1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት የተጎዱ የአማራ ክልል አካባቢዎች ትምህርት መጀመሩ 

ማክሰኞ፣ ጥር 17 2014

በአማራ ክልል ጦርነት በነበራቸው የምስራቅ አማራ ዞኖች በአብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ያልተሟሉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ትምህርት መጀመሩን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ተማሪዎችና መምህራን ትምህርት መጀመሩን ቢገልፁም መሰረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶች በመዘረፋቸውና በመውደማቸው በርካታ ጎዶሎዎች አሉ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/463G6
Äthiopien | Wondwossen Abe
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ቁሳቁሶች በመዘረፋቸውና በመውደማቸው በርካታ ጎዶሎዎች አሉ

በአማራ ክልል ጦርነት በነበራቸው የምስራቅ አማራ ዞኖች በአብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ያልተሟሉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ትምህርት መጀመሩን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ተማሪዎችና መምህራን ትምህርት መጀመሩን ቢገልፁም መሰረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶች በመዘረፋቸውና በመውደማቸው በርካታ ጎዶሎዎች አሉ ብለዋል፣ የወደሙና የተዘረፉ የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግም ታውቋል፡፡ 

ካለፈው ነሐሴ 2013 ዓም ጀምሮ የህወሓት ታጣቂ ኃይል በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች ወረራ በመፈፀም በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ማውደሙን የአማራ ክልል መንግስት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ውድመትና ዝርፊያ ከተካሄደባቸው ተቋማት የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ እንደተፈፀመበት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያመለክታል፤ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ተቋማት ሲወድሙና ሲዘረፉ መቢሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ አካባቢዎች በቅርቡ ከህወሓት ነፃ ከወጡ በኋላ ባልተመቻቼ ሁኔታም ቢሆን ትምህርት መጀመሩን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አቤ ለዶይቼቬለ ተናግረዋል፡፡

ተቋርጦ የነበረው የዘመኑ ትምህርት እንዲቀጥልና በዚሁ ዓመት እንዲጠናቀቅ አዲስ የጌዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶ ትምህርት መቀጠሉንም አብራርተዋል፡፡ በነዚሁ አካባቢዎች 4 የመምህራን ኮሌጆች ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ መፈፀሙን አስታውሰው በተመሳሳይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡በከሚሴ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር ሁሴን እንድሪስ ትምህርት መጀመሩን አመልክተው የተጓደሉ ያሏቸውን ደግሞ አብራርተውልናል፡፡በዚሁ ከተማ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነቸው ምሰይባ አደም ከአንድ ወር ማቋረጥ በኋላ ሰሞኑን ትምህርት መጀመሯን ተናግራለች፡፡በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል 1ሚሊዮን 900ሺህ ተማሪዎች፣116ሺህ መምህራን ተፈናቅለው እንደነበር፣ 4ሺህ107 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን አሊያም መዘረፋቸውን የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል፣ ተቋማቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ 20 ቢሊዮን ብር ስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በጦርነት ስር የነበሩ አብዛኘዎቹ ትምህርት ቤቶች ስራ እየጀመሩ ቢሆንም በሰሜን ወሎና ዋኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ግን ትምህርት ማስጀመር እንዳልተቻለ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ