1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች ሮሮ በደሴ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2014

አማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የገቡ የአካባቢው ተፈናቃዮች ለርሀብና እርዛት ተዳርገናል አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በቂ ባይሆንም ርዳታ እያገኙ እንደሆነ አመልክተዋል። በሰሜንና ደቡብ ወሎ አስተዳደሮች የተፈናቃዩ ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመሆኑ ለማስተዳደር አስቸጋሪ መሆኑም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/42FHp
Internally displaced Persons in Dessie
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አማራ ክልል ተፈናቃዩ 1 ሚሊዮን 900 ሺህ ደርሷል

አማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የገቡ የአካባቢው ተፈናቃዮች ለርሀብና እርዛት ተዳርገናል አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በቂ ባይሆንም ርዳታ እያገኙ እንደሆነ አመልክተዋል። በሰሜንና ደቡብ ወሎ አስተዳደሮች የተፈናቃዩ ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመሆኑ ለማስተዳደር አስቸጋሪ መሆኑም ተገልጧል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ከሰሜን ወሎና ከደቡብ ወሎ  ዞን ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች መጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ ጋር የሚኖሩ ተፈናቃዮች እርዳታ አላገኘንም ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል። አንድ ተፈናቃይ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት ታጣቂዎች ቆቦ ከተማ ላይ ያለውን ይዘርፋሉ፣ የሌለውን ደግም ያሰቃያሉ። ያን በመፍራት ሰሞኑን በአፋር አሳኢታ አቋርጠው ደሴ ቢደርሱም ያገኙት ነገር የለም። ሌላዋ ተፈናቃይ ደግሞ ቀደም ሲል ይረዱን የነበሩ ሰዎች አሁን የሉም፣ አዳዲስ ተፈናቃዮችም በየቀኑ እየመጡ ነው፣ ያም ሆኖ በችግር ላይ እንደሆኑ ገልጠዋል። አንዳንዶቹ እንደተቸገሩ ቢናገሩም በቂ ባይሆንም ርዳታ የደረሳቸው እንዳሉ ደግሞ አንድ ተናግረዋል፣ ሆኖም ሁሉም ተፈናቃዮች እኩል አይረዱም የሚል ቅሬታ አላቸው።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የተፈናቃዩ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ያን ለማስተናገድ ተቸግረናል ብለዋል። ሆኖም የሚቀድሙ ሥራዎችን እያስቀደምን ርዳታው ለሁሉም እንዲደርስ እናደርጋለን ነው ያሉት። የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር እንዲሁ የተፈናቃዩና ያለው አቅርቦት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ለ500ሺህ ተፈናቃይ የመጣ እርዳታ በመኖሩ ከዛሬ ጀምሮ ክፍፍል እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ከተፈናቃይነት ተቀንሰናል፣ እርዳታ አይሰጠንም የሚሉ ቅሬታዎችን በተመለከተ ኃላፊዎቹ «ከፍተኛ ደመወዝ በመንግስት የሚከፈላቸው፣ ዳኞች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ቤተሰቦቻቸው እርዳታ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ ይህን አናስተናግድም» ብለዋል። 

በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 900 ሺህ መድረሱንና አጠቃላይ በክልሉ ያለ ተፈናቃ ደግሞ 1 ሚሊዮን 900 ሺህ መድረሱን የክልሉ አደጋ መከልካልና ምግብ ዋስትና ቢሮ አመልክቷል።

ዐለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ