲፈልግልን ነው የምጠይቀው»

ሰፊ የከብት ሀብት እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ ያላትን ያህል ከዚህ ዘርፍ እጅግም እንዳልተጠቀመች ነው በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴታው የገለጹልን። አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በቆላማው የሀገሪቱ ክፍል እንደመኖሩ የዝናብ እጥረት እና ድርቅ እንደሚደጋገምበትም ተናግረዋል። ድርቅ መደጋገሙ ከታወቀ በከብቶቹም ሆነ በኗሪው ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዳይደጋገም በዘላቂነት መፍትሄ ማበጀት አይቻልም ይሆን? ዶክተር ፍቅሩ፤

«ይቻላል ለዛም መሠራት ያለባቸው ከዚህ በፊት የተጀመሩ ነገሮች ውኃ ማቆርም የመኖ ማልማቱም ሥራ በተጠናከረ መልኩ መሠራት አለበት የምለውም ለዚያ ነው። ይኼኛውን እሳት የማጥፋቱ ሥራ ውስጥ ከመግባት በየጊዜው ዘላቂ የሆኑ የአጭር እና የረዥም ጊዜ ሥራዎችን ሠርቶ መኖውንም ማልማቱ ብቻ ሳይሆን የክምችቱንም ሥራዎች በደንብ መሠራት አለበት።»

 በድርቅ ወቅት ሊከተል የሚችል ተላላፊ እንደሚታሰብ ያረጋገጡት ባለሙያው ሆኖም እንስሳቱ አሁን ተዳክመው ባሉበት መድኃኒት መስጠቱ ያልተጠበቀ ችግር እንዳያስከትል በሚል ክትባቶች ቢዘጋጁም ለጊዜው አለመሰጠቱን አመልክተዋል። በአንድ ወገን ስለድርቅ በሚነገርበት በዚህ ሰዓት ጎርፍ ችግር ያስከተለበት አካባቢ መኖሩን በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴታው ገልጸውልናል። እዚያው ደቡባዊ ኢትዮጵያ ጂንካ ዘንድሮ ብቻ ሳይሆንም አምና እና ካቻምናም ተመሳሳይ ጎርፍ ማጋጠሙንም አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ