1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉጂ ዞን የቀጠለው የአዲስ አስተዳደራዊ ዞን ምስረታ ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2015

ይህ የህዝብ ቁጣ መንገድ በመዝጋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን አስተጓጉሏል፡፡ በተነሳው አመጽም እስካሁን ከቦሬ ሦስት ከአዶላ አንድ ሰው ህይወታቸው አልፈዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4OMEI
Shakiso Town
ምስል Yidnekachew Gashaw

በጉጂ ዞን የቀጠለው የአዲስ አስተዳደራዊ ዞን ምስረታ ተቃውሞ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል በማለት ምሥራቅ ቦረና በሚል የመሰረተው የክልሉ 21ኛ ዞን አሁንም ማወዛገቡን እንደቀጠለ ነው፡፡
የጉጂ ዞን በመሆን ለዓመታት ያገለገለችውን ነገሌ ከተማ ነገሌ ቦረና በሚል ስያሜ ይመሰረታል ለተባለው ለአዲሱ ዞን ማስረከቡ በጉጂ ዞን በዋናነት ቁጣውን የቀሰቀሰ ዐቢይ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የክልሉ መንግሥት ምክር ቤት አደረኩ ባለው 6ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምሥራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን በማገኛነት መሰረትኩ ማለቱ በተለይም በጉጂ ዞን ባስነሳው ተቃውሞ ቢያንስ እስካሁን የአራት ሰው ህይወት ጠፍቷል፡
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች ውሳኔው ካልተቀለበሰ ለአከባቢው ሰላምና ፀጥታ አስቸጋሪ ያሉትን ስጋት ሊያስከትል እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡
«ሰሞኑን በመንግሥት አንድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህ ውሳኔም ለ20 ዓመታት ገደማ የጉጂ ዞን ሆና ስታገለግል የነበረችወን ነገሌ ከተማን ነገሌ ቦረና በሚል ስም ከጉጂ ዞን አስወጥቶ ምሥራቅ ቦረና በሚል ስያሜ ለተመሰረተው አዲስ ዞን መዋቅር ይሰጣል ነው የተባለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ዞን ከጉጂ ሊበን እና ጉሚ የልደሎ የተባሉ ሁለት ወረዳዎች እና ከባሌ ሦስት ወረዳዎችን ቆርሶ ለምሥራቅ ቦረና ዞን የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡ አሁን በከፍተኛ የድርቅ ችግር ውስጥ ላለው ህዝብ ሌላ እራስ ምታት ባልተገባው ነበር፡፡ ውሳኔው እንደተባለው ለመልካም አስተዳደር የተደረገ የሚመስል አይደለም፡፡»
ይህን አስተያየት የሰጡን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአዲስ ዞን ምስረታ ቅሬታ የገባቸው የጉጂ ዞን ቦሬ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሌላው በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት የሰባ ቦሩ ወረዳ አስተያየት ሰጪ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲቆይ ቢጠይቁም አስተያየታቸውን ግን አጋርተውናል፡፡ 
«ለ20 ዓመታት ገደማ የጉጂ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለችን ከተማ የኦሮሚ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ከጉጂ ዞን ወጥታ ወደ ምሥራቅ ቦረና ስለተደራጀች ወደዚያ ትግባ ነው የተባለው፡፡ ይህን የሚያክል ውሳኔ የትኛውም የዞኑ ነዋሪ በሚዲያ ነው የሰማው፡፡ ይህ በምን አይነት መንገድ ነው የሆነው? ማንስ ጠየቀ ? እንዴትስ ተጠና? በሚል የህዝቡ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ ለአስተዳደራዊ ቅልጥፍና ያስፈልጋልስ ቢባል ህዝቡን ማወያየት አይቀድምም ወይ? የሚል ነው ህዝቡን ያስቆጣው፡፡ ይህ የህዝብ ቁጣ መንገድ በመዝጋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን አስተጓጉሏል፡፡ በተነሳው አመጽም እስካሁን ከቦሬ ሦስት ከአዶላ አንድ ሰው ህይወታቸው አልፏል።»
ሌላው የአዶላ ሬዴ ወረዳ ነዋሪ ደግሞ የህዝቡን ጥያቄ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ያመሩ የአገር ሽማግሌዎች ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ሰልፎች እንዲቀንሱና ምላሹን በትዕግስት መጠባበቅ ይበጃል መባሉን በአስተያየታቸው ነግረውናል፡፡
«ሰልፎች አሁን ረገብ ብለዋል፡፡ አልፎ አልፎ መንገዶች የመዝጋት ችግር ይስተዋላል እንጂ ከላይ የሚሰጠውን ውሳኔ እንስማ በሚል ሰልፉ ገታ ተደርጓል፡፡ እናም ህዝብን ከህዝብ ጋር የማያናቁር ሁሉንም ማዕከል ያደረገ ቀና ምላሽ እንጠብቃለን፡፡ የተወሰነው ውሳኔ ድንገቴና ህዝብ መሃል መግባባትን የማይፈጥር ነው ብለን ነው የሰጋነው፡፡ ለወደፊትም ይህ ነገር በቀላሉ ይቆማል የሚል ግምት የለንም፡፡ ከላይ አንድ መፍትሄ መምጣት እንዳለበት ይሰማናል፡፡»
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረኩ ባለው 6ኛ የስራ ዘምን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምስራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና ሞያሌ፣ ጉቺ እና ዋችሌ ወረዳዎችን፤ ከጉጂ ጉሚ የልደሎ እና ሊበን ወረዳዎች እንዲሁም ነጌሌ ቦረና ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳዎችን በማካተት መሰረትኩ ብሏል፡፡ በውሳኔው መሰረት ከዚህ በፊት የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል የነበረችው ነገሌ፤ ነጌሌ ቦረና በሚል መጠሪያ የምስራቅ ቦረና ዞን መቀመጫ ትሆናለች፡፡ አዶላ ሬዴ ደግሞ የጉጂ ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን ነው የተወሰነው፡፡ 
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በጉጂ ዞን ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ተቃውሞና አለመረጋጋት እልባት የሚያገኘው በመርህ ላይ የተመሰረተ ውይይት ተደርጎ ሁሉንም የሚያስማማ ውሳኔ ሲወሰን ነው የሚሉት የዞኑ ነዋሪዎች፤ የችግሩ እልባት እስካ ህዝበ ውሳኔ የሚወስድ መሆን ይገባልም እያሉ ነው፡፡
ስለነዋሪዎቹ ቅሬታ ከመንግሥት መዋቅራዊ አስተዳደሮች ምላሽ ለመጠየቅ ለጉጂ ዞን ዋና አሰርተዳዳሪ ታደለ ኡዶ እና ለምክትላቸው አቶ አብዱራዛቅ በተደጋጋሚ ብንደውልም ፈቃደኝነታቸውን አላገኘንም፡፡ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሚዩኒኬሽ ቢሮ ኃላፊና ለብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳንም አስተያየታቸውን ለማካተት በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ለዛሬ አልተሳካም፡፡ 
ሥዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ