1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2014

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዛሬ በቀረቡበት ፍርድ ቤት ግንቦት 8 በአዲስ አበባ ከተያዙ በኋላ ዓይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ ወዳልታወቀ ምድር ቤት ተወስደው ለሁለት ቀናት ማደራቸውን ተናግረዋል። በሔሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር መወሰዳቸውን የገለጹት ጄኔራሉ የተጠረጠሩበትን ምክንያት እንደማያውቁም ለፍርድ ቤት አስረድተዋል። ጉዳዩ ለግንቦት 22 ተቀጥሯል

https://p.dw.com/p/4BdxA
Äthiopien Addis Abeba |  Tefera Mamo
ምስል Solomon Muchie/DW

ጉዳዩ ለግንቦት 22 ተቀጥሯል

የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በባሕርዳር አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው የ10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጣቸው። ጄነራል ተፈራ ማሞ ከግንቦት 8 ቀን 2014 ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ ባሕር ዳር ተዛውረዋል።  

ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ከሩብ ሲሆን ጀነራሉ ነጠላ ጫማ አድርገው ጠቆር ያለ የስፖርት ሱሪና ሸሚዝ አድርገው ነው አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረቡት፣ የመሰላቸትና የድካም ስሜት ይታይባቸዋል።  ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ተጠይቀውም ምንም እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።  

ጀነራሉ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት በጦር ሜዳ በጥይት የተመቱባቸው የሰውነት ክፍሎቻቸው ከነርቫቸው ጋር በመገናኘት እየታመሙ በመሆኑ ለህክምና ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን አመልክተው ሆኖም ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ ም ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ እዛው አዲስ አበባ ዮሴፍ ከሚባል አካባቢ በማያውቋቸው አካላት ግን ደግሞ የደህንነት ሰዎች ብለው ባሰቧቸው ሰዎች ተይዘው ዓይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ ወደ አልታወቀ ምድር ቤት ተወስደው ለሁለት ቀናት ማደራቸውን ተናግረዋል።  

ከዚያም በሄሊኮፕተር አሁንም አይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ ወደ ማያውቁት ቦታ ከተወሰዱ በኋላ አይናቸው ሲገለጥ ራሳቸው በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው 9ነኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዳገኙ ተናግረዋል።  
አቃቤ ህግ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ስላሉኝ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ለመጠርጠራቸው ምክንያት የሆኑና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ለተለያዩ ሚዲያዎች የሰጧቸውን የቪዲዮ ምስሎች ለመሰብሰብ፣ ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች ስለሚቀሩ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት የሚመጡ ማስረጃዎች ስለሚቀሩ፣ ሁለት ስልኮቻቸውን ለመርመር የተጠየቀው ቀን ይሰጥኝ ስል ተከራክሯል፡፡ 

የጀነራሉ ጠበቃ በበኩላቸው ቪዲዮዎቹን በቀላሉ ከኢንተርኔት ማውረድ ይቻላል፣ ሌሎች የተባሉ ተጠርጣሪዎችም በስም ባለመጠቀሳቸው፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ግለሰቡን ወደ ባሕር ዳር ሲልክ ያሉትን ማስረጃዎች ጨምሮ ልኳል፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችም ግለሰቡን በቁጥጥር ባደረጉ ሰዎች እጅ በመሆናቸው ያለፉት 5 ቀናት ምርመራውን ለማድረግ በቂ ጊዜ ስለነበር ደንበኛዬ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር ይፈቱ ሲል ጠይቋል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ የግራቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ቀሩ የተባሉትን የምርመራ ስራዎች ለማከናወን ተገቢ ሆኖ ባለማግኘቱ በ10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ 
በዚሁም መሰረት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ እስከዛው ድርስ አሁን ባሉበት የፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ብሏል፡፡ ጀነራል ተፈራ ማሞም አሁን ባሉበት ቢቆዩ እንደሚመርጡ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ 
በመሆኑም ጀነራሉ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ ም ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የሚቅረቡ ይሆናል። ጀነራሉ ወደ ፍርድ ቤት በመጡ ጊዜ በርካታ የፀጥታ ኃይል አካባቢውን በከፍተኛ ሁኔታ ሲጠብቅ ተመልክተናል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ዓለምነው መኮንን