1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

ሰኞ፣ ኅዳር 14 2013

ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩት “እኛ የተረዳንው እና የተቀበልንው ከህወሓት ጋር መንግሥትን ለማደራደር አይደለም” ያሉት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም "የተለያዩ መንግሥታት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ያ ፍላጎት አለ ማለት በዚህ በኩል ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3leuT
Äthiopien Billene Seyoum
ምስል DW/Yohannes G. Egzihaber

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የመረጧቸው ሶስት የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት የኢትዮጵያን ፌድራል መንግሥት ከህወሓት ለማደራደር አይደለም ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ “ልዑካኑ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ለማሸማገል” በመጪዎቹ ቀናት ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ ቢሉም ቢልለኔ ግን አስተባብለዋል።  

ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩት “እኛ የተረዳንውም፤ የተቀበልንውም ከህወሓት ጋር መንግሥትን ለማደራደር አይደለም ” ያሉት ቢልለኔ "የተለያዩ መንግሥታት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፤ ሊገልጹም ይፈልጋሉ። ያ ፍላጎት አለ ማለት በዚህ በኩል ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ቢልለኔ “በእኛ በኩል ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ [በደቡብ አፍሪካ] ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው። ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋ ውይይትም እያደረጉ ነው። እዚያ በነበራቸው ቆይታ እና ውይይት መሠረት እነሱ ደግሞ ቀጣይ ልዑክ እዚህ ልከው ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንዲነጋገሩ ተቀብለናል። ይኸ የድርድር ወይም የሽምግልና ጉዳይ ከህወሓት ቁጭ ብሎ ወደዚያ አይነት ይገባል ማለት አይደለም” ብለዋል።

የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ክጋሌማ ሞትላንቴ እና የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖን ልዩ ልዑክ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ሊልኩ መዘጋጀታቸውን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ያስታወቁት በአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነታቸው በሚገለገሉት ይፋ የትዊተር ገጽ በኩል ነው።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

እሸቴ በቀለ