1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔራዊ አደጋ ሥጋትና አመራር ኮሚሽን ተጨማሪ በጀት ጠየቀ

ሐሙስ፣ ኅዳር 8 2015

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ወደ 8.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ ተጨማሪ 13 ቢሊዮን ብር ምደባ እንደሚያስፈልገው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ። ኮሚሽኑ ይህንን ሥራ ለማከናወን አሁን ላይ በካዝናው 6 ቢሊዮን ብር ብቻ ተቀማጭ እንዳለው ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4JfiK
Äthiopien Schäden durch Auseinandersetzungen in Adis Abeba nach Beendigung des Ramadan
ምስል Seyoum Getu/DW

13 ቢሊዮን ብር ምደባ ያስፈልጋል፤ ተቀማጭ 6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነዉ

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ወደ 8.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ ተጨማሪ 13 ቢሊዮን ብር ምደባ እንደሚያስፈልገው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ። ኮሚሽኑ ይህንን ሥራ ለማከናወን አሁን ላይ በካዝናው 6 ቢሊዮን ብር ብቻ ተቀማጭ እንዳለው ገልጿል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የሦስት ወራት የሥራ ክንውን ሲያደምጥ እንደተባለው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ያጋጠመው የሥነ ልቦና ችግር እጅግ ከፍተኛ ነው። የውጭ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ወገኖች ድጋፎች በዋናነት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲሄድ የመፈለግ ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ የፍትሐዊነት ችግሮች አልነበሩም ማለት አይቻልም ተብሏል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 22.1 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውም ተገልጿል።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለ ማርያም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ዘገባ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው 22.1 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ውስጥ 9.9 ሚሊዮን ያህሉ በመንግሥት የአስቸኳይ ድጋፍ ይደረግለታል፣ የቀሪ 11 ሚሊዮን ገደማ ያህሉ ደግሞ ረጂ ድርጅቶች በሚሰጡት ድጋፍ የሚሸፈን ነው።

"በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ላይ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ 263 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ 98 ሺህ ኩንታል የሰብዓዊ ድጋፍ ማጓጓዝ ተችላል" ብለዋል።

የተረጂነት አስተሳሰብ እና አመለካከት ከፍተኛ ነው የሚሉት የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ሰሜን ኢትዮጵያን ያደቀቀው ጦርነት ያደረሰው  "የሥነ ልቦና ቁስል እጅግ ከፍተኛ ነው" ሲሉ ምክር ቤቱ ጉዳዩን በውል እንዲያውቀው አድርገዋል።

ከእርዳታ በፍትሐዊነት መዳረስ ጋር ተያይዞ ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን "ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ወደ ሰሜን አካባቢ እንዲያተኩሩ ፍላጎት ነበር። ይህ የሆነው የድጋፍ ሰጪዎች ፍላጎት ስላለ ነው። የፍትሐዊነት ችግር የለም ማለት አይቻልም" ብለዋል።

ብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን 3 ትልልቅ ተጨማሪ የመጋዝን ስራዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ ዳርቻዎች ለመሥራት የያዘው እቅድ እስካሁን እንዳልሰመረለት ገልጿል።

ተቋሙ በድርቅ ምክንያት በተለይ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችንም  በተቻለው አቅም ሁሉ እያገዘ መሆኑን ገልጿል።

የመንግሥትን እና የሕወሓትን ስምምነት ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፎች በተሽከርካሪ እና አውሮፕላን በተለይ ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ ተጀምሯል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ