1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቢቢ መሔጃቸዉ ይሆን?

ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2012

ጠረጴዛዉ ላይ ከዶሮ አርስቶ እስከ አሳ ጥብስ፣ ከነጭ ወይን እስከ ቀዩ፣ ከኬክ እስከ ጣፋጭ፣ ከወይራ ፍሬ፣ እስከ ቱፋሕ---ምግብ፣ መጠጥ እትክልቱ ዓይነት ባይነት ደረደሩ።ከትልቁ ጠረጴዛ ጀርባ ግዙፍ አሻንጉሊት ጎለቱ።ጥቁር ሱፍ ከቀይ ከረባት ጋር ለብሷል።ሸበቶ አጭር ሉጫ ፀጉሩ ወደ ጎን ተኝቷል።ቁርጥ ሰዉዬዉን።ቢኒያሚን ኔታንያሁን።ቢቢን። 

https://p.dw.com/p/3gMMV
Israel Protest gegen Netanjahu | Jerusalem
ምስል picture -lliance/AP Photo/O. Balilty

የኔታንያሁ ዘመነ ሥልጣን ስንት ይቀረዉ ይሆን?

ያቺን በጠላት የተከበበች፣ ወጣት፣ትንሽ ግን ከከበቧት ሰፋፊ ቱጃሮች ይበልጥ የከበረች፣ በጦር የደረጀች፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ኃያል ሐገርን የሳቸዉን ያክል ለረጅም ጊዜ የመራ ጠቅላይ ሚንስር የለም።እድሜያቸዉ ከትንሿ ሐገራቸዉ የነጻነት ዕድሜ ትንሽ ያንሳል።ሐገራቸዉ 72 ዓመት እሳቸዉ 71 ፈሪ።ቢንያሚን ኔታንያሁ።ቢቢ።ለረጅም ጊዜ በመምራት ቀዳሚም-አቻም እንደሌላቸዉ ሁሉ፣ስልጣን ላይ እያሉ በመከሰስም የመጀመሪያዉ ናቸዉ።የመጀሪያ የሆኑባቸዉ ሥልጣን እና ክስ በሕዝባቸዉ ዘንድ ያሳደሩት መሰላቸትና ጥርጣሬ ያሰለለዉን ስልጣናቸዉን መጋቢት ላይ ጨርሶ ከመበጠስ ያዳነዉ ኮቪድ 19ኝ ነበር።አሁን ግን የመቅስፍቱ መጠናከር፣ከመሰላቸቱና ጥርጣሬዉ ጋር ተዳምሮ ሕዝባቸዉን ለተቃዉሞ ካሳደመባቸዉ፣ ሁለተኛ ወሩን ሊደፍን ጥቂት ቀረዉ ።ተቃዉሚዉ እየበረከተ፣ ጥያቄዉ እየመረረ ፤በቁኝ ሒዱልኝ፣ እያለ ነዉ።ተቃዉሞዉ መነሻ፣ፖለቲካዊ ስብዕናቸዉ ማጣቀሻ፣መሔድ-አለመሔዳቸዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ። 

የቴል አቪብ ከያኒያን ትርዒት።ሮብ።ከትልቁ የራቢን አደባባይ ሰፊ፣ረጅም የምግብ ጠረንጴ ዘርጉ።አግድም 10 ሜትር ይረዝማል።ጠረጴዛዉ ላይ ከዶሮ አርስቶ እስከ አሳ ጥብስ፣ ከነጭ ወይን እስከ ቀዩ፣ ከኬክ እስከ ጣፋጭ፣ ከወይራ ፍሬ፣ እስከ ቱፋሕ---ምግብ፣ መጠጥ እትክልቱ ዓይነት ባይነት ደረደሩ።ከትልቁ ጠረጴዛ ጀርባ ግዙፍ አሻንጉሊት ጎለቱ።ጥቁር ሱፍ ከቀይ ከረባት ጋር ለብሷል።ሸበቶ አጭር ሉጫ ፀጉሩ ወደ ጎን ተኝቷል።ቁርጥ ሰዉዬዉን።ቢኒያሚን ኔታንያሁን።ቢቢን። 
ጥቅል ትርዒቱን እየሱስ ክርስቶስ ለደቀ-መዛሙርቱ የፀሎተ ሐሙስ ምሽት በጋበዘዉ ማዕድ ስም ሰየሙት።ከያኒያኑ።«የመጨረሻዉ ዕራት» ብለዉ። 
                                        
«የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ከጠረፄዛዉ ጀርባ መሐል ላይ ተቀምጠዉ ምግብና መጠጡን በሙሉ ራሳቸዉ ብቻ ሲያሻምዱና ሲመጥጡ ታያለሕ።አሁን ምግቡን በልተዉ ጨርሰዋል።የድሕረ ምግብ ማወራረጃዉ (ዲዘርት) ነዉ የቀራቸዉ።የመጨረሻዉ ሰዓት ላይ መድረሳቸዉን ለማመልከት ነዉ።የእስራኤልን ዴሞክራሲ ለማዳን አንድ ነገር  ከምናደርግበት ደቂቃ ላይ ደርሰናል።»
ይላል ከከያንያኑ አንዱ ኢታይ ዛላይት።
እስራኤልን ለመምራት አንድም እንደ ዴቪድ ቤን ጎርዮን የዓለም አቀፉ ፅዮናዊ ንቅናቄ እዉቅ ታጋይ፣ ሁለትም እንደ ሺሞን ፔሬዝ አንደበተ ርቱዕ፣ በሳል ዲፕሎማት፣ አለበለዚያ እንደ ይትሳቅ ራቢን ወይም ኤሁድ ባራክ ምርጥ ጄኔራል መሆን አስፈላጊ ነዉ።ግድ ግን ዓይደለም።
ቤኒያሚን ኔታንያሁ (ቢቢ-በቅፅል ስማቸዉ) እንደ ቤን ጎሪዮን፣ እንደነ ሞሼ ሻሬት፣ ወይም እንደ ጎልዳ ሚር  የፅዮናዊ ንቅናቄ አባል ለመሆን፣ ለእስራኤል ምሥረታ ለመታገልም አይችሉም ነበር።አልተወለዱም።
ጥቅምት 1949 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ተወለዱ። 
እርግጥ ነዉ በወጣትነታቸዉ የእስራኤል ኮማንዶ ጦር ባልደረባ ሆነዉ ከ1967 እስከ 1973 ድረስ ከግብፅ፣ከዮርዳኖስ፣ከሶሪያና ከሊባኖስ ጋር በተደረጉ ዉጊያዎች፣ ፍልስጤሞች ላይ በተወሰዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች ተካፍለዋል።ከሻምበልነት የዘለለ ማዕረግ ግን የላቸዉም።እና የነ ኢትሳቅ ራቢንን፣ የነ ኤሁድ ባራክን ወይም የነ አሪየል ሻሮንን ዓይነት የጦር ሜዳ ጀግንነት፣ የምርጥ አዋጊ ጄኔራልነት  ማዕረግ፣ክብር ዝንም የላቸዉም።
Massachusetts Institute of Technology (MIT) በተባለዉ በአሜሪካዉ ምርጥ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ሆነዋል።እንደነ ሼሞን ፔሬስ ከልጅነቱ ጀምሮ በአደባባይ የመናገር ርቱዕነት፣ የማስተባበር፣ የመደራደር ብልሐት፣ ፖሊሹን ከሩሲያዉ፣እንግሊዝኛዉን ከፈረንሳይኛ፣ ይዲሹን ከሒብሩ እያቀያየሩ፣ እያቀለጣፉ የመናገር ልዩ ክሒል ግን የላቸዉም።
እና እስራኤልን ለመምራት  ሶስቱንም አይደሉም።ስሶቱንም አለመሆናቸዉ ግን በ1996 በተደረገዉ ምርጫ ለጠቅላይ ሚንስትርነት ከመወዳደር አላገዳቸዉም።ተወዳደሩ።
ተቀናቃኛቸዉ ከ1984 እስከ 1986 ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት፣ በ1995 አይሁድ አክራሪ  የገደላቸዉን ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢንን ተክተዉ በድጋሚ ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት፣ ከፍልስጤሞች ጋር በመደራደራቸዉ ከራቢን እና ከሊቀመንበር ያሲር አረፋት ጋር የ1994ቱን የዓለም የሰላም ኖቤል የተሸለሙት የ72 ዓመቱ አንጋፋ ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ነበሩ።ሼሞን ፔሬስ።
በጦር ሜዳ፣ በፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ምንም ወይም ትንሽ የሚታወቁት  ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ የምርጫ ዘመቻቸዉ ዓብይ መርሕ ያደረጉት የራቢን-ፔሬስን ግዛትን ለሰላም የሚል ሰላማዊ መርሕን ጨርሶ የሚቃረን ነበር።የፍልስጤሞችን  የመንግስትነት ጥያቄን አይቀበሉም።
                                     
«የፍልስጤሞች ምልክት በየትኛዉም አቅጣጫ ጥቂት ማይል ርቀት ላይ ይገኛል።ሙሉ መንግሥት ማለት የጦር ኃይል ያለዉ መንግስት፣ ከኢራቅ ወይም ከኢራን ጋር የሚተባበር ሊሆን ይችላል።»
በምረጡኝ ዘመቻቸዉ ወቅት ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባንደኛዉ ደግሞ ኤቢሲ ኒዉስ እንደዘገበዉ «ከሶሪያ ጋር ሰላም ማስፈን እንፈልጋለን» አሉ።እስራኤል በኃይል የያዘችዉን የሶሪያን ግዛት መመለስን ግን «ሰላም» አይገዛም።
«እስራኤል የጎላን ኮረብታን ብትለቅ ሰላም ይሰፍናል የሚለዉ ሐሳብ እዉነታዉን ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ነዉ።በ20ኛዉ ምዕተ-ዓመት ሰላምን አትገዛም።»
የአዲሱን ቀኝ አክራሪ ወጣት ትዉልድ ልብን ማርከዉ፣ የራቢን-ፔሬስን የሰላም መርሕን አጣጥለዉ አሸነፉ።ግንቦት 1996።በእስራኤል የእስከዛሬ ታሪክ የመጀመሪያዉ ወጣት ጠቅላይ ሚንስትር ሆኑ።46 ዓመታቸዉ ነበር።
በ1999 በተደረገዉ ምርጫ ግን የራቢን-ፔሬስን የሰላም መርሕ በሚቃነቅኑት በቀድሞዉ ጄኔራል ኤሁድ ባራክ ተሸነፉ።ከሽንፈት በኋላ ለጥቂት ዓመታት  ከፖለቲካ ርቀዉ ነበር።በ2009  በተደረገዉ ምርጫ ግን እንደገና ጠቅላይ ሚንስትር ሆኑ። ዛሬም ጭምር።
ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን እንደያዙ የቀጠሉት ሶስቴ  በተደረጉ ምርጫዎች ግልፅ አሸናፊ ባለመኖሩ በተጠባባቂነት ነበር።ዘንድሮ መጋቢት በተደረገዉ ምርጫ ደግሞ ከዋና ተፎካካሪያቸዉ ከቤኒ ጋንትስ ጋር ተቀራራቢ ድምፅ በማምጣታቸዉ የመሪነት ስልጣኑን ለሁለት ለመካፈል ተስማምተዉ ነዉ።
ጋንትስ በሙስና ከተከሰሱት ኔታንያሁ ጋር ስልጣን መከፋፈሉን አልፈለጉትም ነበር።ይሁንና ለኔታንያሁ አንድ ጋዜጠኛ እንዳለዉ ፈጣሪ በኮሮና አሳብቦ ጣልቃ ገበላቸዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት በማስጋቱ ሌላ ምርጫ ከመጥራት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን በፍርርቅ ለመያዝ ሁለቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ተስማሙ።
በስምምነቱ መሠረት ኔታንያሁ የመጀመሪያዉን፣ ጋንትስ ደግሞ ተከታዩን 18 ወራት በጠቅላይ ሚንስትርነት ይመራሉ።የእስራኤል ሕግ በተለይም ሕዝቡ የረጅም ዘመኑን ጠቅላይ ሚንስትር የሚታገስ አለመስሉ ነዉ የኔታንያሁ ጭንቀት።
የእስራኤል ፖሊስ ከ2016 ጀምሮ በኔታንያሁና አባሪ ተባባሪዎችቻቸዉ ላይ ያደረገዉ ክትትል፣ መረጃ ማሰባሰብና ምርመራ ተጠናቅቆ የሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለፈዉ ሕዳር ቀኝ አክራሪዉን ፖለቲከኛ እምነትን በማጉደል፣ ጉቦ በመቀበል፣ እና በሙስና ክስ መስርቶባቸዋል።
ባለፈዉ ግንቦት እየሩሳሌም ያስቻለዉ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ክሱን ግራ ክንፎች ቀኝ ፖለቲከኞችን በምርጫ ማሸነፍ ሲያቅታቸዉ «የሸረቡት ሴራ» በማለት ለማጣጣል ሞክረዋል።የፍርድ ቤቱ ሙግት እስከ መጪዉ የጎርጎሪያኑ ዓመት ድረስ በተሰጠዉ ቀጠሮ  ቀዝቀስ ሲል ሕዝባቸዉ በተራዉ ያመፅባቸዉ ያዘ።
                                 
ተንታኞች እንደሚሉት የስራ አጡ ቁጥር ከ20 ከመቶ በላይ ነዉ።በኮሮና ተሕዋሲ የሚለከፈዉ ሰዉ ቁጥር ባማካይ በየቀኑ 2000 ደርሷል።የስራ አጡ ቁጥር በናረበት፤የሕዝቡ ጤና ለአደጋ በተጋለጠበት በዚሕ ወቅት የተመሠረተዉ ጥምር መንግሥት 36 ሚንስትሮች እና 16 ምክትል ሚንስትሮች አሉት።
እስካለፈዉ ግንቦት ድረስ እስራኤል የነበሯት ሚንስትሮች ከ20 እስከ 23 የሚደርሱ ነበሩ።አዲስ ለተሾሙት ሚንስትሮች ደሞዝና አበል  የእስራኤል ሕዝብ ከሚከፍለዉ ቀረጥ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ከ254 ሚሊዮን ዶላር ማዉጣት አለበት። ተደራራቢዉ ችግርና ገዳብ ያጣዉ ወጪ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሙስና ሕዝቡን በተለይ ወጣቱን ለአደባባይ ሰልፍ ለማሳደም ከበቂ በላይ ነዉ የሆነዉ።እየሩሳሌም፣ ቴል አቪቭ፣ ኬስኤሪያ እና በሌሎች ከተሞች በየአደባባዩ ቢቢ «በቁን በቃንዎት» ማለት ከጀመረ ሁለተኛ ወሩን ያዘ።
                              
ኔታንያሁ  ተቃዋሚዎቻቸዉን ፀረ-ዴሞክራሲ፣ መገናኛ ዘዴዎችን  ሐላፊነት የጎደላቸዉ፣ ፖለቲከኞችን ደግሞ ዝምታን የመረጡ ብለዋቸዋል።
 «ተቃዋሚ ሰልፈኞች ችቦ ይዘዉ ሲመጡ፣ ጓዳ ሰራች ፈንጂ በጠቅላይ ሚንስትሩ መኖሪያ ቤት ላይ ለመጣል ሲያስፈራሩ በእዉነቱ መወቀስ የሚገባችሁ እናንተ ናችሁ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ባልፎር (መኖሪያቸዉ ነዉ)  ከሌለ ተቃዉሞ ሰልፍ ማድረጉ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ።ጠብ ጫሪና አደጋ ጣይ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ፣ ከትናንት ወዲያ ጭምር ጠቅላይ ሚንስትሩንና ቤተሰቦቹን ለመግደል ሲሞከር መገናኛ ዘዴዎች ጉዳዩን ችላ ብለዉ ይዘግባሉ፣ ፖለቲከኞቹ ደግሞ ዝም ብለዋል።»
ሁሉንም ወቀሱ።ማን? ምን ቀራቸዉ? «ሁሉም ግን የቢቢ የመጨራሻዉ ዕራት እንዲሆን ተስፋ አለዉ» ይላል የቴል አቪቩን ትርዒት የጎበኘዉ ነዋሪ።«ይሕ ተቃዉሞ የቢቢ የመጨረሻ  እራት እንዲሆን ሁሉም ተስፋ አድርጓል።የሙስናዉ ክፋት አለቅጥ በተትረፈረፈዉ ስጋ፣ በወተት፣ በጣፋጭ ና አትክልቶች  ተመስሏል።ይሕን ሳይ በጣም አስከፊ የሆነ ዘመን እንዳስታዉስ ያደርገኛል።»
አስከፋም አላስከፈ ዘመነ-ኔታንያሁ እንደነ ቤን ዓሊ፣ እንደነ ሙባረክ እንደነ---- ያበቃ ይሆን?

Israel, Tel Aviv I Protest I COVID-19
ምስል Getty Images/AFP/J. Guez
Israel I Premierminister Benjamin Netanyahu
ምስል Reuters/Pool/T. Shahar
Israel I Premierminister Benjamin Netanyahu
ምስል Reuters/Pool/T. Shahar
Israel Protest gegen Netanjahu | Jerusalem
ምስል AFP/M. Kahana

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ