1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉባ ወረዳ ጥቃት በመፈጸም ከተጠረጠሩ ስምንቱ መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2 2012

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ጥቃት በመፈጸም ከተጠረጠሩ መካከል ስምንቱ በጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ መለሰ ˝ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ ነበረ። የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ከስምንት በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/3gfjo
Karte Äthiopien Metekel EN

በጉባ ወረዳ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ታጣቂዎች መካከል ቢያንስ ስምንቱ በጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት አስታወቁ። ባለፈው ሐምሌ 20 ቀን በተፈጸመው ጥቃት ከቆሰሉ ሰዎች መካከል የሶስቱ ሕይወት አልፎ የሟቾች ቁጥር 16 መድረሱን በመተከል ዞን የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ኩምሳሪ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ አቡጃር ቀበሌ ጥቃቱ የተፈጸመው ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። በጥቃቱ 13 ሰዎች ሲገደሉ አምስት ሰዎች ቆስለዋል።  ̋በዚህ ግርግር ውስጥ በእነሱ [በታጣቂዎቹ] አማካኝነት የጠፉ ንጹሀን ዜጎች አስራ ስድስት ደርሷል˝ ሲሉ አቶ አሕመድ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ አቶ አሕመድ እንዳሉት ታጣቂዎቹ ከክልሉ እና ከፌድራል መንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች በተደጋጋሚ ተጋጭተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ጥቃት በመፈጸም ከተጠረጠሩ መካከል ስምንቱ በጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ መለሰ ˝ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ ነበረ። የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ከስምንት በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች የግድያ እርምጃ በእኛ ታጣቂ ኃይል ተወስዷል" ቢሉም ኩነቱ የተፈጸመበትን ትክክለኛ ቀን ሳይናገሩ ቀርተዋል።

Äthiopien, Assosa - Ashadli Hassen, Präsident der Region Benishangul Gumuz
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን አስራ ሁለት ታጣቂዎች መገደላቸውን አስራ አራት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረው ነበርምስል DW/N. Dessalegn

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት መንግሥት በተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ሲናገሩ ይኸ የመጀመሪያቸው አይደለም። ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የክልሉ መንግሥት ተጠርጣሪዎች መገደላቸውን እና በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቆ ነበር። የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን "በተለይ በጉባ ወረዳ እና አጎራባች ወምበራ ወረዳ አካባቢ ሕግ የማስከበር ሥራ ለመስራት ተሞክሯል። በዚህ አግባብ በ12 ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ተችሏል፤ አስራ አራት የሚሆኑት ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለዋል" ሲሉ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።

እስካሁን ባለፈው ሐምሌ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። የክልሉም ይሁን የፌድራል መንግሥት ታጣቂዎቹ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ለማስተጓጎል ጥረት አድርገዋል ሲሉ ይከሳሉ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ  ̋የኅዳሴ ግድቡ ውኃ የሚተኛበት የምንጣሮ ሥራ ለማስተጓጎል ከውስጥም ከውጪም የሚሰጡ ተልዕኮዎችን በመቀበል ጫካ ውስጥ ሸፍተው ሥልጠና ሲያደርጉ ነበር˝ ሲሉ በድጋሚ ከሰዋል።  

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ ሐምደኒል በጥቃቱ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅ እንዳለበት መናገራቸውን የመተከል ዞን በፌስቡክ ባሰራጨው የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ዘገባ ላይ ተጠቅሷል። የጥቃቱ ፈጻሚዎች “የጉሙዝ ህዝብን ነፃ የሚያወጣ የራሱ ጦር ያስፈልገዋል” በሚል የተደራጁ፤ በሱዳን ጠረፍ አቡልታ በተባለ ልዩ ቦታ ካምፕ መስርተው የተኩስ ስልጠና የወሰዱ እና "በስነ-ምግባር ችግሮች ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከክልሉ የፀጥታ አካላት የተቀነሱትን እና ከአካባቢውን ወጣቶች የተመለመሉ መሆናቸውን ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ እንደተናገሩ ይኸው ዘገባ ይጠቁማል።

የክልሉ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ታጣቂዎቹ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ካደረጉት የተኩስ ልውውጥ በኋላ የተረፉት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ተናግረዋል። "ከዚያ በኋላ [የጸጥታ አስከባሪዎች ታጣቂዎችን] ከበዋቸው የተለያዩ ሞተር ብስክሌቶች˝ ተይዘዋል። ኃላፊው "ስንቅ የሚያቀብሉ እና ጉዳዩን የሚያስተባብሩ 121 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል˝ ብለዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የጉባ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እንደሚገኙበት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተናግረው ነበር። "የተጠረጠሩ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች አሉ" ያሉት የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ኩምሳሪ በበኩላቸው የሚሊሺያ እና የፖሊስ አባላትን ጭምር በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አረጋግጠዋል።

"የታጣቂ ቡድኑ አባላት ቁጥር እየተመናመነ ነው" የሚሉት አቶ መለሰ ክረምት በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ ተናግረዋል። "በጣም ጥቂት የሚባሉ ቡድኖች አሁንም በተለያዩ አቅጣጫዎች ሸፍተው አሉ። እነሱንም የጸጥታ ኃይሎች እየተከታተሏቸው ነው" ሲሉ አክለዋል። አንድ አርፒጂ፣ ስድስት ክላንሽንኮቭ፣ 293 የብሬን እንዲሁም 30 የክላሽ ጥይቶች መያዛቸውንም ባለሥልጣናቱ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ