1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነ አራርሶ ቢቂላን "እንደ ኦነግ አመራሮች መቀበል አይችልም"

እሑድ፣ መጋቢት 19 2013

በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያካሔደውን ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ የሊቃነ-መናብርት ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውድቅ አደረገ። በዚሁ ምክንያት በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ ያቀረበውን ጥያቄ ሳይመለከተው ቀርቷል። 

https://p.dw.com/p/3rInT
Äthiopien Addis Abeba | OLF Anführer Qejela Meredasa, Birhanu Lema Tekedami , Ararso Biqila und Gelana
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመሩት ኦነግ ያካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ የነበሩበትን እንከኖች ነቅሶ በማውጣት "ተቀባይነት የለውም" የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ጠቅላላ ጉባኤው እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ለመምራት የተመረጡ አዳዲስ አመራሮች ተቀባይነት ባለማግኘታቸው በጥቂት ወራት ውስጥ በሚካሔደው ምርጫ ለመሳተፍ "የምልክት መረጣ እና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት" ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳይመለከተው ቀርቷል። 

በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ የድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ተሰብስቦ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች መምረጡን ያስረዳሉ የተባሉ ሠነዶች ባለፈው ሳምንት ማቅረቡን ቦርዱ አስታውቆ ነበር።

በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ አቶ አራርሶ ቢቂላ ሊቀ-መንበር፤ አቶ ብርሐኑ ለማ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር እንዲሁም አቶ ቀጀላ መርዳሳ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው መመረጣቸው ተገልጿል። በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ "የምልክት መረጣ እና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት" ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቧል። 

ጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ የሊቃነ-መናብርቱ ምርጫ ግን አቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመሩት የግንባሩ ሌላ ቡድን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ቃል አቀባይ አቶ በቴ ኡርጌሳ "ይኸ ስብሰባ ሕገ-ወጥ ነው። የድርጅቱ አመራር አያውቀውም፤ አልተጋበዙም" ሲሉ ጠቅላላ ጉባኤው ተካሒዶ አዳዲስ አመራሮች ተመረጡ በተባለበት ዕለት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ ባደረገው ውሳኔ የጠቅላላ ጉባኤ ማስፈጸም የሚችለውን አስፈጻሚ ኮሚቴን ባቋቋመበት ስብሰባ ከሥራ አስፈፃሚው ሁለት ሶስተኛው መሰብሰብ ቢኖርበትም የታደሙት ሶስት አባላት ብቻ መሆናቸውን አስታውቋል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳለው "የጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የተቋቋመው ኮሚቴ በደንቡ መሰረት ምልዐተ ጉባኤ ሳይሟላ የተቋቋመ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባኤውን መጥራትና ማስፈጸም አይችልም።"

ተካሔደ በተባለው ጠቅላላ ጉባኤ በኦነግ መተዳደሪያ ደንብ መሳተፍ አለባቸው የተባሉ አካላት መገኘታቸውን፤የጠቅላላ ጉባኤው ተካፋዮች የፓርቲውን ደንብ ማሟላታቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻለም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በውሳኔው አስታውቋል።

ተካሔደ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ከዚህ ቀደም በኦነግ ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብ "የፓርቲው አመራሮችን ፣ መዋቅሮቹን እና አባላቶቹ የተለያዩ በፓርቲው ሕገ-ደንብ ላይ በተቀመጡ መንገዶች በመጠቀም በጠቅላላ ጉባኤ ችግሩን እንዲፈቱ" በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ "መሰረት አድርጎ የተከናወነ ጉባኤ መሆኑን አያሳይም" ተብሏል። 

ጠቅላላ ጉባኤ የነበሩበትን እንከኖች ነቅሶ ያወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳለው እነ አቶ አራርሶ ቢቂላን "እንደ ኦነግ አመራሮች መቀበል አይችልም።" አዲስ ተመረጡ የተባሉት አመራሮች በመጪው ምርጫ "ለመሳተፍ እና እጩዎች ለማቅረብ ያቀረቡትን ጥያቄ አሁን የተመረጠው አመራር ተቀባይነት" ባለማግኘቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "ማየት እንዳላስፈለገው" አስታውቋል። 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ