1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን 20 ጉባኤ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2011

መሪዎቹ ቦኒስ አይሪስ የገቡት የሶሪያን ዉድመት፤ የየመኖችን ዕልቂት፤ የጋዜጠኛ ኻሾጂን ግድያን እንደ ሁለተኛ ርዕሥ ከየዶሴያቸዉ  ዶለዉ  ነዉ።ይሁንና ከራሳቸዉ ከፑቲን ቀጥሎ ግን ከመራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እኩል፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ጠብን ጉዳዩ ያደረገ መሪ ከነበረ-ኢማኑኤል ማክሮን ቀዳሚዉ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/39Nad
Argentinien G20 Gipfel in Buenos Aires l Plenarsaal
ምስል AFP/Getty Images

ቡድን 20 ስምነት-እና ልዩነት

በየጉባኤ-ድርድሩ የአዉሮጳ ሕብረትን አርማ ከፍአድርገዉ የሚያዉለበልቡት መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከበርሊን ቦኒስ አይሪስ ለመድረስ «ኡራ» ወጡበት።ጀርመናዊዉ «ምስኪን አንጊ» እያለ መሪዉን ሲያፅናና የአዉሮጳ ሕብረትን አርማ ከሜርኪል ለመቀበል ሳይከጅሉ አይቀርም የሚባሉት ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ቦኒስ አይሪስ ላይ የክሪሚያን እሳት ለማጥፋት ሲባትሉ ፓሪስ ሲነድ ጠበቃቸዉ።ሁለቱ «የተገለሉ» የተባሉት ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን እንደ ጥብቅ ወዳጅ ጎረምሳ «bro-five» በሚባለዉ ስልት ተጨባበጡበት።ሁለቱ የዓለም ቱጃር ሐገራት መሪዎች የገጠሙትን የንግድ ጦርነት ለመግታት «ተኩስ አቁም» አወጁበት።የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ።ጉባኤዉ መነሻ፤ የጎንዮሽ ስብሰባዉ ማጣቃሻ፤ ዉጤቱ መድረሻችን ነዉ።

በርሊን፣ ሐሙስ ማታ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የጀርመን ከፍተኛ የልዕካን ጓድ ዕቅድ አርብ ሲነጋጋ ቦኒስ አይሪስ ለመግባት ነበር።ሜርክል እና ተከታዮቻቸዉ ቦኒስ አይሪስ ላይ የሚሉ፤የሚያደርጉትን እያሰላሰሉ ከግዙፉ ካዉሮፓላን ተሳፈሩ።በዝነኛዉ የጦርነት ማግሥት መራሔ-መንግስት በኮንራድ አደናወር ስም-የተሰየመዉ A340-300 ለመሪ እንዲመች ተደርጎ የተሰራ ግዙፍ-ልዩም ነዉ።ምቹ መቀመጫ፣ ፅሕፈት ቤት፤መገናኛ፤ አልጋ፤ሁሉም አለዉ።ከሁሉም በላይ ሚሳዬል ቢተኮስ ቀልቦ-የሚያከሽፍ፣ የሚተናኮል አዉሮፕላን ቢመጣ አነፍንፎ በፍጥነት መስመር የሚቀይር ወይም በቀርሶ የሚጥል መሳሪያም አለዉ።

ከበርሊን ተነሳ።ባለሥልጣናቱ የየመቀመጫ ቀበቷቸዉን ቁልፍ ሲያጠባብቁ አብራሪዉ የመገናኛ ቁልፉን ተጫነ-አይሰራም።እንደገና ተጫነ-የለም።ደገመ አልሆነም።እረዳቱ ሞከረ።አይሰራም።የኤሌክትሮኒክሱ መሳሪያ ተበላሽቷል።ምርጫ የለም።ካፒቴኑ ለመጠባበቂያ የተሰጠችዉን የሳተላይት ስልክ አስንስቶ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መናገር ያለበትን ተናገረ።ቀጥሎ ለመንገደኞቹ።አስልሶ የአዉሮፕላኑን አፍንጫ ወደ ኔዘላንድስ አቅጣጫ አዞረ፣-ከዚያ ቅርብ ወዳለዉ አዉሮፕላን ማረፊያ።ኮሎኝ-ቦን፣ ኮንራድ አደናወር አዉሮፕላን ማረፊያ።

Argentinien G20 Gipfel in Buenos Aires - Xi Jinping und Donald Trump
ምስል Reuters/K. Lamarque

ኮንራድ አደናወር አዉሮፕላን-ኮንራድ አደናወር አዉሮፕላን ማረፊያ አረፈ።የልዩ አዉሮፕላን እና የአዉሮፕላን ማረፊያዉ ስሞች መገጣጠም ሳያስደምም አይቀርም።በጣም የሚያስገርመዉ ግን የልዩዉ አዉሮፕላን ልዩ ብልሽት ነዉ።የጀርመን አየር ኃይል የበረራ ጉዳይ አዛዥ ጌዲዮ ሔንሪሽ ብልሽቱን ግራ አጋቢ ይሉታል።

                                  

«አዉሮፕላኑ፣ በመሠረቱ ሁሉም (ነገሩ) ተጠግኗል።ሁሉም ተሞክሯል።ሁሉም ይሰራ (ትክክል) ነበር።እንዲያዉ ዛሬ እንደሆነዉ ሁሉ፣ ምንጊዜም ሊያጋጥም የሚችል የአካላት አለመስራት ነዉ።»

ሜርክል ማለት፣ አለማለታቸዉን አናወቅም።የሆነዉ ግን በርግጥ «እንዳሰቡት አይሆን» የሚያሰኝ ነዉ።ቦን አድረዉ፣ የስጳኝን የመንገደኞች አዉሮፕላን ተኮናትረዉ በፊት ካሰቡት አስራ-ሁለት ሰዓት ዘግይተዉ ደረሱ።

ከዓመት በፊት (ኃምሌ 2017- ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሐቡርግ-ጀርመን ላይ የተሰየመዉ ጉባኤ አስተናጋጅ፣ አንፀባራቂ ኮኮብም የነበሩት ሜርኪል ዘንድሮ «የቤተሰብ»  ለሚባለዉ የቡድን ፎቶ እንኳን አልደረሱም።ብዙ ቀጠሮዎቻቸዉንም ማራዘም-ወይም መሰረዝ ግድ ሆኖባቸዋል።

ይሁን እና  ጉባዉ እንደተጀመረ ባረፉት በቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ሐዋርድ ቡሽ (ትልቁ) ሞት ሐዘን ገብቶኛል ያሉትን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ለማፅናናት ለማነጋገርም የተረፋቸዉ ጊዜ በቂ ነበር።ትራምፕ ቀረጥ በመጨመራቸዉ ሰበብ ከዩናትድ ስቴትስ ጋር የንግድ ጦርነት ከገጠመች ከቻይና ፕሬዝደንት ቺ ሺፒንግ ፤ የዩክሬን መሪዎችን ደፈላልቆ ለመጣል ሳያስቡ አይቀርም ከሚባሉት ከፕሬዝደንት ፑቲን፤ ካስተናጋጁ ከአርጀንቲናዉ ፕሬዝደንት ሞሪቺዮ ማስሪይ ጋርም ተነጋግረዋል።

Argentinien G20 Gipfel in Buenos Aires l Plenarsaal
ምስል picture-alliance/dpa/G20 Argentina

ከየመሪዎቹ ጋር ባደረጉት ዉይይት፣ እንዳዲስ የተቀጣጠለዉ የዩካሬን እና የሩሲያ ጠብ ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይንር አቻዎቻቸዉን ለማሳመን ያደረጉት ጥረት የተስፋ ጭላጭል ፈንጥቋል።«ስለ ሶሪያ ሁኔታ በተለይም ስለ ኢድሊብ ተነጋግረናል።አዞቭ ባሕር ላይ ስላለዉ ሁኔታም ተነጋግረናል።ምክንያቱም እዚያሕ አዞቭ ባሕር አካባቢ ያለዉ ዉጥረት ሊወገድ ይገባል።እኛ የጠቆምነዉ እና በሌሎቹም የተደገፈዉ ሐሳብ፣ የኖርማንዲ አምሳያ-በሚባለዉ ስልት አማካይነት የሁሉም ሐገራት አማካሪዎች ይነጋገሩ-የሚለዉ ነዉ።ማለትም፣ የፈረንሳይ፤ የጀርመን፤የሩሲያ እና የዩክሬን (ባለስልጣናት) በሚያደርጉት የጋራ ስብሰባ አሁን ባለዉ ሒደት ላይም ይወያያሉ።ይሁንና  ግልፅ ማድረግ የምፈልገዉ ነገር፣ በአዞቭ ባሕር ላይ ወደ ዩክሬን የባሕር ጠረፍ እና ከተሞች በነፃነት መጓጓዝ እንደሚቻል ዋስትና ሊሰጥ ይገባል።ይሕን በሚመለከት ከ2003 ጀምሮ የስምምነት መሠረት አለ።ሩሲያ ይሕን የስምምነት መሠረት ማክበር አለባት።»

የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ግን ከዝግ በር ጀርባ የተስማሙበትን ወይም ተስማምተዉበታል የተባለዉን ባደባባይ አልደገሙትም።ፑቲን ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ከኪየቭ ባለሥልጣናት ጋር የገጠሙት እሰጥ አገባ ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ባሉት መንገድ የሚቃለልም አይመስልም።

«አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የዩክሬን ባለሥልጣናት ግጭቱን ለመፍታት፤ በተለይም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት  ጨርሶ ፍላጎት የላቸዉም።ሥልጣን ያለዉ የጦርነት ፓርቲ ነዉ።እነሱ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ፣ እንዲሕ አይነቱ አሳዛኝ ድቀት፣ጦርነቱም ይቀጥላል።»

ጉባኤዉ አርብ ሊጀመር-ዕሁድ የሩሲያ ባሕር ጠረፍ ጠባቂ ጦር የሩሲያ የባሕር ክልልን ጥሰዋል ያላቸዉን 3 የዩክሬን የባሕር ኃይል መርከቦች ከነ-ወታደሮቻቸዉ ከማረከ ወዲሕ ዳግም የናረዉ የሁለቱ የቀድሞ ሶቭየት ሕብረት ሪፐብሊኮች ጠብ፣ የኃያል ሐብታም ሐገራት መሪዎችን ትኩረት ስቧል ።

መሪዎቹ ቦኒስ አይሪስ የገቡት የሶሪያን ዉድመት፤ የየመኖችን ዕልቂት፤ የጋዜጠኛ ኻሾጂን ግድያን እንደ ሁለተኛ ርዕሥ ከየዶሴያቸዉ ዶለዉ ነዉ።ይሁንና ከራሳቸዉ ከፑቲን ቀጥሎ ግን ከመራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እኩል፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ጠብን ጉዳዩ ያደረገ መሪ ከነበረ-ኢማኑኤል ማክሮን ቀዳሚዉ ናቸዉ።

የአዉሮጳ ሕብረት በይፋ ያልፀደቀ መሪ የሚባሉት አንጌላ ሜርክል ከፖለቲካዉ ዓለም ለመገለል አንድ ሁለት ማለት ከጀመሩ ወዲሕ፣ ያልፀደቀ የመሪነቱን ሥልጣን ለመያዝ ይጣጣራሉ የሚባሉት ማክሮ ቦኒስ አይሪስ ላይ የመከሩ፣የተወያዩ የተስማሙ-የተቃወሙት ጉዳይ አስተንትኖ ሳያበቃ ፓሪስ በተቃዋሚዎቻቸዉ ተጥለቅልቃ ትነድ ገባች።

Argentinien G20 Gipfel - Putin und Merkel
ምስል picture-alliance/TASS/M. Klimentyev

ምክንያቱ የኑሮ ዉድነት ነዉ። በተለይም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረት።ማክሮ ጉባኤዉ በተጀመረበት ዕለት አርብ ከሳዑዲ አረቢያዉ ልዑል ከአልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ላፍታ ቆም ብለዉ ያወጉት የነዳጅ ዋጋ ንረት ላስቆጣዉ ሕዝባቸዉ ነዳጅ ፍለጋ አልነበረም።ከአልጋወራሹ ጋር ሲያወጉ የተነሱት ፎቶ እና ፊልም ግን ለሪያድ ፕሮፓጋንዲስቶች መሪያችን «አልተገለሉም» ለማለት ጥሩ ማስረጃ ነዉ የሆነዉ።

በየመኑ እልቂት፣ በተለይ ደግሞ በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ግድያ የሰብአዊ መብት፤ የፕረስ ነፃነት፤ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች «ዓይንሕ ላፈር» ያሏቸዉ አልጋወራሽ ቢን ሰልማንን ለመክሰስ የአርጂቲና የሕግ ባለሙያዎች መረጃ ማሰባሰብ መጀመራቸዉ ተዘግቦ ነበር።ሰዉየዉ ግን ዳኛም ፖሊስም ሳይገላምጣቸዉ ከቦኒስ አይሪስ ንዋክቾት ሞሪታንያ ገብተዋል። ከዳባባይ ተቃዉሞ ግን እዚያም አላመለጡም።

ቡድን 20 ከሚያስተናብራቸዉ ሐገራት ብቸኛይቱ አረባዊት ሐገር ሳዑዲ አረቢያ ናት።በዘንድሮዉ ጉባኤ ሳዑዲ አረቢያን የወከሉት ልዑል አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ከሌሎቹ መሪዎች መገለላቸዉን ለማወቅ የሚሻ «የቤተሰብ» በተባለዉ ፎቶ የቆሙበትን ካየ ብዙም አስተንታኝ አይፈልግም።

አልጋወራሹ፣ ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር የተለዋወጡት «ብሮ ፋይቭ» የሚባለዉ ዓይነት ሰላምታ ግን ከሁለቱ መሪዎች ወዳጅነት ይልቅ ሁለቱ መሪዎች ከተቀሩት መገለላቸዉን ጠቋሚ ነዉ ባዮች ብዙዎች ናቸዉ።አምና ከብዙዎቹ መሪዎች ተገልለዉ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዘንድሮ በቡሽ ሞት፤ቀዝቀዝ ባለ አቀራረብም፣ ወይም እንደ ቢን ሰልማን ይበልጥ የተገለ መሪ በመኖሩ ሰበብ ዘንድሮ ከቡድኑ አባላት ይበልጥ የተቀየጡ መስለዋል።  

ትራምፕ በተለይ ከቻይናዉ ፕሬዝደንት ቺ ሺ ፒንግ ጋር ባደረጉት ዉይይት የከፈቱትን የንግድ ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ ለማቆም መስማማታቸዉ ለብዙዎች እፎይታ ነዉ-የሆነዉ።የሁለቱ መሪዎች ዉይይት በእራት ግብዣ የታጀበ ነበር።የጎድን-ተዳቢት ስቴካቸዉን፤ በርጀንቲና ዋይን እያወራረዱ፤ በሹካ፤ቢላ፤ብርጭቆዉ ቅጭልጭልታ መሐል የተለዋወጧቸዉ ቃላት በገጠሙት ጦርነት ከሳሪ አንጂ አሸናፊ አለመኖሩን ማወቃቸዉን መስካሪ ናቸዉ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈዉ መስከረም የቻይናዉ መሪ «ከእንግዲሕ ጓደኛዬ አይደሉም» ብለዉ ነበር።ባለፈዉ ቅዳሜ ግን «ጥብቅ ቀዳጅ ነን» አሉ። «ፕሬዝደንት ቺ እና እኔም ራሴ (ድርድሩ ጥሩ ይሆናል) የሚል ተስፋ አለን።እስደናቂ ግንኙነት መስርተናል።በብዙ ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን።ንግድ አንዱ ነዉ።የሆነ ደረጃ ላይ ለቻይናም ለዩናይትድ ስቴትስም ጠቃሚ የሆነ ነጥብ ላይ እንደርሳለን።ከፕሬዝደንት ቺ ጋር ያለን ግንኙነት በጣም ልዩ ነዉ።ምናልባትም ለሁለቱም ሐገራት የሚጠቅም ነገር ላይ ለመድረስ የሚረዳንም ይኸዉ ነዉ።»

የቺ አፀፋ።-«ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ፣በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ሁለት ጠናካራ ሐገራት ናቸዉ።ለዓለም ሠላም እና ብልፅግና ትልቅ በጣም ጠቃሚ ኃላፊነት አለባቸዉ።ለዓለም ሠላም እና ብልፅግና ልናገለግል የምንችለዉ (ሁለታችን) ስንተባበር ብቻ ነዉ።»

Argentinien G20 Gipfel - Putin und bin Salman
ምስል picture alliance/AP Photo/N. Pisarenko

ቢያንስ ለጊዜዉ ለመተባበር ተስማምተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ወደ ሐገሯ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የአስራ-አምስት በመቶ የቀረጥ ጭማሪ ለማድረግ ወይም እስካሁን 10 በመቶ የነበረዉን ቀረጥ ወደ ሃያ-አምስት ከመቶ ከፍ ለማድረግ ያሳለፈችዉን ዉሳኔ ለዘጠና ቀናት ያክል አንስታለች።ቻይናም በዘጠናዎቹ ቀናት ዉስጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ብዙ ቢሊዮን የሚያወጣ ሸቀጥ ለመሸመት ተስማምታለች።

የንግድ ጦርነት ተኩስ አቁሙ በሚፀናባቸዉ ዘጠና ቀናት ዉስጥ የሁለቱ ሐገራት ባለስልጣናት አግባቢ ነጥብ ለማግኘት ተጨማሪ ድርድር ያደርጋሉ። የዓለም አንደኛ እና ሁለተኛ ቱጃር መንግስታት መስማማት ለ18ቱ መንግሥታት በተለይም ለባለ ኢንዱስትሪዎቹ ሐገራት ጠቃሚ፣ ለመሪዎቹም አስደሳች ነዉ።

የንግድ ልዉዉጥን፤ የገንዘብ እና የሸቀጥ ዝዉዉርን ለማጠናከር የዛሬ አስር ዓመት ግድም የተመሰረተዉ ቡድን 20 እንደ ብዙዎቹ ጉባኤዎች ሁሉ የዘንድሮዉም ፖለቲካ ተጫችኖታል።መሪዎቹ አምና እና ሐቻምና ከነበረዉ ጉባኤ ይልቅ ባሁኑ የተግባቡ መስለዋል።በጉባኤዉ ማጠቃላይ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ በተለይ የተፈጥሮ ጥበቃን የሚመለከተዉ ክፍል ግን የሚመለከተዉ 19ኙን ሐገራት ብቻ ነዉ።አሜሪካን አይመለከትም።የትራምፕዋ አሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ይጋይ እንጂ፣ ስምምነቱም የተፈጥሮ ሐብትን ማስጠበቁም አይመለከታትም።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሠ