1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባህላዊ ጎዳና ጀፎሮ/ጀፏረ/

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2011

አንድ ኅብረተሰብ ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍል የሚለየው የራሱ መገለጫ የሆኑ እሴቶች ባለቤት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ የሚከተለው የህይወት ፍልስፍናና የአኗኗር ዘይቤውን መነሻ በማድረግ ሲሆን በዚህም ውስጥ የኅብረተሰቡ ባህላዊ፣ ትውፊታዊ፣ ሥነ-ጥበባዊ፣ ቁሳዊና ሀይማኖታዊ ክዋኔዎቹ በዋንኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

https://p.dw.com/p/38i0P
Meskel Urlaubsort Äthiopien
ምስል DW/R.Kifle

ባህሉንና ትውፊቱንም ይገልፅበታልh።

የጉራጌ ኅብረተሰብም ልክ እንደሌሎቹ የአገራችን ብሔር ብሄረሰቦች ውብና ማራኪ ባህልና ወግ ባለቤት ነው። ከነዚህ ውስጥ ብሔረሰቡ በዋነኛነት ከሚታወቅባቸው ሀብቶቹ መካከል የመንደር አመሰራረቱ ነው። የጉራጌ የመንደር አመሰራረትም መሰረት የሚያደርገው ጀፎሮ/ጀፏረ ሲሆን ይህም አረንጓዴ ሳር ለብሶ ውብና ማራኪ ገጽ ያለውና ባህላዊ ጎጆ ቤቶች ታጅቦ በሁለት መንደሮች መካከል በትይዩ  የሚገኝ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ፣ መተላለፊያ፣ መግቢያና መውጫ የሆነ ሰፊ መሬት ነው።

በጉራጌኛ ጀፎሮ ማለት ባህላዊ አውራ መንገድ ማለት ነው። የጉራጌ የመንደር አመሰራረት ያኔ እንደዛሬው የኢንጅነሪንግ ጥበብ ባልተስፋፋበት ዘመን የብሔረሰቡ አባቶች የጥበብ አሻራ ያረፈበትና ዛሬ የደረስንበት የስልጣኔ እርከን የኢንጂነሪንግ ጥበብ የጉራጌ አባቶች ከረጅም ዘመናት በፊት ሲተገብሩት መቆየታቸውንም ጭምር ያሳያል፡፡

አባቶች ምንም አይነት የዘመናዊ ምህንድስና ቀለም ሳይቆጥሩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የቀየሱበት የመንገድ አይነት ነው። ለጉራጌ መንደሮች ትልቅ ውበት መላበስ አንዱ ምክንያቱ ባህላዊ ጀፎረ ነው። ለጉራጌ ኅብረተሰብ ጀፎሮ የዓይን ብሌን ነው ብለን ብንናገር ማጋነን አይደለም። ጀፎሮ በጉራጌ ኅብረተሰብ ዘንድ ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አሉት። ሰው ሲሞት የለቅሶ ስነ ስርአት ይከናወንበታል። በሰርግ የሙሽሪትና ሙሽራው አጃቢዎችና ዘመዶች በባህላዊ ዘፈን በማጀብ ይሞጋገሱበታል። ሕጻናት ይጫወቱበታል። ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወቱበታል። በቅሎ እና ፈረስ ይገራበታል። ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርአት ይከናወንበታል። ወንዶችና ሴቶች የደቦ ስራ ለመስራት ቁጭ ብለው ይመካከሩበታል። በመስቀል በአል አዛውንቶችና ወጣቶች የበአሉ እለት የደመራ ሥነ- ስርአት ያከብሩበታል ፤ ተሰብስበው ይመራረቁበታል። አዛውንቶች ተቀምጠው ጊዜያቸውን ያሳልፉበታል።

ለሰው መሰብሰቢያ፣ ከብቶች ጠዋት ከመሰማራታቸው፤ ማታ ደግሞ ወደየበረታቸው ከመግባታቸው በፊት የጋራ ማቆሚያ ስፍራ ከመሆኑም ባሻገር ለመንደሮች ውበትም የላቀ ሚና ይጫወታል። አቶ ፍቅሬ በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ እንድብር ከተማ ይኖራሉ። ስለ ጀፎሮ የሚያውቁትን እንዲህ ይተርካሉ። የመሬት ልኬቱ በአካባቢው በተመረጡ የባህል ሽማግሌዎች ወይም የመሬት ልኬት ዳኞች አማካኝነት ይለካል። ከ60 ሜትር በላይ ስፋት ያለው ይሆናል።

Meskel Urlaubsort Äthiopien
ምስል DW/R.Kifle

ጀፎሮ ለብሔረሰቡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ በርካታ ክፍለ ዘመናት የተሻገረ ሲሆን ስለ አጠቃቀሙም ቢሆን የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑ አባቶች ተሰባስበው በመምከር በባህላዊ መልክ የሚዳኝበትን ህግ አርቅቀው ተግባራዊ በማድረጋቸው ጀፎሮ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ መስጠት ያለበትን ሰፊ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ጀፎሮ ባለቤትነቱ የሕዝብ ሆኖ ማንኛውም ሰው የሚተላለፍበት ሲሆን ደህንነቱ የሚጠበቀውም በአካባቢው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ከዘመናት ጀምሮ ጉራጌ በጀፎሮ ደስታውንና ሐዘኑን ሲገልፅበት የመጣ ሲሆን አሁን እየገለፀበት ይገኛል፡፡ቂም በቀሉን ያበርድበታል ስለሰላሙ ይመክርበታል ስለሕይወቱ ይዘክርበታል፡፡ የተበዳዮችን እንባ ያብስበታል ፍትህ የተነፈጉ አካላት ካሉ ፍትህ ያሰፍንበታል፡፡ እምነቱን ይገልፅበታል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ይከውንበታል፡ ባህሉንና ትውፊቱንም ይገልፅበታል፡፡ 

አቶ ክፍሌ ኃብቴ ይባላሉ በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በአካባቢያቸው ያለውን ጀፎሮ 60 የሚሆኑ አባወራዎች ይጠቀሙበታል። ማንኛውም መንገደኛ በሚተላለፍበት ወቅት ሲደክመው ማረፊያ ነው። በጉራጌ በሁሉም የነዋሪው አካባቢ ጀፎሮ እንዳለ ነግረውናል።

በጀፎሮ ላይ ያለ ማንኛውም ነገር የግል መጠቀሚያ እንደማይሆንም አቶ ክፍሌ ነግረውናል። ምክንያቱም የጋራ መጠቀሚያ በመሆኑ ነው። አፈር ሆነ ምንም ነገር መጠቀም አይቻልም። ጀፎሮ ላይ የተተከለ የዛፍ ቅጠል እንኳን ቢሆን ወደ ቤት ይዞ መግባት የተከለከለ ነው በጉራጌ ባህል።

 

ነጃት ኢብራሂም

ማንተጋፍቶት ስለሺ