1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህላዊ እሴቶች ሚና ለሰላም

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

"ሃሳባችንን እንደ ኋላ ቀር የማየት አባዜ ሰፍኗል፡፡ ትውልዱ ጋር አውቃለሁ ባይነት ከፋ፡፡ ይህ ደግሞ አይሆንም፡፡ አሁንም ላለው ችግር እኛ የምንለው ተቀባይነት አጣ እንጂ ከመናገር ሀሳብ ከመስጠት ታቅበን አናውቅም”

https://p.dw.com/p/4fNtv
የኦሮሚያ አባገዳዎች
የኦሮሚያ አባገዳዎችምስል Seyoum Getu/DW

ሃሳባችንን እንደ ኋላ ቀር የማየት አባዜ ሰፍኗል


አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ የቱለማ  ኦሮሞ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዋና ጸሃፊ ናቸው፡፡ ስለኦሮሞው የገዳ ስርዓት እሴት ሲያነሱ ስርዓቱ ለሃቅ እንጂ ለውሸትና ማስመሰል ስፍራን የማይሰጥ፤ ፍትህን የሚያስፍን በመሆኑ ህዝቡም ሲመራበት እንደነበር ያወሳሉ።  አባገዳ ጎበና ሆላ አሁን አሁን የዚያ እሴት መሸርሸር ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት ሚናውን እንዳይጫወት ትልቁ ተግዳሮት ተደቅኖበታል ይላሉ፡፡ “የኦሮሞን ህዝብ አሁን የምንገኝበት እንዲህ ያለ ችግር ፈጽሞ አጋጥሞት አያውቅም፡፡ እንደ ህዝብ ፈጽሞ እንዲህ ያለ ቅርቃር ውስጥ ገብተን አናውቅም፡፡ የኦሮሞ የገዳ ስርዓት ኦሮሞ በአዋቂዎች እንዲመራ የሚፈቅድ በመሆኑም ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ስርዓቱ የአስተዳደር ሁኔታዎችን እንደአስፈላጊነቱ ከፋፍሎ ያስቀመጠም እንደመሆኑ ጥቅሙ ጉልህ ነበር፡፡ እኛ አሁን በገዳው በእጃችን ባለው ሃላፊነት ከተሾምን ጊዜ ጀምሮ ህዝቡ በፖለቲካና በኢኮኖሚው እንዳይበደል ብዙ ብዙ ብለናል፡፡ ግን እኛ የምናቀርበው ሃሳብ ምን ያህል ተቀባይነት እያገኘ ነው ብትለኝ ምንም ነው መልሴ፡፡ የምናቀርበውን ሀሳብ የሚቀበል ትውልድ የታለ?፡፡ ሃሳባችንን እንደ ኋላ ቀር የማየት አባዜ ሰፍኗል፡፡ ትውልዱ ጋር አውቃለሁ ባይነት ከፋ፡፡ ይህ ደግሞ አይሆንም፡፡ አሁንም ላለው ችግር እኛ የምንለው ተቀባይነት አጣ እንጂ ከመናገር ሀሳብ ከመስጠት ታቅበን አናውቅም” ብለዋል፡፡

የጦርነት አውዳሚ ገጽታ በከፊል
የጦርነት አውዳሚ ገጽታ በከፊልምስል Tiksa Negeri /REUTERS


የሃይማኖት እና ባህል መሪዎች ሚና መደበላለቅ
ይህን ሃሳብ የሚጋሩት የስላሌ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ የታሪክ ተመራማሪ ዶ/ር ብራቱ ቀነዒ አሁን ለገጠመን ማህበረሰባዊ ቀውስ መሰረታዊ ምክንያቱ ሁለት ነው ይላሉ፡፡ ቀዳሚው የሃማኖት አባቶችና ባህላዊ መሪዎችን የሚያደምጥ ትውልድ መጥፋቱ ነው ይላሉ፡፡ “አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ስራቸውን የሚሰሩት ስናደምጣቸው ብቻ ነው፡፡እነሱ ጠመንጃ የላቸው በምን ያስገድዳሉ፡፡ እነዚህን የሚያደምጥ ማንነቱን አክባሪ ማህበረሰብ ነው እያጣን የመጣነው አሁን፡፡ መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ እነሱን እየሰማ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ ቆም ብለን እራሳችንን መመልከት አለብን፡፡ ሰው ጥቅም ፈላጊ እራስ ወዳድ ሆኗል እንጂ እንኳን ለኛ ለሌላውም የሚተርፍ እሴትና አዋቂዎች አሉን፡፡ እነሱን ቆም ብለን ካላደመጥን አሁን የምንጓዝበት መንገድ መፍትሄ የለውም” ነው ያሉት፡፡
ዶ/ር ብራቱ ሁለተኛው  ችግር  ከባህል እና ሃይማኖት መሪዎች የማይጠበቅ መስማት ነው በማለት ሐሳባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ “ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ብቻ ብንመለከት ከማህበረሰቡ ባሻገር ከሃማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች መካከልም ችግር ያለባቸው አሉ፡፡ ጦርነት ጠልና ማህበረሰቡ ስያጠፋ የሚሞግት ሳይሆን ከመንጋው ጋር ሆ ብለው ደም ማፋሰሱን የሚደግፉ አባቶች ገጥመውናል፡፡ አሳዛኝ ነው ይሄ፡፡ ተደማመጡ ተወያዩ የሚል ምክር ብቻ ነበር ከነሱ የሚጠበቀው፡፡ ሌላው የገባንበትን ቀውስ ያመጣው ይሄ ነው” ብለዋል፡፡


የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚና እና ጥረት
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዶቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ግን በግለሰብ ደረጃ የሃይማኖትን አካሄድ የሳቱ ቢኖሩም እንደ ሃይማኖት ተቋም ጦርነት አስቀድሞም እንዳይከሰት ብዙ ተደክሟል ይላሉ፡፡ “የእኛ የሃማኖት ተቋማት ሃሳብ ሰላም ነው” የሚሉት ቀሲስ ታጋይ በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዳይከሰት አስቀድሞ በተቋማቸው በኩል ብርቱ ያሉት ጥረት መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡ ይሁንና በወቅቱ ሰሚ ማጣታቸው ተፋላሚዎችን ለማይቀረው ጦርነት ዳርጎ የሚሊዮኖችን ደም አፋሶ ለቁጥር የሚታክት ንብረትም አውድሟል፡፡ 
የሃማኖት ተቋማት ሚና ስለሰላምና በጎ ሁሉ መስራት ነው ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊው አንዳንድ ጊዜ በሃይማኖት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የሚያስተላልፉት ከሃይማኖት መርህ ውጪ የሆኑ ሀሳቦች በግለሰቦቹ እንጂ በተቋም አይን ሊታዩ የማይገባ ብለዋል፡፡  
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር