1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሬግዚት ጣጣ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2011

ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት የተስማማችበት የብሬግዚት ውል የብሪታንያ ፖለቲከኞችን ማወዛገቡ ቀጥሏል። በሌላ በኩል ብሪታንያ ከህብረቱ እንድትወጣ ከሚጠይቀው ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩሉ የህዝበ ውሳኔ ውጤት በኋላ በርካታ ብሪታንያውያን ወደ ሌሎች ሀገራት እየፈለሱ ነው። ከመካከላቸው ደግሞ አየርላንድ የብዙዎቹ ምርጫ ናት።

https://p.dw.com/p/3Fgym
Großbritanien | Theresa May | Unterhaus | Brexit
ምስል picture-alliance/dpa/empics/PA Wire/House of Commons

የብሬግዚት ጣጣ

ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት የተስማማችበት የብሬግዚት ውል እጣ ፈንታ ዛሬም አልታወቀም።ሁለት ጊዜ በሰጠው ድምጽ ውሉን የተቃወመው የብሪታንያ ፓርላማ ሃሳቡን ይቀይር እንደሆን ለመሞከር  በዚህ ሳምንት ለሶስተኛ ጊዜ ድምጽ ይሰጣል ተብሏል። ይሁን እና ሜይ ትናንት እንዳሉት ውሉን መልሶ ለምክር ቤቱ ማቅረብ የሚቻልበት በቂ ድጋፍ የለም። ትናንት የፓርላማው አባላት በብሬግዚት ውል ምትክ በአማራጭነት በሚቀርቡ ሃሳቦች ላይ ድምጽ መስጠት እንዲችሉ በአብላጫ ድምጽ ወስነዋል። ያም ሆኖ የብሬግዚት እጣ ፈንታ አሁንም ግልጽ አይደለም። እስካሁን በርግጠኝነት ከሚታወቁት ውስጥ ሜይ ሀገራቸው ከህብረቱ የምትወጣበት ጊዜ እስከ ሰኔ 23፣2011 ይራዘም ብለው ህብረቱን ቢጠይቁም የመጨረሻው ቀነ ገደብ እስከ ግንቦት 14 እንዲሆን ህብረቱ መፍቀዱ አንዱ ነው። ህብረቱ በተጨማሪም የብሪታንያ ፓርላማ እስከ ሚያዚያ 4 ድረስ አዲስ እቅድ ይዞ እንዲቀርብ ወይም ያለ ስምምነት ለቆ ለመውጣት እንዲወስን ጊዜ መስጠቱም ሌላው ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጭ በብሬግዚት ላይ በብሪታንያ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል ሰፍቶ ውዝግቡም ቀጥሏል። የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ ብሪታንያ ያለ ስምምነት ከአውሮጳ ህብረት ከወጣች ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለማስወገድ የሚረዳ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል። የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ብሪታንያ በአዲሱ የብሬግዚት ቀነ ገደብ ያለ ስምምነት ህብረቱን ለቃ ልትወጣ ትችላለች የሚለው እምነት እያመዘነ በመምጣቱ ለዚህ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል። በመግለጫው እንደተጠቀሰው ህብረቱ የሚወስደው እርምጃ ብሪታንያ ያለ ስምምነት ከህብረቱ ከወጣች ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ሙሉ በሙሉ ሊያስቀረው አይችልም ፤በዝግጅት አለመኖር የሚፈጠረውን ችግርም የሚያስወግድ ወይም አባል ሀገራት የሚያገኙትን ጥቅም የሚተካም አይሆንም። የብራሰልስ እና የለንደን ፖለቲከኞች እንዲህ ሲወዛገቡ የብሬግዚት መዘዞች ደግሞ በየአቅጣጫው መታየታቸው ቀጥሏል። ከመካከላቸው ከብሪታንያ ወደሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የሚያካሂደው ፍልሰት ይገኝበታል። በሰኔ 2008 ዓም ከአውሮጳ ህብረት መውጣት ወይም ከህብረቱ ጋር መቆየት የሚሉ ሁለት ምርጫዎች የቀረቡለት የብሪታንያ ህዝብ በሰጠው ድምጽ ፣መውጣትን የመረጠው በጠባብ ልዩነት በልጦ የብሬግዚት ድርድር ከተጀመረ በኋላ ብሪታንያ የሚገኙ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች እና ብሪታንያውያን ወደ ሌሎች ሀገራት እየፈለሱ ነው። በተለይም ወደ ጎረቤት አየርላንድ የሄዱት ቁጥር ያመዝናል። ዶክተር መሐሪ ፍስሀ የአየርላንድ ዜግነት ያላቸው የፍልሰት፣ የአውሮጳ ፖለቲካ ጉዳዮች እና የህግ ምሁር ናቸው። አየርላንድ ሲኖሩ 21 ዓመታት ተቆጥረዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ብሬግዚት በአየርላንድ በሰሜን አየርላንድ እና በብሪታንያ ልዩ ልዩ መዘዞችን አስከትሏል። 
በብሬግዚት ውል ውስጥ ከሚያወዛግቡት ጉዳዮች አንዱ የብሪታንያዋ የሰሜን አየርላንድ እና የአየርላንድ ሪፐብሊክ ድንበር ጉዳይ ነው። ብሪታንያ ከህብረቱ ከወጣች እስካሁን ቁጥጥር የማይካሄድበት ሁለቱን የሚያዋስነው ድንበር ጥበቃ እንዴት ይቀጥል የሚለው ሲያከራክር ቆይቷል። ከዚህ ሌላ በሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት ገበያ ካላቸው ብሪታንያ ከሚገኙ ኩባንያዎች አንዳንዶቹ፣ ብሪታንያ ህብረቱን ስትለቅ ችግር ላይ እንዳይወድቁ በመስጋት ወደ ሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት መሄድን መርጠዋል። ብሪታንያ ከህብረቱ መነጠልዋ ችግር ያስከትልብናል ብለው የሰጉ ብሪታንያውያንም የአየርላንድ ዜግነት እየሰወዱ ነው እንደ ዶክተር መሐሪ። ይህ
የብሪታንያውያንም ሆነ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ከብሪታንያ መውጣት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደሚዳርግ ዶክተር መሀሪ ያስረዳሉ። ብሬግዚት እውን ከሆነ ደግሞ በተለይ በትምህርቱ ዘርፍም ብሪታንያ የምታጣው ብዙ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ዶክተር መሀሪ በስፔኑ ግራንዳ ዩኒቨርስቲ «ኤራስሙስ ሙንዱስ» በተባለው የአውሮጳ ህብረት የትምህርት መርሃ ግብር የፍልሰት ጉዳዮች መምህር ናቸው። ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ ከወጣች ፣ይላሉ ዶክተር መሀሪ ከ5 የተለያዩ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የሚመለመሉ ተማሪዎች  በ3 ሀገራት በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እየተዘዋወሩ የድህረ ምረቃ ወይም የፒ ኤች ዲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት የዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆን አትችልም።

Großbritannien London People's Vote Demonstration
ምስል Imago/i Images/P. Maclaine
Großbritanien | Theresa May | Brexit
ምስል Reuters/Pool/J. Brady
Großbritannien London People's Vote Demonstration
ምስል AFP/N. Halle'n

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ