1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ አሸነፈ

እሑድ፣ ሐምሌ 4 2013

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ፓርቲ ብልጽግና ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ አሸነፈ። ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት ትናንት ምሽት ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/3wKDP
Parlamentswahl in Äthiopien 2021
ምስል T. Dinssa/DW

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ውድድር በተደረገባቸው እና ውጤታቸው በይፋ ከተገለጸ 436 ወንበሮች ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ 410 ወንበሮችን በማሸነፍ ለቀጣይ አምስት አመታት መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱ ተገልጿል። በአዲስ አበባ ከተማ አንድ የግል ተወዳዳሪን ጨምሮ 4 የግል ዕጩዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሚያደርጋቸውን ድምጽ እንዳገኙ ቦርዱ ገልጿል። በአማራ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን 5 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ በደቡብ ክልል ደግሞ የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት መቀመጫዎችን አሸንፏል። ኦነግ እና ኦፌኮ ራሳቸውን ከምርጫው ባገለሉበት እና ውድድር በተደረገባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ከሶስት መቀመጫዎች በቀር ገዢው የብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ ሆኗል። በቦርዱ የሎጀስቲክ እጥረት አልያም ተከስቷል ባለው አለመረጋጋት  በሌሎች በአስራዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ምርጫ እንደሚደረግ ገልጧል። በምርጫው ያሸነፈው የብልጽግና ፓርቲ በቀጣዩ የጥቅምት ወር አዲስ መንግስት ይመሰርታል ተብሎ ይጠበቃል። 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሀገሪቱ በብርቱ ፈተና ውስጥ ሆና ያከናወነችው ምርጫ ነው ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርትኳን ሚደቅሳ ተናግረዋል። ነገር ግን ሕዝቡ በመረጠው ሊተዳደር ዕድል ፈጥሮለታል፤ ሂደቱም ወደ ኋላ የማይመለስ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም መመስረት አስችሏል ፤ብለዋል።