1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጎ ፈቃደኛዋ ጥሩወርቅ ዘለቀ በጀርመን

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 4 2013

ጀርመን ከኖረችባቸው 20 ዓመታት 15ቱን በበጎ ፈቃድ ስራ ነው ያሳለፈችው። በዚህ ነጻ አገልግሎትም በብር የማይተካ ብዙ የመንፈስ እርካታና ደስታ ሸምቻለሁ ትላለች ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ዘለቀ።ጀርመናዊ አግብታ ጀርመን ከመጣች በኋላ የባሏ ስም ተጨምሮ ጥሩወርቅ ኤንድረስ ትባላለች።የሚቀርቧት ቴሪ፣ ጥሩዬ እያሉ ያቆላምጧታል።

https://p.dw.com/p/3yoao
Tiruwork Zeleke
ምስል Privat

በጎ ፈቃደኛዋ ጥሩወርቅ ዘለቀ በጀርመን

በጀርመን ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል።በጎ ፈቃደኞቹ ታዳጊ ወጣቶችን በትምህርት በስፖርትና እርዳታ በሚያሻቸው ጉዳዮች ሁሉ ያለ ያለ ክፍያ ይረዳሉ። የታመሙና በእድሜ የገፉ ሰዎችን ይንከባከባሉ፣በእሳት አደጋ መስሪያ ቤት፣ ወይም ቀይ መስቀልን በመሳሰሉ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ውስጥ ያገለግላሉ፣ስደተኞችን ይደግፋሉ ያማክራሉ ጀርመንኛ በደንብ ለማይረዱ የውጭ ዜጎች በአስተርጓሚነት ጉዳዮቻቸውን በማስፈጸምና በመሳሰሉት መንገዶች የነጻ አገልግሎቶች ይሰጣሉ። በዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን የምናስተዋውቃችሁ ትውልደ ኢትዮጵያዊት እንግዳችን ከነዚህ በጎ ፈቃደኞች አንዷ ናት። ጀርመን ከኖረችባቸው 20 ዓመታት አስራ አምስቱን በበጎ ፈቃድ ስራ ነው ያሳለፈችው። በዚህ ነጻ አገልግሎትም በብር የማይተካ ብዙ የመንፈስ እርካታና ደስታ ሸምቻለሁ ትላለች ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ዘለቀ።ጀርመናዊ አግብታ ጀርመን ከመጣች በኋላ የባሏ ስም ተጨምሮ ጥሩወርቅ ኤንድረስ ትባላለች።የሚቀርቧት ቴሪ፣ ጥሩዬ እያሉ ያቆላምጧታል።የዛሬው ዝግጅታችን ወይዘሮ ጥሩወርቅንና የበጎ ፈቃድ ስራዋን ያስተዋውቀናል። 

Tiruwork Zeleke
ምስል Privat

በሕይወቷ  ለበጎ ፈቃድአገልግሎት የምትሰጠው ቦታ የተለየ መሆኑን የገለጸችልን ወይዘሮ ጥሩወርቅ እንደምትለው አገልግሎቱን በስፋት በጀርመን ትስጥ እንጂ፣ ኢትዮጵያ እያለችም እገዛ የሚያሻቸው አቅመ ደክሞችና ልጆችን አቅሟ በፈቀደው መጠን መርዳት ልምዷነበር።ከሀገርዋ የተከተላትን ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ጀርመን ከመጣች በኋላ አሳድጋ እገዛዋንም አጠናክራ ቀጠለች።በመጣች በስድስት ዓመትዋ ነበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጀመረችው።  
ጥሩወርቅ በጀርመን አገልግሎቱን የምትሰጠው በበጎ ፈቃደኝነት ከመዘገቧት ድርጅቶችና ግለሰቦች እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው እንዳለ ጥቆማ ሲደርሳት ነው።በመስኩ እውቀቷን ለማስፋትና እውቅናን ለማግኘትም የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዳለች።ከመካከላቸው አንዱ ካሪታስ የተባለው የእርዳታ ድርጅት የሚሰጠው ስልጠና አንዱ ነው።መቅደስ ፈቃደ፣ወይዘሮ ጥሩወርቅን የምታውቃት የዛሬ ሰባት ዓመት ነው።ያኔ ነፍሰ ጡር ነበረች። በአደገኛ የባህር ጉዞ ከሊቢያ ኢጣልያ የገባችው መቅደስ ወደ ኦስትሪያ ከሄደች በኋላ ወደ ጀርመን ለመሻገር ስትሞክር በያዘችው የተሳሳተ ወረቀት ምክንያት ኦስትርያ ትታሰራለች። ከርስዋ ቀድሞ ጀርመን የገባው ጥሩወርቅ በምትኖርበት በራይንባህ ከተማ የሚገኘው ባለቤቷ ይህን ለወይዘሮ ጥሩ ወርቅ ይነግራታል።ሰውን ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ የምታደርገው ጥሩወርቅ ፣ እንደሰማች ጊዜ ሳታጠፋ ፣ያለችበት እስር ቤት ደውላ ጉዳዩን አጣርታና አስረድታ ከእስር እንድትፈታ እንደረዳቻት መቅደስ ትናገራለች።
በጀርመን ህይወትዋ የጥሩወርቅ እርዳታ አልተለየኝም የምትለው መቅደስ በተለይ የበኩር ልጇውን እዚሁ ጀርመን ስትገላለገል ጥሩወርቅ ከጎኗ ስለነበረች ካልተጠበቀ አደጋ አድናኛለች ትላለች።
ጥሩወርቅም በጎርጎሮሳዊው 2013 መቅደስ የነበረችበትን ሁኔታና በኋላም የሆነው እንዲህ ታስታውሳለች።ጥሩወርቅ ፣መቅደስን ከዚህ አደጋ መጠበቅ የቻለችበት ይህ አጋጣሚ  ከምትደሰትባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤቶች አንዱ ነው።ኤርትራዊው ከሰተ ፍታዊና ጥሩወርቅ ከጎርጎሮሳዊው 2015 አንስቶ ነው የሚተዋወቁት።ሜከንሃይም የሚባለው ከተማ ውስጥ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ እያለ ነበር ጥሩዬ የሚላትን ጥሩወርቅን ያገኛት።ይላል።የከሰተና የጥሩ ወርቅ ትውውቅ ቀጥሎ  አሁን ደግሞ ቤተሰቦቹ ወደ ጀርመን ሊመጡ ስለሆነ ጥሩ ወርቅ በቤት ፍለጋ እያገዘችው ነው።ይጠያየቃሉም። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭዋ ጥሩ ወርቅ በቅርቡ የምትኖርበትን ራይንባህ ከተማን ጨምሮ  ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰባቸው የተለያዩ የጀርመን ከተሞች እየሄደች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠች ነው።ልጅዋን ጭምር ይዛ የምትንቀሳቀሰው ጥሩ ወርቅ ጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዚህን መሰሉ የበጎ አድራጎት ስራ በስፋት እንዲሳተፉ ትመክራለች።የጥሩወርቅ የወደፊት እቅድዋ ቢሳካላት በሀገርዋ ድጋፍ የሚያሻቸውን ወገኖች እዚያው ሄዳ ማገልገል ነው። 

Tiruwork Zeleke
ምስል Privat

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ