1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉራጌ ዞን የሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውሳኔያቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቀረቡ

ሰኞ፣ ነሐሴ 9 2014

ምክር ቤቶቹ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት ባለፈው ቅዳሜ በክላስተር ለመደራጀት ፈላጎት እንዳላቸው በየጉባዔዎቻቸው ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወረዳ ምክር ቤቶቹ የቀረበውን ጥያቄ መቀበሉን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት አንድ የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊ ምክር ቤቱ ጥያቄውን በመመርመር ውሳኔ ይሰጣል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4FYty
Äthiopien | Bezirksräte in Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW

5ቱ ወረዳዎች ደቡብ ክልልን 2 የሚከፍለው የክላስተር አደረጃጀት ገቢራዊ ይሁንልን ሲሉ ጠይቀዋል


በጉራጌ ዞን የሚገኙ አምስት የወረዳ ምክር ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል ለሁለት የሚከፍለው የክላስተር አደረጃጀት ‹‹ ገቢራዊ ይሁንልን ›› ሲሉ ጥያቄቸውን ለአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ አቀረቡ ፡፡  ምክር ቤቶቹ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በክላስተር ለመደራጀት ፈላጎት እንዳላቸው በየጉባዔዎቻቸው ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወረዳ  ምክር ቤቶቹ የቀረበውን ጥያቄ መቀበሉን  ለዶቼ ቬለ DW  ያረጋገጡት አንድ የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ጥያቄውን በመመርመር ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡

በጉራጌ ዞን የሚገኙ አምስት የወረዳ ም/ቤቶች የደቡብ ክልልን በሁለት አስተዳደራዊ ክልሎች ለማደራጀት የቀረበው ሀሳብ ‹‹ ገቢራዊ ይሁንልን ›› ሲሉ ዛሬ ጥያቄያቸውን ለአገሪቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት አቅርበዋል፡፡ ጥያቄያቸውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያቀረቡት የማረቆ ፣ የመስቃን ፣ የቀቤና እና የሶዶ ወረዳ ም/ቤቶች ናቸው፡፡

የወረዳ ም/ቤቶቹ አሁን ያለው የደቡብ ክልል በአዲስ መልክ ይዋቀራል በተባለው የክላስተር አደረጃጀት እንዲካተቱ የሚጠይቀውን ደብዳቤ ለፌዴሬሽን ም/ቤቱ ያስገቡት በዋና አፈ ጉባኤዎቻቸው አማካኝነት ነው፡፡ ወረዳዎቹ ከሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳ ጋር በመጣመር የጋራ ክልል ለመመሥረት ፍላጎት እንዳላቸው በደብዳቤቸው ላይ መግለጻቸውን የማረቆና ፣ የምሥራቅ መስቃን ወረዳ ም/ቤት ዋና አፈጉባኤዎች ገልፀዋል፡፡ የቀረበው ጥያቄ ም/ቤቶቹ ከትናንትና በስቲያ ቅዳሜ በየጉባኤዎቻቸው ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ነው የማረቆ ወረዳ ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ስኳሬ ኮሊሶ የምሥራቅ መስቃን  አፈጉባኤ አቶ ዓለሙ ግዛው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት፡፡

የወረዳ ም/ቤቶቹ ዛሬ አቀረቡት በተባለው የአደረጃጀት ጥያቄ ዙሪያ ዶቼ ቬለ ማረጋገጫ የጠየቃቸው የፌዴሬሽን ም/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ ‹‹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወረዳ  ምክር ቤቶቹ የቀረበውን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን ጉዳዩን በመመርመር ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል ›› ብለዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተማራማሪ ናቸው ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ በክላስተር እንደራጃለን የሚለው ውሳኔያቸውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያቀረቡት የወረዳ ም/ቤቶች የሕዝብ ውክልና ያላቸው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ መምከራቸው በራሱ ችግር የለበትም ይላሉ ፡፡ ይሁንእንጂ አካሄዱ ላይ የሕግ ቅደም ተከተልን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን ረዳት ኘሮፌሰሩ ለዶቼ ቬለ  አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

Äthiopien | Bezirksräte in Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW

በደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት መሠረት አስተዳደራዊም ሆኑ  የማንነት ጥያቄዎች በቅድሚያ ለክልል የሕግ አውጭ ም/ቤት መቅረብ እንዳለበት ያስቀምጣል ያሉት ረዳት ኘሮፌሰሩ ‹‹ ም/ቤቱም ጥያቄው በቀረበለት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ በመስጠት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ያደርጋል ይላል ፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠም ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት ሊሄድ እንደሚችል ክፍት አድርጓል፡፡ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የወረዳ ም/ቤቶች ዛሬ አቀረቡት የተባለው የአደረጃጀት ጥያቄ ግን ሕጉ በሚጠይቀው ቅደም ተከተል መሠረት የተከናወነ ነው ለማለት ያስቸግራል ›› ብለዋል፡፡

የወረዳ ም/ቤቶች ጥያቄ ሕጋዊ የአቀራረብ ሥርዓቱን የተከተለ አይደለም በሚለው ሀሳብ ላይ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የፌዴሬሽን ም/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ‹‹ አሁን ም/ቤቶቹ እያቀረቡ ያሉት የአካሄዱ ጉዳይ ሳይሆን በዞን ምክር ቤት የተላለፈው የአደረጃጀት ውሳኔው የሕዝብ ፍላጎት ነው ወይ ? ሌሎች ያሳለፉት ውሳኔ ተፈጻሚ ሊሆንብን አይገባም ወይ ? ይሄ ይጣራልን በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ምላሽ የሚጠይቁ በመሆናቸው የሕግ መጣረስን የሚያስከትል አይሆንም ፡፡ ነገር ግን ከወረዳ ም/ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ጋር ባደረግነው ውይይት የጥያቄው አቀራረብ ሕጉ የሚጠይቀውን ሂደት ተከትሎ መምጣት እንዳለት ተማምነናል፡፡ በቅድሚያ  የጉራጌ ዞን ም/ቤት ፣ ቀጥሎም በደቡብ ክልል ም/ቤት ከታየ በኋላ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ የታወቀ ነው ››  ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል የሚገኙ የዞንና  የልዩ ወረዳ ም/ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት የክላስተር መዋቅር ለማደራጀት የሚያስችለውን ሀሳብ በመደገፍ ጥያቄያቸውን ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል ፡፡ በአንጻሩ የጉራጌ ዞን ም/ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ የክላስተር አደረጃጀትን ውድቅ በማድረግ ጉራጌ እራሱን በቻለ ክልል እንዲዋቀር የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወቅ ነው ፡፡ የአገሪቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት የፊታችን ሐሙስ በጠራው ጉባኤ ከየአቅጣጫው የቀረቡ የደቡብ ክልል አደረጃጀት ጥያቄዎችን በመመልከት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡


 ሸዋንግዛው ወጋየሁ 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ